‘ለወያኔ እድሜ ማራዘሚያ በተዘጋጀ መድረክ ተቀዋሚዎች ምን ይሰራሉ?’ የሚለው የአቶ ይገረም ዓለሙ ጥብቅና አልተመቸኝም!

24 Oct

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)
 

ከላይ በተጠቀስው ርዕስ ጥቅምት 23 ቀን 2016 አቶ ይገረም ዓለሙ በኢትዮሚዲያ ፎረም ላይ ፋና ብሮድካስት በአዲስ አበባ ስላዘጋጀው ስብሰባ የፖለቲካውን ጽዩፍነታቸውን የዘገቡበት ጽሁፍ ስላልተመቸኝ፣ ስለፖለቲካችን አያያዝና ሂደት ትንሽ እንዳስብ አድርገውኛልና ከልብ አመስግናቸዋለሁ።

ከመነሻው ስንደረደር እንዲታወቅ የምሻው፣ በመደምደሚያቸው ጭምር የተመለከተውን የሚከተለውን የጸሐፊውን ሥጋት በሚገባ ግንዛቤ ውስጥ አስገብቻለሁ፦

“ወያኔ የሥልጣን እድሜውን ለማራዘም ይጠቅማል እስካለ ድረስ [ወደ] መድረክ መጋበዝ አይደለም ትንሽ ትንሽ ሥልጣን እስከመስጠት ሊሄድ ይችላል። በዚህ ወቅት እየተንገዳገደ ያለውን ወያኔ ተጋግዞ ከመግፋት ይልቅ በየግል ፍላጎት ምክንያት በወያኔ ድርጊት እየተታለሉም ሆነ እየማለሉ ጥያቄውን በመመለስም ሆነ ስጦታውን በመቀበል ምርኩዝ መሆን የኢትዮጵያ ህዝብ በባርነት አንዲኖር ተባባሪ መሆን ነውና ያስጠይቃል።”

በእኔ ዕይታ ግን – ጸሐፊው እንደሚሉት ሳይሆን – ወያኔ የማስታወስ፣ የፖለቲካና የፖሊሲ ጉዳዮችን በሚገባ በማቀነባበር ኅብረተሰብ የመምራት ችሎታው ዝቅተኛ መሆኑን በአገዛዝ ዘመኑ ግልጥ አድርጎ አሳይቶናል። ይህም ማለት ከዕለታዊ ጥቅሙ ውጭ ወያኔ ሥልጣን ለክቶ እንኳ የመስጠት ችሎታ ነበረው አለው ለማለት የሚያስችል ነገር አላየንም። ያ ቢሆነ፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዛሬ ካለበት የአንድ ወገን የበላይነት ጫናና በሰብዓዊ ክብር ገፈፋ ምክንያት አብዛኞች ዜጎቻችን ወደ ባርነት መውረድና ወገኖቻችን ሙሰኞችና ጥጋበኞች በሚያደርሱባቸው ሰለባዎች ምክንያት መጎሳቆላቸውን ባላየን ነበር።

ይህንንም ስል፣ ትንሽ ትንሽ ሥልጣን እንደ ለውሻ አጥንት መወርወሩን መዘንጋቴን ለማሳየት አይደለም። ለቅጥረኞቹ ፍላጎቱን የሚያረኩለትን የሥልጣን አምሳያ መውርወሩን አልዘነጋሁም! ለዚህም ተግባሩ ወዶ ተቀጣሪዎችን ይመለምላል። መልምሏልም! በሌላ አባባል፣ ወያኔ ተመቻችቶ ለመግዛት ሲጥር የነበረውና – ባይሳካለትም – እየጣረ ያለው ያለውን የሰውና የመሣሪያ ኃይል በመጠቀምና በማጭበርበር ነው።

በኢትዮጵያውያን በኩል፡ በጥብቅ ማስታወስ ከሚገቡን መካከል፡ በቅርቡ ቦሌ ወረገኑላፍቶጋምቤላአርባ ምንጭ ኮንሶቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ወዘተን አስታውሱ! ሕወሃት የመሬት ዘረፋው፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር እነኮለኔል ይህደጎ ሥዩምና ተባባሪ ካድሬዎቻቸው ይህንን ለማስፈጸም አሮጊት ሽማግሌ የረጋገጡበት፡ ሕጻናት በንጋት እምባ የረጩባት፡ ሕሙማን መሬት ለመሬት የተጎተቱባትና ሰዎች ተደብድበው ሕይወት ያለፉባቸው ሁኔታዎች የሥቃይ ክምችት ለዛሬው የአልገዛም ባይነት ትንቅንቅ ሃገራችንን ባላደረሳት ነበር።

ከብዙ በጥቂቱ በእነዚህም ምክንያቶች ነው ባመቸው መንገድ ሁሉ እኩይ ተግባሩን ማጋለጥ የሚያስፈልገው! ለዚህም የተገኘውን መድረክ ሁሉ መጠቀም ያስፈልጋል። ያንንም የምናይበት መንገድ፣ ጠላት ካምፕ ውስጥ ገብቶ ፈንጅ ከሚወረውር ወታደር ባልተለየ መልኩ መሆን ይኖርበታል።

የሃገራችን ከፍተኛ የሚዲያ ባለሥልጣኖች የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማኅበር ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ከበደ; በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ፋካልቲ መምህር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮና የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ ሚ/ ዴኤታ አቶ ጌታቸው ረዳ (ፎቶ ኢብኮ)

የሃገራችን ከፍተኛ የሚዲያ ባለሥልጣኖች የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማኅበር ም/ሥራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ከበደ; በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ፋካልቲ መምህር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮና የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ ሚ/ ዴኤታ አቶ ጌታቸው ረዳ (ፎቶ ኢብኮ)

ወደኋላ መለስ ብለን ብንመለከትም፣ ከ25 ዓመታቱ ጸረ ሕዝብ የሸፍጥ፣ የዘረኝነት፣ የእሥራት፣ የረገጣ፣ የገደላና የዘረፋ አገዛዝ በኋላ ለአቶ ይገረም ዓለሙ ቁጣ ምን ምክንያት እንደሆናቸው የወያኔን ከንቱ ዓላማ ኢትዮጵያዊ ቀርቶ – ከሰሞኑ እንደምመለከተው ከሆነ – ባዕዳንም አልሳቱትም።

ቢቢሲሲ.ኤን. ኤን. The Indian Oceannewsletter, The Washington Post፣ ወዘተ እንኳ ስድስት ከመቶ የማይሞሉት ትግራዉያን የቀረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ረግጠው መያዛቸው ምን ያህል የችግሩ ምንጭ መሆኑን ሲተርኩ መስማቱ ምን ያህል አመለካከትና ጊዜው እንደተለወጠ ገላጭ ለመሆኑ ሌላ ምስክርነት አያሻም።

የሕወሃት ሰዎችም ነፍስ ውጭ ደረጃ ላይ በመሆናቸው፡ ካድሬያቸው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን የጎንደር ሕዝብ በአጋዚ ላይ እጁን እንዳያነሳ መገዘታቸው እንዴት ይዘነጋል፣ እንኳን ፋና ብሮድካስትን በመጠቀም በዴሞክራሲ አማኞች ይመስል፡ እንነጋገር ቢሉ እምብዛም ሊያስገርም አይገባም!

ሌላው ቀርቶ ሰበታ ካላት 73 ሺ ሕዝብ ውስጥ አይደል እንዴ አንድ ሺ ተጠርጣሪዎች ያዝን ብለው ወጣቱንና ዐይነ ቀለሙ ያላማራቸውን በጥቂት ሰዓታት ያፈኑት። ያን ባደረጉ በጥቂት ቀናት ውስጥ አይደል እንዴ “በሰበታ ከተማ ሕዝባዊ የሰላም ጉባዔ ተካሂዶ መሰል ሁከትና ግርግር ዳግም እንዳይከሰት የከተማ አስተዳደሩና የከተማዋ ነዋሪዎች በጋራ መስራት ባለባቸው ጉዳይ ላይ ምክክር አደረጉ” የሚል ዜና ፋና የለጠፈው።

በዘራቸው የተመረጡት ካድሬው ፓትሪያርክ ለኢትዮጵያውያን መጨፍጨፍ ግድ ሳይኖራቸው አይደል እንዴ ሕወሃት እንዳይገለበጥ የጎንደር ሕዝብ አመጹ እንደተፋፋመ እጁን በሠራዊቱ ላይ ቢያነሳ እንደሚያወግዙት የተናገሩት?
=============
 

ይህንን ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ ካስገባን በኋላ፡ ፋና ስላዘጋጀው ስብሰባ ዓላማው ከላይ የተጠቀሱት ጋር ተመሳሳይ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር አልነበረኝም። እንዲያውም የዚያ ዐይነት ስብሰባ በፋና አዘጋጅነት መካሄዱ ብቻ ሳይሆን፣ የመደረክ አስተናባሪ ሆኖ የተኮፈሰው ብሩክ ከበደ፣ የፋና ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ በአዲስ አበባ መሬት ዘመቻ ዘረፋ ግንባር ቀደም ተዋናይ (lead political operative) መሆኑን በሚገባ ስለማስታውስ፣ የጸሐፊውን የቁጣ ስሜት መንስዔ ብገነዘብም፣ የሰሞኑ ስብሰባ ላይ የተቃዋሚዎችን መገኘንትን መኮነናቸውን ግን አልጋራም።

ከሁሉም የከፋ ደግሞ በዚህ ሚናው የተዘረፈውን መሬት የሕወሃት ሰዎች በካዳስተር አስመዝግበው ሕጋዊ ለማስደረግ ብሩክ በፋና አማክይነት ተመሳሳይ የፋና ጉባዔ ከኢትዮጵያ የመረጃና ስለላ ድርጅት (INSA) ተወካይ፣ ከቤቶችና ከተማ ሚኒስትሩ መኩሪያ ኃይሌ (አንደ አንደተመጠጠ ሎሚ በቅርቡ ወያኔ የተፋው) አማካሪ ይትባረክ መንግሥቴ ጋር ማካሄዳቸውን መዘገቤንና እንዲሁም መተቸቴትን አስታውሳለሁ።

በዚያ ስብሰባ ላይ አቶ ብሩክ ከበደ “ተፅዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ ለመገንባት ያሉ ዕድሎች፣ ፈተናዎችና መፍትሔዎቻቸው” በሚል ር ዕስ ባቀረበው ‘ጥናታዊ ‘ ጽሁፍ የመንግሥት አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው፣ የኅብረተሰቡና የመገናኛ ብዙኃን ክትትል ወሳኝ መሆኑን አስረድቶ፣ መንግሥት የመረጃ ነፃነትን በሁሉም ዘርፎች ማረጋገጥ፣ የሚዲያ ተቋማትን እንደ ሁነኛ የሕዝብ ድምፅ ማዳመጫ፣ መከታተያና መገንዘቢያ በመውሰድ መደበኛ መከታተያና ማስፈጸሚያ ሥርዓት መዘርጋት ይኖርበታል ብሏል። የዚህ ሁሉ ሾኬ ዓላማ፣ የተዘረፉትን መሬቶ ሕጋዊ ለማስደረግ የተካሄደ ቅስቀሳ ነበር። ለነገሩ ሁሉም የሕወሃት ባለሥልጣኖች የምፈልጉት በመሆኑ ነው በሣምንታት ውስጥ የካዳስተር ድንጋጌው የወጣው!

ስለሆነም፣ እነዚህን ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ በማሰገባት፡ በቅርቡ የተካሄደው የፋና ስብሰባ ከመጀመሩ በፊትና እየተካሄደ እያለ እኔም ትዕዝብቴን እንደሚከተለው በትዊተር ገልጨ ነበር፦

 

ፋና እንደ ሕወሃት ጉዳይ ማስፈጸሚያ መሣሪያነቱ የካዳስተር ደንቡ በአዲስ አበባ ከተማ እንደወጣ። በጨረታ አዲስ አበባ ውስጥ የተሸጠው መሬት – በወቅቱ ባደረኩት ስሌት መሠረት – የመሬት ዋጋ በዚያን ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ ከስቶኮልምና ቶኪዮ በላይ ንሮ ነበር። ሕወሃት ስግብግብ በመሆኑ፣ እነብሩክ ዐይነቶችን ጥቅም አደሮች ተጠቅሞ ይህንን ሲፈጽም፡ ያልተገነዘበው ነገር ቢኖር፡ መሬት የኤኮኖሚው ዕምብርትና ሞተር በሆነባት ሃገር፡ ያንን ዐይነት የመሬት ዘረፋና ችርቻሮ በማካሄድ፡ ኤኮኖሚውን የመግደል ሥራ ነበር (ነውም) ያካሄዱት!
==============
 

ታዲያ ዛሬ እነብሩክ ከበደ ያካሄዱት፣ አቶ ወልዱ ይምሰል (ጥሩ ስም)፣ የፋና ዋና ሥራ አስኪያጅና አባ ዱላ ገመዳ ባርከው ለተሳታፊዎች ያስተላለፉት ስብሰባ አንዳችም እንደሚፈይድ ሕወሃት ይህንን አለመገንዘቡ ይበልጥ አስገርሞኛል። የሚያስገርመው ነገር በየክልል ሁሉ ተመሳሳይ ስብሰባዎች ለማካሄድ ለማድረግ ዝግጅት እንዳላቸው ቀድም ሲል አስታውቀዋል።

የዚህም ዋና ዓላማ፣ መድረኩ ላይ እነብሩክ እንደተነፈሱት፣ በነጻ ንግግርና ዲሞክራሲ ስም ሕዝቡ እነዚህን በማዳመጥ ቋጣውን ለማስተንፈስ ሕወሃት ከሚያደርጓጋቸው ጥረቶች አንዱ ነው።

ስለሆነም ተቃዋሚዎች ደህነነታቸው እስከተረጋገጠ ድረስ፣ የሕዝቡ ወገኖች የሚያውቋቸውን የሕወሃትን ደባ በእነዚህ መድረኮች ላይ በሚኖራቸው ተሳትፎ የሕወሃትን ደባ ማጋለጡ ክፋቱ አይታየኝም። የማይፈልግ አይሳተፍ፤ ተቃዋሚ ሆኖ የሚሳተፍ ደግሞ በደንቡ ተዘጋጅቶ የስብሰባውን ዓላም ማጋለጥ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

ዋናው አሰደናቂው ነገር ተቃዋሚዎችም ሆኑ ታርጋ የሌላቸው አንዳንድ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ባለፈው ጊዜ ስብሰባው ላይ የሠነዘሯቸው አስተያየቶች እጅግ ጠቃሚ ነበሩ። የማናውቀውን ነገር ባንሰማም እንደነ ዶር መረራ ዐይነት ግለሰቦች የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከወጣ በኋላ፡ በሕወሃት በራሱ መድረክ ሕወሃቶች ብቻ እርስ በእርስ ተመሰጋገነው እንዳይለያዩ ማንነታቸውን መነገራቸው መደገፍ አለበት።

ሌላ ከአቶ ይገረም ዓለሙ ጽሁፍ ቅር ያሰኘኝ፡ ኢትዮጵያ ማንም እንደፈቀደው እሱ የሚፈልገው እስካልሆነ ድረስ ይህንን ማድረግ እርሱ/እነርሱ ጠላት ከሚሉት ጋር “…ተባባሪ መሆን ነውና ያስጠይቃል” የሚለው አባባል ሕግ አውጭና ሕግ አስፈጻሚነትን ግለሰባዊ ወይንም አሁንም የቡድን ማድረግ የሚሻ ይመስላል።

ይህም ካለፉት ባልተሻለ መንገድ፣ የግለሰብን የማሰብ፣ የመናገርና በስብሰባዎች ላይ በነጻነት መሳተፍን በመገደብ ዲሞክራሲያዊ ባህል በሃገራችን እንዳይዳብር የተለመደው ቀጣዩ መሰናክል እንዳይሆን እሠጋለሁ! ተሳታፊ የሆኑ ተቃዋሚዎች ለሕወሃት ድጋፍ አይደለም የሠጡት! እነርሱ በመሳተፋቸው ደግሞ ሕወሃትን ከጀመረው ድጥ ያወጣዋል ብዬ አላምንም።

የወደፊቷ ኢትዮጵያ በዜጎች ፍላጎት ላይ የምትመሠረት ናት እስካልን ድረስ፡ ወደፊት በዜጎች ፍላጎቶችና ጥቅሞች ላይ ተመሥርተው በሚወጡት ሕግጋትና መዋቅራዊ ደንቦች መሠረት – ሕጉ እስከፈቀደላቸው ድረስ – በድርጅት የተደራጁ ሰዎች ዓላማቸውን ለማራመድ ተመካክረው የማድረግ መብታቸው መከበሩን ሕዝቡ የሚደግፍ ይመስለኛል።

ታሪካችንን ብዙ ትኩረት ስላልሠጠነው ነው እንጂ፣ ሃገራችን ውስጥ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በተዋህዶና ቅባት ክፍፍል ወቅት ሁሉ፣ ጉዳዮ ውሳኔ እስካገኘበት እስክ 17ኛው ክፍለ ዘመን በየገጠሩ መከፋፈሉ ሥር ቢሰድና ለዘውዱ ችግር ቢፈጥርም፡ በአደባባይ ግን ካህናቱ በግልጽ ተገናኘተው መከራከራቸው የስምምነት ፍሬን አፍርቷል።

የሕዝብ ድጋፍ የሚመነጨው ደግሞ መጭው መንግሥትም ሆነ ውስጡ የሚደራጁት የፖለቲካ ደርጅቶች የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ መብት በማክበር ላይ መሆኑን ከአሁኑ እየጨበጥን ከሄድን ወደፊት የኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ግንባታ የተሻለ መሠረት ላይ የሚያስቀምጠው መሆኑን በግልጽ መገንዘብና ማስተዋል ያስፈልጋል።

ይህ የሕግ መሠረት በሌሎች ሃገሮች እንደሚደረገው ሁሉ የሕዝብን ጥቅም ከሚጎዱ ጋር መተባበር ያስጠይቃል። በሃገራችንም የዚህ መሠረት ‘በሕጋዊ መንገድ የኅብረተሰብን ጥቅም – የፖለቲካ ፓርቲን ሣይሆን’ መጣሉ አስፈላጊነት ቢታመንበትም፡ አሠራሩና አፈጻጸሙ የዘራፍ ባዮች ጅራፍ እንዳይሆን በጥብቅ ልናስብበት ይገባል!

ሕወሃትን መታገል አንድ ነገር ነው! ሃገራችን ውስጥ የ ‘vigilante justice’ ሥርዓት እንዳንኮተኩት ጥንቃቄ ማድረግ ደግሞ ሌላው ነው!
 

%d bloggers like this: