ከኢትዮጵያ ሶማሌ ግዛት እስከ መቀሌ፣ ከዚያም እስከ አዲስ አበባ ሰሞኑን የታየው የቡክኖች ዕብሪትና ዕብደት

29 Sep

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)
 

እስከዛሬ ጭብጡን በሚገባ መያዝ ያልቻልኩት፡ ሕወሃትና ቅጥፈትን ምን እንዲህ እንዳዛመዳቸው ነው! የየዕለቱን ፕሮፓጋንዳና ድርጊቶቹን ልብ ብሎ በግለስብ ደረጃም ሆነ በቡድን ላስተዋላቸው ሰው፣ ሕወሃት ውስጥ አንድም ለመሃላ እንኳ ሃቀኛ ሰው አለመኖሩ ተብሎ ያለቀለት ነገር ነው። ሌላው የሚያሳስበው ነገር ደግሞ ቅጥፈት እንደቂጥኝ ተላላፊ መሆኑ/መምስሉ ነው!

እስኪ ከጠቅላይ ሚኒስተር ተብየው ወደታች በካቢኔው በኩል አድርጋችሁ ቱባ የሚባሉትን የሕወሃት ያልሆኑትን ባለሥልጣኖች ታዘቧቸው። እነርሱም እንደ ሕወሃት ሰዎች ሁሉ እውነት የሚባል ነገር በአፋቸው አልነገርም ብላ እንቅራ የተፋቻቸው የቀጣፊዎች ክምችት ናቸው።

ያሳዝናል! አንድ ሃገር በቀጣፊዎች ተጠርንፋ ማዕበል ላይ እንዳለ መርከብ፣ በሕገ መንግሥት እየማሉ ከሕግ ውጭ በሚያስተዳድሯት መያዟ!

ሰሞኑን ልክ እንደ 1997 ከምርጫ ዘረፋውና ሕወሃት ኢትዮጵያውያኖችን በግፍ ከጨፈጨፈ በኋላ እንደነበረው ሁሉ፡ ሕወሃት መፈክር ሳይቀር በራሱ ካድሬዎች ለኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አስተዳደር ጽፎ በመሥጠት፡ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በማጋጨት የመተዳደሪያ እምነቱ፡ በኦጋዴን ሕወሃታዊ ሶማሌዎች ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ሲያሳጣና ሲያሰድብ መክረሙን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ እንዳለው ገምታለሁ።

የዚህም ዜና መስከረም 17 ቀን 2009 ፋና እንደዘገበው፣” የጅግጅጋና አከባቢዋ ነዋሪዎች ለህገ መንግሥቱና ለፌዴራል ሥርዓቱ ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት ዛሬ ሰልፍ አካሄዱ” ተብሎ ቀርቧል!

ሆኖም በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ የተቃጣው መሠረተ ቢስ ክስ፣ ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት ለመናድ ግንቦት ሰባትና ኦነግ ሕዝብ አነሳስተውብናል የሚል ነበር። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕወሃት ከማን ጋር ነው በሰላም ያለው? ከገበሬው፡ ክመምህራን፡ ከተማሪዎች፡ ከወጣቱና ከአብዛኛው የኅብረተስብ ጋር በመናከሱ፡ ምዕምናን ሳይቀሩ በድፍረት አገዛዙን በጣዕም ቋንቋ መታገል መጀመራቸውን፡ የ2008 መባቻና የ2009 አጀማመር አሳይቶናል! ይህ ብቸኝነቱ ይሆን፡ በኪሣራና በድለላ እየኖረ ቀኑን ከሚቆጥረው የሶማሌ ሕዝብ ጠላት ጉያ ሕወሃት መሸሸጊያ እንዲፈልግ ያደረገው?

በእሽክርናው በስም የኦጋዴን አስተዳዳሪ በተግባር ግን የአካባቢው የሕወሃት ወታደራዊ ባለሥልጣኖች አለቅላቂ የሆነው አብዲ መሀሙድ ባድረገው ንግግር፣ በክልሉ ነዋሪ የሆኑ አማሮችና ኦሮሞች በሠልፉ ላይ ተገኝተው በሕወሃት ላይ ክንዳቸውን ያነሱትን ግለስቦችና ቡድኖች ካላወገዙ ከሥራቸው መባረር፡ የንግድ ፈቃዳቸውን መነጠቅ ብቻ ሣይሆን ከክልሉ ይባረራሉ በማላት ለሁለት ቀናት ያህል ያናፋው አባባል፡ እንደ ሕወሃት ሁሉ ሕገ ወጥነቱን አሳይቷል።

ይህንን የሚፈጽሙ ናዚዎችና ፋሽስቶች ነበሩ፤ ዛሬ በሃገራችን ሥልጣንን ዘርፈው የያዙ ወገኖች ማድረግ የሚችሉት ሕጋዊን ተቀባይነት ያለው አስተዳደር መመሥረት ሳይሆን በኃይልና ብልጣብልጥነት ሲችሉ ረግጠው ለመግዛት አለያም ለከፋፍለህ ግዛው የሰሉ ግለሰቦች መጥፎና ጸረ-ሕዝብ ተግባር ላይ ተሠማርተው ርቃናቸውን ሲቀሩ እያየን ነው።፡ለዚህም የደነስቱ የሕወሃት ባለሥልጣኖችና በሕወሃት ዙሪያ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ናቸው!

ለነገሩ ከላይ እንዳመለከትኩት ሃገሪቱ በሕግ የማትተዳደር ሆና ነው እንጂ፡ በየትኛው አንቀጽ ነው የሕወሃት ሕገ መንግሥት ዜጎችን የማባረር ሥልጣን ለአብዲ መሀሙድ የሚሠጠው?

አንቀጽ 32 “(1) ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሃገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሃገሪቱ አካባቢ የመዘውዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት፡ እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሃገር የመውጣት ነጻነት አለው።”ይላል።

የሚያሳዝነው መንግሥት ነን በማለት በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች፡ ራሳቸው ሕጉን እየናዱ፡ እነረሱው ሕግ አስከባሪ ለመሆን መሞክራቸው ነው። የኢትዮጵያ ሶማሌዎች ከሁሉም በከፋ የግፍ አገዛዝ ሥር እየተረገጡ መሆናቸውን እንኳን እኛ ኢትዮጵያውያን ባዕዳን መንግሥታትም ያውቁታል። ስለሆነም፣ የኢትዮጵያውያን ቅሬታ መሆን ያለበት በራሱ የሕወሃት አሽከር በሆነው በክልሉ አስተዳዳሪ ነውና ዙርያውን በተኮለኮሉት በኮንትራባንድ ንግድ የሚተዳደሩትየሕወሃት ወታደራዊ መኮንኖች ነው!

በእርግጥ አሁን ያለው የሕወሃት አገዛዝ ሌቦችንና ቀጣፊዎችን ያነገሠ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ሥሩ እንደተላ ዛፍ ጤና መስሎ የቆመውን አስተዳደር ገፍትሮ ከመጣል ውጭ አማራጭ የሌለው መሆኑን ልብ ማለት አለበት!

የኃይለማርያም አስተዳደር እንኳ ለሌው ኢትዮጵያዊ ከለላ ሊሆን፡ ራሱንም አክብሮ አንገቱና ቀና አድርጎ የማይሄድ በመሆኑ፡ እርሱ ሕገ መንግሥቱን በማስከበር በሶማሌ ክልል ውስጥ ያሉትንና ሶማሌ ያልሆኑትን ዜጎች መብት ማስከበር ይቻል ብሎ የሚያስብ ኢትዮጵያዊ ዛሬ አለ ብዪ ለማመን እቸገራለሁ!

ራሱ ትግሬዎች አላግባብ ተፈናቅለዋልና እንድረስልህ የሚሉት ወገኖች፣ ሕወሃት የኢትዮጵያን ሕዝብ ጠብ ያለሽ በዳቦ ማለቱ መሆኑ ቢገባቸው፣ እዚህ አሳፋሪ ተግባር ውስጥ ባልተዘፈቁ ነበር!
 

%d bloggers like this: