ራዕይ ገዳይ አደረጃጀቶች!

20 Sep

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በሸንቁጥ አየለ
 

– አጼ ቴዎድሮስ ሲፎክሩ እንዲህ ይሉ ነበር “የኢትዮጵያ ባል የእየሩሳሌም እጮኛ”፡፡ ቴዲ እንዲህ የሚሉት ዘመነ መሳፍንት ለ179 አመታት እንክት አድርጎ በበላት፡፡ ፍርስርሷን ባወጣትና በጨለማ ዉስጥ በምትደናገር አንድ የጎንደር ቀበሌ ተወልደዉ ነዉ፡፡ በሳቸዉ ዘመን ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አልነበረችም፡፡ ትግሬ ለብቻዉ: ሸዋ ለብቻዉ: ጎንደር ለብቻዉ: ወሎ ለብቻዉ; ጎጃም ለብቻዉ; ወለጋ ለብቻዉ: ምስራቁ ለብቻዉ እና ደቡቡ ለብቻዉ ጎንዶ/ጎጆ ቀይሶ/ ነበር፡፡

– ይሄ ሁሉ ጎናዴ (ጎጆ ቀያሽ) ሁሉም ጦረኛ ነበር::በድርድርና በማግባባት እሽ ብሎ የሚመጣ ሀይል አልነበረም፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ጦረኛ ነበሩ እና የጦረኞችን ባህሪ በደንብ ያዉቁት ነበር፡፡

– ቴዎድሮስ ግን በጨለማ ዉስጥ በትንሽ መንደር ዉስጥ ሆነዉ ራዕያቸዉ ኢትዮጵያ ብቻ አልነበረችም::እየሩሳሌም ጭምር እንጅ፡፡

– ጥንታዉያን ኢትዮጵያዉያን ከሙሴ ሚስት : ከኢትዮጵያዊቷ ሳጲራ ጋራ ወደ እስራኤል ሀገር ሙሴን እየረዱና የሙሴን ጽላት እየመሩ ሄደዉ ነበር፡፡ እስራኤላዉያን ሀገራቸዉ ሲደርሱ 12 እጣ ተጣጥለዉ እስራኤልን ለመከፋፈል ተነሱ፡፡ በመሃል በርካታ ቁጥር የነበራቸዉ ኢትዮጵያዉያንም “ለእኛም እጣ ይዉጣልን እንጅ” ሲሉ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ እናም 13ኛ ሆነዉ እጣዉ ዉስጥ ገቡ፡፡ በሚደንቅ ሁኔታ ለኢትዮጵያዉያን እየሩሳሌም ደረሳቸዉ፡፡ እናም ጥንታዉያን ኢትዮጵያዉያን ነገስታት እየሩሳሌምን የኢትዮጵያ ግዛት አካል አድርገዉ ይቆጥሯት ነበር፡፡ ለዚህም ነዉ ባለ ታላቅ ራዕይዉ አጼ ቴዎድሮስ “የኢትዮጵያ ባል የእየሩሳሌም እጮኛ” ይል የነበረዉ፡፡ ኢትዮጵያንም ሆነ እየሩሳሌምን ጠቅልዬ በክንዴ ግዛት ስር አደርጋቸዋለሁ ሲል፡፡

– ዋዉ! ምን አይነት ጀግንነት? ምንስ አይነት ራዕይ ነዉ? አሁን ዘመን ላይ የቆመ ፖለቲከኛ ከሸዋ ጋር መደራጀት አልችልም ስለዚህ ጎጃም ግሎባል አሊያንስ ይሻለናል ይልሃል፡፡ ሌላዉም ከጎንደር ጋር መደራጀት አልችልም ስለሆነም ሸዋ የኢትዮጵያ አንድነት ብሎህ ዘጭ ይላል፡፡

ሌላዉም ለሚስጥር ጥበቃ መደራጀት ያለብን በጎንደር ህብረት ነዉ ይልሃል፡፡ በዚህ አይበቃም፡፡ ኦሮሞ እና አማራ ከንግዲህ በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ስር መደራጀት ማለት ጸጉር ከምላስ መንቀል ነዉ ብሎህ ብዙ ማብራሪያ ይሰጥሃል፡፡ ምነዉ ስትለዉ;- ኦሮሞዉ ጉልበት አዉጥቷል ወይም አማራዉ እየተደራጀ ነዉና ብኋላ ስልጣኑን ቀድሞ እጁ ያደርጋል ብሎ ያስፈራራሃል፡፡ ማስፈራሪያዉ ማለቂያ የለዉም::ከፈራህ የራስህ ጥላ ሊያስፈራህ ይችላል፡፡ የቴዎድሮስ ልጅ ከሆንክ ግን የሚነገረዉ ሁሉ አያሳምንህም፡፡

-በቴዎድሮስ ዘመን የወሎ ኦሮሞዎች ጠንካራ ጦረኛ ንግስት እየመራቻቸዉ ነበር፡፡ የጅማ መንግስትም የማይበገር ነበር፡፡ የሸዋ ነገስታት በምድር ላይ ያለ ጦርን ሁሉ እንሰብራለን ብለዉ የሚፎክሩ ነበሩ፡፡ የትግሬ ሀይል ጦርን እንሰራታልን ብሎ የሚታበይ ነበር፡፡ ጎጃም ላይ የነበሩ ነገስታት ከኛ በላይ ጦር አዋቂ ላሳር ብለዉ የሚፎክሩ ነበሩ፡፡

-ባለ ራዕይዉ ቴዎድሮስ ግን በልቡ እንዲህ አለ “ይሄ ሁሉ የዘመነ መሳፍንት መስፍንና ንጉስ እሽ ካለ በአንድ ይገብራል፡፡ እንቢ ካለም በሀይል ይሰበራል፡፡ ኢትዮጵያም እንደ ጥንቱ በአንድ ትመጣለች፡፡”

-እናም እንዳሰበዉ አስቦት አልቀረም፡፡ ኢትዮጵያን በባዶ እግሩ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ አሰሳት፡፡ የዘመነ መሳፍንትን ጦረኛ ሁሉ ሰባበረዉ፡፡ ሁሉ በአንድ ለጥ ሰጥ ብሎ እንዲገባ ሆነ፡፡ በምድር ላይ ያለን የጦር ሀይል ሁሉ የመስበር ጉልበቴ የታመነ ነዉ ያለዉ ሸዋ ሁለት ግዜ በቴዎድሮስ ላይ አመጸ፡፡ ሆኖም የማያዳግም ቅጣት ተቀጥቶ ሸዋ ለቴዎድሮስ ራዕይ ገበረ፡፡ ኢትዮጵያ ጸጥ ለጥ ብሎ ለቴዎድሮስ ራዕይ ሰገደ::ቢሆንም ገና የቀሩ ሀይሎች ነበሩ፡፡ የቴዎድሮስ ራዕይን ያነገበዉ ንጉሰ ነገስት ሚኒሊክ የቴዎድርሮስ ራዕይን ፈጸመለት፡፡

– አለመታደል ሆኖ አሁን ኢትዮጵያ እንደገና ትርምስ ዉስጥ ገብታለች፡፡ እራስ ስሁል ዘመነ መሳፍንትን ያመጣ የትግራይ መስፍን ነበር፡፡ ወያኔም በጎሳ ፖለቲካ ታጅሎ ዘመነ መሳፍንትን በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ዳግም እንዲያንዣብብ አድርጎታል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ በጨለማ ዉስጥ ቆመዉ እንደ ቴዎድሮስ ታላቅ ራዕይን ማዬት የሚችሉ ጀግኖችን እየተጣራች ነዉ::እነዚያ ጀግኖች ብቅ ይላሉ ብለን ስንጠብቅ ግን ከብሄር አደረጃጀት በወረድ ወደ ወንዝ አደረጃጀት ይዘዋት የሚነጉዱ ፖለቲከኞች ተነስተዉ በራዕይ ገዳይ የፖለቲካ አደረጃጀት እየተንቦጫረቁላት ነዉ፡፡

-ራዕይ ገዳይ አደረጃጀቶች የመጨረሻ ግባቸዉ ዳግም ዘመነ መሳፍንትን ማስፈን ይሆናል፡፡ ራስ ስሁል ከትግራይ ተነስቶ ዘመነ መሳፍንትን በኢትዮጵያ ላይ እንደጫነባት: ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስም ከ179 አመታት ብኋላ በጨለማ ዉስጥ ቆመዉ በማይታጠፍ ራዕያቸዉ ኢትዮጵያን ዳግም እንደፈጠሯት አይነት የታሪክ እራስን ደገማ ሂደት ይከሰት እንደሆነ አይታወቅም፡፡ አሁን ከትግራይ የተነሳዉ ወያኔ በኢትዮጵያ ላይ ዳግም ዘመነ መሳፍንትን ጋርጦባታል፡፡ የሀገሪቱም ፖለቲከኞች ወደ ዘመነ መሳፍንት ቁልቁለት በፍጥነት እየተንደረደሩ ይመስላል፡፡ የማይሆን የሚመስለዉ ሁሉ ይሆናል፡፡

-ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ባሰብኩ ቁጥር የንጉሰ ነገስት አጼ ቴዎድሮስ ራዕይና ቁመት እጅግ ገዝፎ ወደ ሰማያት ከፍታ ሲመጥቅብኝ በደስታ ፈገግ እላለሁ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ አሁንም ሲናገሩ ይሰማኛል “የኢትዮጵያ ባል የእየሩሳሌም እጮኛ” ሲሉ፡፡ ጨለማ በወረሰዉ ትንሽ ቀበሌ ዉስጥ ቆሞ እንዲህ ማሰብም ይቻላል፡፡

-የታላቅ ህዝብ ታሪክ ሲዘረጋ ድርሳኑ ታላላቅ አስተምህሮቶችን የያዘ ነዉ፡፡ መማር ከፈለግህ ያባቶችህን ድርሳን ገልጠህ አንብበዉ፡፡ በፍራት አትራድ፡፡ ምድር ቢንቀጠቀጥ የማይርዱ ባለ ራዕይ አባቶች እንደነበሩህ አስታዉስ፡፡ ታላቅ ህዝብ ታላላቅ ራእይ ያነገቡ ታላላቅ እንደሚወልድ አትርሳ፡፡ እናም ፖለቲከኛ ከሆንክ ታላላቅ ራዕዮችን ተከተል እንጅ በፍርሃት ወደ ቀበሌ ኅሳቤ አትንጎድ፡፡ የማይሰበር የሚመስለዉን ሁሉ እንደ ንጉሰ ነገስት ቴዎድሮስ በታላቅ ራዕይ ትሰባብረዋለህ፡፡ የታላቅ ህዝብ ልጅ መሆንህን ለቅጽበት አትርሳ፡፡

– በዚህ ዘመን ዉስጥ ቆመህ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ስለ መግንባት ራዕይህ አድርገህ ተነሳ እንጅ የዘመኑን መጨለም አይተህ አትርበትበት፡፡ ድል አንድ ነዉ፡፡ ሽንፈትም ገጽታዉ አንድ ነዉ::ትግል ስትገጥም ወይ ታሸንፋለህ፡፡ አለዚያም ትሸነፋለህ፡፡ ስለሆነም ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማለትም ሁሉም ዜጋ የሚስማማባትን: ሁሉም ማህበረሰብ የሚረካባትን: ብልጽግና እና ፍትህ የሚታወጅባትን: ወንድማማችነትንና ሰበአዊነት የሚሰፍንባትን ብሎም የሰዉ ልጅ የስልጣኔ አስተሳሰብ የገራቸዉ ታላላቅ ስነ መንግስታዊ መርሆዎች የሚተገበሩባትን ታላቅ ሀገር ለመመስራት ተነስ፡፡

ለዚህም በሚመጥን ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ አሳላጭ ስልት ተደራጅ፡፡ ራዕይ ገዳይ አደረጃጀቶችን መቀበል እነ አጼ ቴዎድሮስ የዘሩትን ኢትዮጵያዊ ራዕይ በወንዝ አጥር አጥሮ በግር መርገጥ ነዉና ቢያንስ ወደ ዘመነ መሳፍንት ጊዜ ከወረደ አደረጃጀት ዉጣ፡፡ የአደረጃጀት ዋናዉ ቁልፉ ምርጦቹን ለይቶ የአንድ ድርጅት ካድሬ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በማያወላዳ ቀንበር ስር ድርጅታዊ መርህን እንዲከተሉ ማድረግ መቻል ነዉ፡፡
 

%d bloggers like this: