የፓርላማ አባሏን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በብዙ መልኩ የተቃወሙትን የባሕር ዳር ተወካይ ወ/ሮ አዲሴ ዘለቀን ቢሮአቸው ውስጥ ማን/ምን ገደላቸው?

16 Nov

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
ኅዳር ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ/ም (ኢሳት ዜና):በባሕር ዳር ከተማ ሰፈነ ሰላም ክፍለ ከተማ ነዋሪ የነበሩትና የባህር ዳርን ሕዝብ በመወከል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያገለግሉ የነበሩት ወይዘሮ አዲሴ ዘለቀ ባልታወቀ ሁኔታ በአዲስ አበባ ከተማ በትላንትናው ዕለት ማለትም ማክሰኞ ኅዳር 6 /2009 ዓም. በጽ/ቤታቸው ሞተው ከተገኙ በሁዋላ፣ ጉዳዩ የባሕር ዳርን ሕዝብ እያነጋገረ ነው።

ወ/ሮ አዲሴ በፓርላማው በቆዩበት ወቅት ጠንከር ያሉ አስተያየቶችን መሰንዘር የሚታወቁበት ሲሆን በባሕር ዳር ከተማ የክልሉ ምክር ቤት ጥቅምት 06/2009ዓም ባካሄደው ስብሰባ በፓርላማው ሳይፀድቅ ቀድሞ ስራ ላይ የዋለውን የወያኔን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያጸድቀው የቀረበውን ሃሳብ ከተቃወሙት መካከል አንዷ ናቸው፡፡ወይዘሮ አዲሴ በዕለቱ የክልሉን ምክር ቤት አባላት በደስታ ያስጨበጨበ የተቃውሞ ንግግር ያደረጉ ሴት ተወካይ እንደነበሩ የቅርብ ጓዶቻቸው ተናግረዋል።

ወ/ሮ አዲሴ ዘለቀ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሕዝብ ቅሬታ ሰሚ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆነው በሰሩበት ጊዜ አስተዳደራዊ ፍትህ ፈልገው የሚመጡ ባለ ጉዳዮችን በመቀበልና አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ በሁሉም መስሪያ ቤቶች አስተዳደራዊ ጥፋቶች እንዲሻሻሉና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በማደራጀትና በመተንተን ትክክለኛ ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ ሲሰሩ ነበር።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የህዝብ ቅሬታ ሰሚ ጽ/ቤት በህዝብ የቀረቡትን ቅሬታዎች በትክክል መተግበራቸውን ከማረጋገጥ ባሻገር አገልግሎት ሰጭ መስሪያ ቤቶች የተገልጋዩን እርካታ ለማስገኘት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለባቸው በጽኑ ሲታገሉ መቆየታቸውን የሚያውቁዋቸው ሰዎች ይናገራሉ። በወይዘሮ አዲሴ ድንገተኛ ሞት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን እየገለጹ ሲሆን፤ የሟች አስከሬን አለመመርመሩና በጥድፊያ እንዲቀበሩ መደረጋቸው ግለሰቧ የሞቱት በሰው እጅ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ በሕዝቡ ላይ አሳድሯል።

በክልሉ የሚገኙ ባለሥልጣናት የባሕር ዳር ከተማ ተወካይ በድንገት በመሞታቸው “ለምን?” የሚል ጥያቄ ከማንሳትና የአስከሬን ምርመራ ከማድረግ ይልቅ የሃዘን መግለጫ ባነሮችን በማሰራት ለቀብር ሱሯሯጡ ታይተዋል። ትናንት ኅዳር 06/2009 በተወለዱ በ48 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ወ/ሮ አዲስ ዘለቀ የሁለት ልጆች እናት ነበሩ።

የቀብር ሥነ-ስርዓታቸው በባሕር ዳር ከተማ ድንባቄ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በርካታ የከተማዋ ሕዝብ እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ዛሬ ረቡ ከቀኑ በስድስት ሰዓት ተኩል ተፈጽሟል።
 

%d bloggers like this: