የጎንደር ቅዳሜ ገበያን በማቃጠል የተጠረጠሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ቢገለጽም፣ ባለንብረቶቹ ተጠርጣሪ የተባሉት እንዳልሆኑ ያሰማሉ፤ ማን ይሆን በእሳት መጫወት የሚወደው?

21 Sep

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በሪፖርተር
 

መስከረም 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡20 ሰዓት ላይ በጎንደር ከተማ መሀል አራዳ ክፍለ ከተማ፣ ቅዳሜ ገበያ በማቃጠል የተጠረጠሩ የጥበቃ ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ውለው እየተመረመሩ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ጉዳቱ የደረሰባቸው የንግድ ባለመደብሮች ግን፣ መደብሮቻቸው በጥበቃ ሠራተኞች ተቃጥለዋል የሚል እምነት እንደሌላቸው እየተናገሩ ነው፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምርያ አዛዥ ምክትል ኮማንደር አሰፋ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ ሌላ ማንም ተጠርጣሪ ስለሌለ ለጊዜው በወቅቱ የነበሩት የጥበቃ ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ውለው እየተመረመሩ ነው፡፡

የቃጠሎው መነሻ ምክንያት ታውቆ ከሆነ እንዲናገሩ የተጠየቁት ኃላፊው፣ ‹‹በእኛ በኩል ማረጋገጥ የቻልነው እሳቱ ከውስጥ የተነሳ መሆኑን ነው፤›› ብለዋል፡፡ በቃጠሎ የወደሙት ከ400 በላይ የአገር ልብስ፣ የብረታ ብረትና የቅመማ ቅመም መሸጫ መደብሮች ግምት እስካሁን አለመታወቁንም ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እያንዳንዱ ባለመደብር የነበረውን ግምት ባለማቅረቡ መሆኑን ምክትል ኮማንደሩ ገልጸዋል፡፡

በቃጠሎው የወደሙት የንግድ መደብሮች ፍርስራሽ በከተማ አስተዳደሩ ከፀዳ በኋላ አስተዳደሩ መደብሮቹን በዘመናዊ ሁኔታ ለመገንባት ሐሳብ ያቀረበ ቢሆንም፣ የመደብሮቹ ባለቤቶች አለመስማማታቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቦታው ላይ ጊዜያዊ የንግድ መደብሮችን በመሥራት ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

ለቃጠሎው ምክንያት ይሆናሉ በማለት በቁጥጥር ሥር ስለዋሉት የጥበቃ ሠራተኞች አስተያየታቸውን የሰጡት ባለመደብሮቹ፣ ከ50 ዓመታት በላይ የቆዩ የንግድ መደብሮች ጥበቃዎች አቃጥለውታል ወይም ለቃጠሎው ምክንያት ሊሆኑ ይችሉ የሚል ግምትም ሆነ ጥርጣሬ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ በእነሱ ግምት ጥፋተኛ ማን ሊሆን እንደሚችል ተጠይቀው ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
 

%d bloggers like this: