በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፓስት የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ አፈፃፀም መመሪያ

16 Oct

የአዘጋጁ ትዕዝብት

  ሕጉ እንደ ደራሲዎቹ ሁሉ ፈላጭ ቆራጭ መሆኑ አያነጋግርም። በዚህ ትዕዝብታችን ትኩረታችን ግን በየዕለቱ ችግር ሲሰጠን ስለኖረው ስለየሆሄያት ወረራ ላይ ነው አስተያየታችን ያረፈው።

  ሥልጣኑን ለመጠበቅ የቋመጠ መንግሥት፣ የሕዝቡንም ሥልጣኔና ባሕላዊ ዕድገት ተገቢውን ትኩረት ሊሠጠው በተገባ ነበር። እዚህ አዋጅ ውስጥ የሕግ ባለሙያዎቹን አሰባስቦ በአማርኛ ጽሁፍ ላይ የአጥቂነት የሆሄያት ጭፈጨፋ ፈጽሟል።

  ወጣቱ ትውልድ የቀረበለትን ተቀብሎ በስህተተኛ መንገድ እየተመራ ነው። የአማርኛ ጽሁፍ የራሱ ባሕርያት አሉት። እኛ በልጅነታችን እየተቆነጠጥንም እንድናስተውለው ስለተደረግን ተምረነዋል። ወጣቱ ትውልድ ግን በአብዛኛው አማርኛውን የሚጽፈው ፊቱና አጠገቡ ባለው በትግሪኛ ሆሄያት ከሆነ ስንብቷል። በትግሪኛ ተናጋሪዎች በኩል እነአብርሃ ደስታ ሁሉ ተሳታፊ የሆኑበት የ ‘ቀ’ አማርኛ ተናጋሪዎች የሚጽፉትና ትግሪኛ ተናጋሪዎች ደግሞ የለም መቐለ ሲሉ የተከራከሩበትን እናስታውሳለን! ትክክል ናቸው በተለይም ስሞች እንደስምነታቸው መጻፍና መንገር አለባቸው – ይኸኛው የቋንቋ ስሙ እንጂ የየትም ስሙ ባለመሆኑ!

  ሊታሰብበት የሚገባ ችግር ነው፣ ዛሬ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ መነሳቱ ጽሑፉን ለማንበብ ያጋጠምን ችግር በርትቶብን ቢሆንም።

  ሆሄያት እንደ ሥዕል ይታያሉ፤ የአንባቢያንም ምቾት ያስፋፋሉ። ይህ ባይሆን ኖሮ አረብኛውንም ሆነ ሳንክሪስቱን በዘፈቀደ በየቀኑ በሰገሰግንበት ነበር!

  አሁን የመጣው ለውጥ ከትግርኛ የተወረሰ ነው። ለምን ትግራኛ የራሱን ሲጠብቅ አማርኛ ተናጋሪዎች – ብለውም ኢትዮጵያውያን – የራሳቸውን ያጠፋሉ፤ ለዚያውም ግዳጁ ሳይጀመር?

  መሆን ስላለባቸው ጥቂት ምሣሌዎች ለመጥቀስ ያህል፣ ‘ሕግ’፣ ‘ሕዝብ’፣ ‘ብሔራዊ’ና ‘ትምሕርት’ ወዘተ የሚጻፉት በሐመሩ ‘ሐ’ ነው።

  መንግሥት፣ ሥነ ሥርዓት የሚጻፋት እዚህ እንደተመለከተው ነው።

  ‘ና’የሚለው ተቀጽላ ማገናኛ ቢሆንም፣ አሁን አሁን እንደ ትግሪኛ ሁሉ ‘እና’ እየተባለ ይጻፋል። ይህም ስህተት ነው።’እና’ ራሱን ችሎ ሊገባ የሚያስገድድ ሁኔታም አለ – የውጭ ስሞች ወይንም ምህጻረ ቃላት ስንጠቀም ነው።

  መሬቱን ለመጠበቅ ሕዝብ፡ ቁርጠኛ ትግል የሚያካሄድ አዕምሮአዊ ሃብቱንም መንከባከብና ማዳበር የራሱ ብሔራዊ ግዴታ ነው።

  ለዛሬው የሕወሃት አሰተዳደርና የሕግ ባለሙያዎቹ የሠጡንን ራስ ምታት ለዘለቄታው ለመፈወስ አመለካከታችንን እዚህ ላይ እንገታለን።

 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ለማስከበርና የህዝብና የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የደነገገ ሲሆን በቅርቡ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተስተዋለውን የጸጥታ መደፍረስ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር አድርጎ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ወደ ነበረበት ለመመለስ በየቦታው ለታየው ሁከት፣ ረብሻና ስርአት አልበኝነት ዋንኛ መገለጫ በሆኑ አውዳሚ ተግባራት ላይ የተጣለውን ክልከላ እንዲሁም ክልከላዎቹ ሲጣሱ በአዋጁ መሰረት የሚወስዱ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን በመለየት አስቀድሞ ለህዝብ ማሳወቅ እንዲሁም አዋጁ ተፈፃሚ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ክልከላዎቹን ጥሰው በሚገኙ ሰዎችና ድርጅቶች ላይ ተገቢውን የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ሆኖ ስለተገኘ የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር—መስከረም 28/2009 አንቀፅ 13/2/ እና በደንቡ አንቀፅ 4 በተፈቀደው መሰረት የሚከተለው መመሪያ ወጥቷል።

ክፍል አንድ

የተከለከሉ ተግባራት

ንዑስ ክፍል አንድ

በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች የተከለከሉ ተግባራት

አንቀፅ 1. ሁከትና ብጥብጥ የሚያስነሳ ቅስቀሳና ግንኙነት ማድረግ ማንኛውም ሁከት፣ ብጥብጥና በህዝቦች መካከል መጠራጠርና መቃቃር የሚፈጥር፣ ይፋዊም ሆነ ድብቅ ቅስቀሳ በማናቸውም መልኩና ዘዴ ማድረግ፣ ፅሁፍ ማዘጋጀት፣ ማተምና ማሰራጨት፣ ትእይንት ማሳየት፣ በምልክት መግለፅ ወይም መልእክትን በማናቸውም ሌላ መንገድ ለህዝብ ይፋ ማድረግ፣


አንቀፅ 2. ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ማድረግ

በሽብር ከተሰየሙ ድርጅቶች እና ከፀረ ሰላም ቡድኖች ጋር ማናቸውንም ግንኙነት ማድረግ፣

የአሽባሪ ድርጅቶችን የተለያዩ ፅሁፎች መያዝ ማሰራጨት፣ አርማቸውን መያዝ ወይም ማስተዋወቅ፣

የቴሌቪዥን ወይም የሬድዮ ፕሮግራምን መከታተል፣ የኢሳት፣ የኦ.ኤም.ኤን. እና የመሳሰሉትን የሽብርተኛ ድርጅቶች ሚዲያዎችን ማሳየት፣ መከታተልና ሪፖርት ማድረግ የተከለከለ ነው።

አንቀፅ 3. ያልተፈቀደ ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ

የህዝብና የዜጎች ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል ከኮማንድ ፓስቱ ፈቃድ ውጭ ማናቸውም ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ ማድረግ የተከለከለ ነው።


አንቀፅ 4. ለህዝብ አገልግሎት አለመስጠት

  (1) ህዝብ የሚጠቀምባቸውን ወይም ፈቃድ የወጣባቸው የንግድ ስራዎች፣ ሱቆች ወይም የመንግስት ተቋማት መዝጋት ወይም ምርትና አገልግሎት ማቋረጥ፣ ከስራ ቦታ ያለ በቂ ምክንያት መጥፋት ወይም ስራ ማቆም፣ ተገቢውን አገልግሎት አለመስጠት፣ ስራን መበደል፣

  (2) የመንግስት ወይም የግል ተቋማት ሰራተኞች ወደ መደበኛ ስራቸው እንዳይገቡ መዛትና ማስፈራራት የተከለከለ ነው።

አንቀፅ 5. በትምህርት ተቋማት አድማ ማድረግ

በትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርስቲዎች እና በሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደትን የሚያውክ አድማ ማድረግ፣ የትምህርት ተቋማትን መዝጋት ወይም በነዚህ ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረግ የተከለከለ ነው።

አንቀፅ 6. በስፖርት ማዘውተሪያዎች አድማ ማድረግ

በስፖርት ማዘውተሪያ ማእከላት ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ የሆኑ ሁከቶችን፣ ብጥብጦችን መፍጠር የተከለከለ ነው።

አንቀፅ 7. የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ማወክ

የተሽከርካሪ፣ የእግረኛ እና ሌሎች የመጓጓዣ ዘዴዎችን እንቅስቃሴ መንገድ በመዝጋት በዛቻ እና በሌሎች መሰል ድርጊቶች ሰላማዊ እንቅሰቃሴን ማወክ፣ አገልግሎት ማስተጓጎል፣ የመጓጓዣ ዋጋ ታሪፍ መጨመር፣ የሚመለከተው አካል ከደለደለው የስራ ስምሪት ውጪ መሆን የተከለከለ ነው።

አንቀፅ 8.በመሰረተ ልማቶችና ሃይማኖታዊ ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረስ

በግል፣ በህዝብና በመንግስት ማናቸውም ተቋማት፣ በመሰረተ ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች የልማት አውታሮች እንዲሁም በሃይማኖታዊ ተቋማት ላይ በማንኛውም መንገድ ጉዳት ማድረስ ወይም ዘረፋ መፈፀም የተከለከለ ነው።

አንቀፅ 9. ህዝባዊና ብሄራዊ በዓላትን ማወክ

ህዝባዊና ብሄራዊ በዓላትን በማንኛውም ሁኔታ ማወክ፣ ማደናቀፍ ወይም ከበዓሉ አላማ ጋር የማይገናኙ የፖለቲካ አጀንዳዎች ወይም መፈክሮችን በማንኛውም መንገድ ማስተጋባት የተከለከለ ነው።

አንቀፅ 10. ሀይማኖታዊ፣ ባህላዊና ህዝባዊ በዓላት ላይ ቅስቀሳ ማድረግ

ሀይማኖታዊ ተቋማት ውስጥ በሚደረጉ ስብከቶችና ትምህርቶች ሀይማኖታዊ አስተምህሮት ከማድረግ ውጪ በህዝቦች መካከል መጠራጠርና መቃቃርን የሚፈጥር፣ በህብረተሰቡ ላይ ስጋት የሚፈጥር፣ ሁከትና ብጥብጥ የሚቀሰቅስ ቅስቀሳ ማድረግ የተከለከለ ነው።

አንቀፅ 11. የህግ አስከባሪዎችን ስራ ማወክ

የህግ አስከባሪ አካላት የሚሰጡትን ማንኛውም ትዕዛዝ አለማክበር ስራቸውን ማደናቀፍ፣ ለፍተሻ አለመተባበር ወይም እንዲቆም ሲጠየቅ አለማቆም፣ ኬላዎችን ጥሶ ማለፍ የተከለከለ ነው፣

በህግ አስከባሪ አካላት ባልደረቦች ላይ ጥቃት መፈፀም ወይም ለመፈፀም መሞከር የተከለከለ ነው፣

አንቀፅ 12. ያተፈቀደ አልባሳት መልበስ

የህግ አስከባሪ ሃይሎችን ዩኒፎርም መልበስ፣ ይዞ መገኘት፣ በቤት ማስቀመጥ፣ አሳልፎ መስጠትና መሸጥ ክልክል ነው።

አንቀፅ 13. የጦር መሳሪያ ይዞ መግባት

ማናቸውም የጦር መሳሪያ፣ ስለት ወይም እሳት የሚያስነሱ ነገሮችን ወደ ገበያ፣ ሀይማኖት ተቋማት፣ ህዝባዊ በአላት የሚከበሩበት ወይም ወደ ማናቸውም ህዝብ የሚሰበሰብበት ቦታ ይዞ መግባት የተከለከለ ነው።

አንቀፅ 14. ትጥቅን በሶስተኛ ሰው እጅ እንዲገባ ማድረግ

ማንኛውም የህግ አስከባሪ አካላት ባልደረባ ወይም ማንኛውም ህጋዊ ትጥቅ ያለው ሰው ትጥቁን በማንኛውም ሁኔታ በሶስተኛ ሰው እጅ እንዲገባ ማድረግ ክልክል ነው።

አንቀፅ 15. መቻቻልን እና አንድነትን የሚጎዳ ተግባር መፈፀም

ማንነትን ወይም ዘርን መሰረት ያደረገ ማንኛውም አይነት ጥቃት መፈፀም ወይም ጥቃት እንዲፈፀም የሚያነሳሳ ንግግር መናገር የተከለከለ ነው።

አንቀፅ 16. የሀገርን ሉዓላዊነት፣ ደህንነት፣ ህገመንግስታዊ ስርዓት የሚጎዳ ተግባር መፈፀም

ማንኛውም ሰው ከውጭ መንግስታትም ሆነ ከውጭ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር የሀገር ሉአላዊነት፣ ደህንነትና ህገ-መንግስታዊ ስርዓትን ሊጎዳ የሚችል ግንኙነትና የመልዕክት ልውውጥ ማድረግ የተከለከለ ነው፣
ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የሀገርን ዑአላዊነት፣ ደህንነት እና ህገመንግስታዊ ሥርዓቱን ማናቸውም ጋዜጣዊ መግለጫ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ሚዲያዎች መስጠት ክልክል ነው።

አንቀፅ 17. ያልተፈቀደ ቦታ መገኘት

ከስደተኛ ካምፕ አግባብ ካለው አካል ከሚሰጥ ፈቃድ ውጭ መውጣት ወይም ህጋዊ ቪዛ ሳይኖረው ወደ ሀገር ውስጥ መግባት የተከለከለ ነው።

አንቀፅ 18. ያለፈቃድ ስለሚደረግ የዲፕሎማቶች እንቅስቃሴ

የኮማንድ ፖስቱ እውቅናና ፈቃድ ሳያገኙ ዲፕሎማቶች ለራሳቸው ደህንነት ጥበቃ ሲባል ከአዲስ አበባ ከአርባ /40/ ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውጪ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።

አንቀፅ 19. የህግ አስከባሪ አካላት ግዳጅ ላይ ስለመገኘት

ማንኛውም የህግ አስከባሪ አካል ባልደረባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈፃሚ በሚሆንበት ጊዜ ከስራ መልቀቅ ወይም አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር የአመት እረፍት ፍቃድ መውሰድ ክልክል ነው።

አንቀፅ 20. የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማደፍረስ ድጋፍ ማድረግ

በዚህ መመሪያ የተከለከሉ ተግባራትን በመተላለፍ ህገወጥ ድርጊት የሚፈፅሙ ሰዎችን፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ መደገፍ እንዲሁም ከለላ መስጠት፣ መደለያ መስጠት፣ ማበረታታት የተከለከለ ነው።

ንዑስ ክፍል ሁለት

በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዳይፈፀሙ የተከለከለ ተግባራት

ከላይ በንዑስ ክፍል አንድ የተደነገነገው እንደተጠበቀ ሆኖ ከአንቀፅ 21-24 የተዘረዘሩት ክልከላዎች ኮማንድ ፖስቱ እየወሰነ ይፋ በሚያደረጋቸው ቦታዎች ወይም አካባቢዎች ላይ ተፈፃሚ ይሆናሉ።

አንቀፅ 21. የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ

ማናቸውም የጦር መሳሪያ፣ ስለት ወይም እሳት የሚያስነሱ ነገሮችን ከግቢውና ይዞታው ውጪ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው።

አንቀፅ 22. በልማት አውታሮችና መሰረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘር ጥቃት

የኢኮኖሚ አውታሮች፣ መሰረት ልማትና የኢንቨስትመንት ተቋማት፣ የእርሻ ልማቶች፣ በፋብሪካዎች እና በመሰል ተቋማት አካባቢ ከቀኑ 12 ሰዓት በኋላ እስከ ንጋት 12 ሰአት ድረስ ከተፈቀደለት ሰራተኛ በስተቀር ማንኛውም ሌላ ሰው መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፣

ከላይ በተመለከቱት ቦታዎች የሰዓት እላፊውን ተላልፎ በተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ የጥበቃ ውይንም የህግ አስከባሪ አካላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል።

ክፍል ሁለት

የተከለከሉ ተግባራት ተፈጽሞ ሲገኝ ስለሚወሰዱ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎች

አንቀጽ 27. እርምጃ ለመውሰድ ስልጣን ስላለው ሰው

ከላይ በክፍል አንድ ከአንቀጽ 1-24 የተመለከቱ የተከለከሉ ተግባራትን ፈጽመው በተገኙ ሰዎችና ድርጅቶች ላይ የህግ አስከባሪዎች እና ባልደረቦቻቸው በአዋጁና በዚህ መመሪያ የተዘረዘሩ የሚከተሉትን የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይችላሉ፡፡

አንቀጽ 28. ክልከላዎች ሲጣሱ ስለሚወሰዱ እርምጃዎች

ከላይ በክፍል አንድ የተመለከቱ ክልከላዎችን ተላልፈው በተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ የህግ አስከባሪዎች ፣

  (1) ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር ማዋል፣

  (2) አዋጁ ተፈጻሚነቱ እስከሚያበቃበት ጊዜ ድረስ ኮማንድ ፖስቱ በሚወስነው ቦታ እንዲቆይ ማድረግ፣

  (3)ተገቢውን የተሃድሶ ትምህርት በመስጠት የሚለቀቀውን እንዲለቀቅ ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርበውን ደግሞ እንዲቀርብ ማድረግ፣

  (4) ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማናቸውም ሰዓት ብርበራ ለማድረግ የአካባቢውን ህዝብና ፖሊስ በማሳተፍ ማንኛውንም ወንጀል የተፈጸመበት ወይም ሊፈጸምበት የሚችል ንብረት መያዝ ወይም ንብረቱ ባለበት እንዲጠበቅ ማድረግ፣

  (5) በማንኛውም ሬድዮ ፡ ቴሌቪዥን ፡ ጽሁፍ ፡ ምስል ፡ ፎቶ ግራፍ ፡ ቲያትርና ፊልም የሚተላለፉ መልዕክቶችን መቆጣጠርና መገደብ፣

  (6)የተዘረፉ ንብረቶችን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመፈተሽ ለባለቤቶቹ እንዲመለሱ ማድረግ፣

  (7) በትምህርት ተቋማት ሁከትና ረብሻ ተሳትፎ በሚያደርጉ ተማሪዎችና ሰራተኞች ላይ ህጋዊ እርምት መውሰድ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ለተቋማቱ ትዕዛዝ መስጠት፣

  (8)ማንኛውም የህዝብን ሰላምና ጸጥታን ሊያደፈርሱ ይችላሉ ወይም ለጉዳት ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው የሚጠረጠሩና የሚታሰቡ ሰዎችን ወይም ቡድኖችን ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ እንዳይገኙ ወይም በተወሰነ አካባቢ ብቻ እንዲቆዩ ማድረግ እና

  (9) አግባብነት ያላቸውን እርምጃዎችን መውሰድ ይችላል፡፡

አንቀጽ.23. ስለ ሰዓት እላፊ

ማናቸውም ሰው በኮማንድ ፖስቱ ውሳኔ የሰዓት እላፊ በይፋ በሚገለጽበት ቦታና ጊዜ የሰዓት እላፊ ክልከላን በመተላለፍ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ አይፈቀድም፡፡

አንቀጽ 24. ሁከትን ለማስቆምና አደጋን ለመከላከል የሚደረግን እንቅስቃሴ ማወክ

ሰላምና ፀጥታን ሊያደፈርሱ ይችላሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች ወይም ቡድኖችን ወይም ለጉዳት ተጋላጭ ናቸው ተብለው የሚገመቱ ሰዎች ወይም ቡድኖች ወደ ተወሰነ አካባቢ ወይም ህንፃ እንዳይገቡ ወይም በተፈቀደላቸው አንድ የተወሰነ አካባቢ ብቻ እንዲቆዩ የተሰጠውን ትዕዛዝ መተላለፍ ክልክል ነው፡፡

ለአካባቢው ደህንነት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ወደ ተዘጋ መንገድ ማንም ሰው እንዳይገባ ኮማንድ ፖስቱ የሰጠውን እግድ ወይም ክልከላ መተላለፍ ክልክል ነው፡፡

ንዑስ ክፍል ሶስት

መረጃ የመስጠትና የማስታወቅ ግዴታ

አንቀጽ 25. የተከራይ መረጃ የመያዝና የመስጠት ግዴታ

ማንኛውም ቤት፡ ቦታ፡ ክፍል ወይም ተሽከርካሪ ወይም ተመሳሳይ መገልገያ አከራይ የሆነ ሰው የተከራዩን ማንነት በዝርዝርና በጹሁፍ የመያዝና በአቅራቢያው ላለ ፖሊስ ጣቢያ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡ በተጨማሪም የውጭ አገር ዜጋን ያከራየ እንደሆነ የፓስፖርቱን ኮፒና የኪራዩን ውል በአቅራቢያው ላለ ፖሊስ ጣቢያ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡

አንቀጽ 26. መረጃ የመስጠት ግዴታ

የህዝብ ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል ማንኛውም ተቋም መረጃ እንዲሰጥ በየደረጃው ባለ የህግ አስከባሪ አካል ሲጠየቅ የመስጠትና የመተባበር ግዴታ አለበት።

አንቀጽ 29. እራስን ለመከላከል በሕግ አስከባሪዎች ስለሚወሰድ እርምጃ

ሕግ አስከባሪዎችናቀ በድርጅቶች ጥበቃ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ከላይ የተመለከቱትን ክልከላዎች እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በጦር መሳሪያ ወይም በስለትና ሕይወታቸውን እና ንብረታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ጥቃት በተሰነዘረባቸው ጊዜ እራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችላቸውን እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡

አንቀጽ 30. በትምህርት ተቋማት የመግባት ስልጣን

በትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርስቲዎች እና በሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ አድማ የሚያደርጉ ሰዎችን ለመያዝና ችግሩን ለማስቆም የህግ አስከባሪ አካላት በእነዚህ ተቋማት ውስጥ በመግባት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ይችላሉ፣ እንዲሁም በሌሎች የግልና የመንግስት ተቋማት ውስጥ አድማ የሚያድርጉ ሰዎችን ለመያዝና ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ የሕግ አስከባሪ አካላት ባልደረቦች በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ለመግባት እንዲሁም አስፈላጊ ከሆነ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡

ክፍል ሶስት

ተሀድሶ እና ፍርድ ቤት ስለማቅረብ

አንቀጽ 31. በሕግ መሰረት በኮማንድ ፖስቱ የሚደረግ የተሀድሶ እርምጃዎች

  (1) ለፍርድ መቅረብ ያለበትን ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ያደርጋል

  (2)ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በተፈጸሙ ሁከትና የብጥብጥ እንቅስቃሴዎች ላይ በቡድን ወይም በግል የተሳተፈ እና

  (ሀ) የጦር መሳሪያ ወይም ማንኛውንም የግልም ሆነ የመንግስት ንብረት የዘረፈ እና በአቅራቢያው ለሚገኝ የህግ አስከባሪ ሀይል የዘረፈውን መሳሪያና ንብረት ይህ መመሪያ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ በ10 ቀናት ውስጥ በአቅራቢያው ላለ ፖሊስ ጣቢያ የመለሰና እጁን የሰጠ ሰው፣

  (ለ) ከዚህ በፊት ለህገወጥ ተግባራት የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረገና ይህ መመሪያ በወጣ በ10 ቀናት ውስጥ ለፖሊስ ጣቢያ እጁን የሰጠ ሰው፣

  (ሐ) ወረቀት በመበተን ፣ አድማ በማድረግ የተሳተፈ፣ ያነሳሳ ሰው ይህ መመሪያ በወጣ 10 ቀናት ውስጥ ለፖሊስ ጣቢያ እጁን የሰጠ ሰው፣

  (መ) ሰው የገደለ፣ ማንኛውንም ንብረት ያቃጠለ፣ ማንኛውንም ወንጀል የፈጸመ ይህ መመሪያ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በ10 ቀናት ውስጥ ለፖሊስ ጣቢያ እጁን የሰጠ ሰው፣ እንደ የወንጀል ተሳትፎው ቀላልና ከባድነት፣ ዋና ፈፃሚና አባሪ ተባባሪ መሆኑ ታይቶ በኮማንድ ፖስቱ የተሀድሶ ትምህርት ተሰጥቶት እንዲለቀቅ ይደረጋል፡፡

አዲስ አበባ ጥቅምት 5 ቀን 2009 ዓ/ም
 

ተዛማጅ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ አፈፃጸም መመሪያ ይፋ ሆነ
 

%d bloggers like this: