በእርግጥ ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ሰላም ሆናለችን? ኢትዮጵያ ውስጥ የፈነዳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ከስሞኑ የኃይለማርያም ደሣለኝ ‘ሰላም መውረድ’ ቅጥፈት አንጻር ሲገመገም!

20 Nov

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በነጋሽ መሐመድና ልደት አበበ የጀርመን ድምጽ ራዲዮ
 


 
የኢትዮጵያዉን ተቃዉሞ፤ ከጆርጂያ እስከ ዩክሬን እንደነበረዉ ቀለም አልተሰጠዉም።ከቱኒዚያ እስከ የመን እንደነበረዉ ርዕሠ-ከተማን በሕዝብ ማዕበል አላጥለቀለቀም።ከሊቢያ እስከ ሶሪያ እንዳየነዉ የእርስበርስ ጦርነት አላቀጣጠለም፤ «አብዮት» በሚል ቅፅል አልተወደሰምም።የተቃዉሞዉ ምክንያት፤ የተቃዋሚዉ ጥያቄ እና ብዛት፤ ተቃዉሞዉ የተቀሰቀሰበት አካባቢ ስፋት ግን ከሌሎቹ ቢበልጥ አንጂ አያንስም።

ጥያቄዉ፤ የአዲስ አበባ የተቀናጀ ማስተር ፕላን የተባለዉን ዕቅድ በመቃወም ጀምሮ፤ የሰብአዊ መብት፤ የዲሞክራሲ፤ የፍትሕ፤ የእኩልነት፤ የነፃነት፤ የታሰሩ ፖለቲከኞች መፈታት፤ የሐብት ክፍፍል፤ ያስተዳደር እያለ እያደገ፤ እየጠነከረ የመጣ ነዉ።

ተቃዉሞዉ፤ ከጊንጪ እስከ ጎንደር፤ ከኮንሶ እስከ ጠገዴ የሚገኙ የመሐል፤ የሰሜን፤ የደቡብና የምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎችን አዳርሷል።የደረሰዉ ጥፋትም ቀላል አይደለም።ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደዘገቡት በትንሽ ግምት ከስምንት መቶ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።በሺሕ የሚቆጠሩ ቆስለዋል።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ታስረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሰየመዉ የአስቸኳይ ጊዜ አጣሪ ቦርድ እንኳን ባንድ ወር ዉስጥ ከ11ሺሕ 6 መቶ በላይ ሰዎች መታሠራቸዉን አምኗል።እርግጥ ነዉ ብዙዎች ቁጥሩ ከተጠቀሰዉ በብዙ እጥፍ ይበልጣል ባዮች ናቸዉ። በንብረት ላይም ከፍተኛ ጥፋት ደርሷል።

መንግሥት ተቃዉሞዉን ለማቆም ከወሰደዉ የሐይል እርምጃ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን የተባለዉን ዕቅድ ሰርዟል።የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል። የኦሮሚያ እና በፌደራሉ መንግስት የካቢኔ ሹም ሽር አድርጓል።ጠቅላይ ሚንስትር ሐይለማርያም ሰሞኑን ለዉጪ ዲፕሎማቶች ነገሩት እንደተባለዉ ደግሞ መንግሥታቸዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገጉ የሐገሪቱን ሠላምና ደሕንነት ማስከበር ችሏል።

በርግጥ ሕዝብ ተረጋግቶ የዕለት ከዕለት ሥራዉን የሚያከናዉንበት ሠላም ሰፍኗል? ዓመት የደፈነዉ ተቃዉሞ፤ የመንግሥት እርምጃዎች፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎችስ ምን ዉጤት አመጡ።ጥቅም፤ ጉዳት አስተምሕሮቱንስ? የዛሬ ዉይይታችን የሚቃኛቸዉ ሐሳቦች ናቸዉ።
 

%d bloggers like this: