አይይ! እማማ ኢትዮጵያ ምን ቀንና ማን እጅ ላይ ጣለሽ!                       ለኢትዮጵያ ትምህርት ውድቀት ተጠያቂ መሆን የሚገባው፣ አማሮችን በፊርማው ከጉራ ፈርዳ ያባረረው የትምህርት ሚ/ሩ በተልካሻ ፖለቲካ ምክንያት የሃዋሣ ዩኒቨርሲቲን ፕሬዚዳንት፣ ምሁርና ፕሮፌሰር ከሥራ አባረረ!

21 Sep

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በሪፖርተር: የትምህርት ሚኒስትሩ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትን አሰናበቱ
 

ለፕሬዚዳንቱ ስንብት ምክንያት የሆነው ወቅታዊው የመምህራን ስብሰባ ነው

የትምህርት ሚኒስቴሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲን በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩትን ፕሮፌሰር ዮሴፍ ማሞን፣ በመካሄድ ላይ ካለው የመምህራን ስብሰባ ዝግጅት ጋር በተያያዘ ከኃላፊነታቸው ማንሳታቸውን ተገለጸ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በመታገዳቸው ሳቢያ ዩኒቨርሲቲውን በዋና ፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ በማስተማር ላይ የሚገኙትን አቶ አያናው ባሪሶን መሾማቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ጣፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፕሮፌሰሩ በከፍተኛ ትምህርት ሕግ አዋጅ 650/200 መሠረት ከኃላፊነት ተነስተዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተማሪዎች መንግሥት ላዘጋጀው ሥልጠና ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በቅድመ ዝግጅት ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩን ሳያስፈቅዱ ወደ ውጭ አገር በመሄዳቸው የስንብቱ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፣ ሚኒስትሩ የስንብት ደብዳቤ እንደጻፉላቸው አረጋግጠዋል፡፡

ፕሮፌሰር ዮሴፍም የሚኒስትሩ የስንብት ደብዳቤ ካለፈው ሳምንት እንደደረሳቸው ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ ነገር ግን ለስንብታቸው ምክንያት ተብሎ በሚኒስትሩ ደብዳቤ የተገለጸላቸውን ግን አስተባብለዋል፡፡

‹‹ሳታስፈቅድ ወደ ውጭ አገር ሄደሃል የሚል በደብዳቤው ላይ ተጠቅሶ ተገልጾልኛል፡፡ እኔ ግን በቅድመ ዝግጅቱ ላይም ተገኝቼአለሁ፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ከራሳቸው ከአቶ ሽፈራው ሽጉጤም ሆነ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝቻለሁ፡፡ በእርግጥ ወደ ውጭ ልወጣ ካሰብኩበት ቀን ቀደም ብሎ ለሥራ ወደ መስክ ወጥቼ የነበረ በመሆኑ በስልኬ ላይ ልገኝ አልቻልኩም ነበር፤›› በማለት ለስንብት ያበቃቸው ጉዳይ በሚኒስትሩ ደብዳቤ የተገለጸው አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን የራሳቸውን ምላሽ ለሚኒስትሩ በጽሑፍ መላካቸውን የሚገልጹት ፕሮፌሰሩ፣ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል፡፡

ፕሮፌሰር ዮሴፍ ዩኒቨርሲቲውን ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በፕሬዚዳንትነት ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በኮንሰርቬሽን ባዮሎጂ የትምህርት መስክ ከእንግሊዝ አገር አቨርዲን ዩኒቨርሲቲ መያዛቸውን የግል ማኅደራቸው ያመለክታል፡፡ የእሳቸውንም ቦታ ተክተው እንዲሠሩ የተሰየሙት አቶ አያናው ባሪሶ በዩኒቨርሲቲው በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እዚያው እየሠሩ መሆኑን ሪፖርተር ከምንጮች ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ይህን ዓይነት ዕርምጃ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ሲወስዱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ኮሬን ማንሳታቸው አይዘነጋም፡፡
 

%d bloggers like this: