የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ሰኞ የሕወሃትን መልዕከተኞች ፍዳ ሲያሳዩዋቸው ዋሉ – ሸገር ዜና

19 Sep

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በሕይወት ፍሬ ስብሃት

በዚህ አዳራሽ ውስጥ የተሰበሰቡት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ሲሆኑ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አድማሱ ፀጋዬ እንዲሁም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ጄሉ ዑመር እና የአካዳሚክ ስታፍ ዳይሬክተሩ ዶክተር ተመስገን ቡርቃ ተገኝተዋል፡፡ በመካከላቸው የዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ካሣ ተክለብርሃን ተገኝተዋል፡፡

መንግሥት ከመሥከረም 4 እስከ 16 ድረስ በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ ምሁራንና ተማሪዎች፣ ወላጆችና የአስተዳደር ሠራተኞች እንዲወያዩ ባሳሰበው ምክንያት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሠራተኞቹን በአራት አዳራሽ ከፍሎ ዛሬ ውይይቱን ጀምሯል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ለብቻቸው እንዲወያዩ በተወሰነላቸው የስብሰባ ማዕከል ተገኝተን እንደተመለከትነው መምህራኑን ለማወያየት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም አቶ ካሣ ተክለብርሃን እና ዶክተር ተመስገን ቡርቃ ፊት ለፊት ተቀምጠዋል፡፡

ጉባዔው ከመጀመሩ አስቀድሞ በዩኒቨርስቲው ምሁራን መካከል በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብና በጋምቤላ ክልሎች ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች ኢትዮጵያዊያን ቢያንስ የህሊና ፀሎት እንድናደርግ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ጥያቄውን ዘለግ ባለ ጭብጨባ በአዳራሹ ውስጥ ያሉ ምሁራን ደግፈውታል፡፡

ምሁራኑ ለውይይት የተመረጡት ርዕሰ ጉዳዮች በኢሜይል እንደተላከላቸው አስታውሰው ርዕሰ ጉዳዮቹ ግን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የተነጋገርንባቸው በመሆናቸው ከንግግራችን በኋላ የመጡት ለውጦች ላይ መወያየት ይገባናል ሲሉ ሃሳባቸውን አሰምተዋል፡፡

ከተወያዬቹ መካከል ለዚህ ጉባዔና ውይይት ተብሎ አምስት ሚሊየን ብር መመደቡን ተናግረው ይህን ያህል በጀት ለድግግሞሽ ርዕሰ ጉዳይ መመደቡን እንደማይደግፉና ገንዘቡ ኑሮ ለከፋቸው ዜጐቻችን መቋቋሚያ እንዲሆን ይሰጥልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በአዳራሹ ያሉ ተሰብሳቢዎችም ሃሳባቸውን በታላቅ ጭብጨባ አጅበውታል፡፡

በዚህ መልኩ በተጀመረው የዛሬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ውይይት ሰብሳቢው አቶ ካሣ ተክለብርሃን የህሊና ፀሎት እንዲደረግ ከፈቀዱ በኋላ መንግሥት ያሰናዳቸው ሰነዶች በዩኒቨርስቲው ኃላፊዎች በኩል መቅረብ ጀምሯል፡፡

የከፍተኛ ትምህር ተቋማት በ25 ዓመት የትምህርት ሂደት ውስጥ የነበራቸው ሚና ምንድን ነው የሚለው ሰነድ በቀዳሚነት ለውይይት ቢቀርብም ጥቂት የማይባሉ መምህራን ከስብሰባው አዳራሽ መውጣታቸውን ተመልክተናል፡፡

%d bloggers like this: