ለ40/60 ቤቶች ግንባታ የሚውል በ15 ሲኖትራኮች የተጫነ ብረት መጥፋቱ ተጠቆመ – ቀደም ሲል ቡና ነበር የሚጠፋው ዛሬ ደግሞ እንደመርፌ ይህን ያህል ብረታ ብረት!

23 Nov

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በሪፖርተር
 

“በተደራጀና በሚገባ በታሰበበት ዕቅድ”

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ለ40/60 ቤቶች ግንባታ የገዛው በ15 ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች የተጫነ ብረት፣ ከነተሽከርካሪዎቹ መጥፋቱን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡

ኢንተርፕራይዙ እያስገነባቸው ለሚገኙት የ40/60 የቁጠባ ቤቶች መሥሪያ የሚውል፣ በሚሊዮኖች ብር የተገዛ ብረት አቃቂ በሚገኘው የዋናው ሳይት መጋዘን የሚያከማች ቢሆንም፣ በ15 ሲኖትራኮች የተጫነና መጠኑ ለጊዜው ያልታወቀ ብረት መጥፋቱን ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ኅዳር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ መጋዘኑ የሄዱት ተሽከርካሪዎች ብረቱን ሳያወርዱ ወደ ሌላ ሳይቶች እንዲወስዱ በመጋዘኑ ኃላፊዎች መታዘዛቸውንና የመረካከቢያ ሰነድ ሳይለዋወጡ እንዳልቀሩ የገመቱት ምንጮች፣ በዕለቱ ወይም በማግሥቱ ማድረስ የነበረባቸው ቢሆንም የት እንደደረሱ አልታወቀም ብለዋል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ ከነብረቱ የተሰወሩት ወይም እንዲጠፉ የተደረገው፣ በተደራጀና በሚገባ በታሰበበት ዕቅድ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዳለ ምንጮች አክለዋል፡፡ ድርጊቱ በከፍተኛ ሁኔታ በፀጥታ ኃይሎችና በተለያየ መንገድ ክትትል እየተደረገበት ስለሆነ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ይውላል የሚል እምነት እንዳለ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ ከጫኑት ብረት ጋር ስለመጥፋታቸው ማብራሪያ እንዲሰጡ የኢንተርፕራይዙን የኮሙዩኒኬሽን ሥራ ሒደት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ዓባይነህን ሪፖርተር ጠይቋቸው፣ ‹‹እኛ ጅግጅጋ ሥራ ላይ ከርመን ገና እየተመለስን ነው፡፡ አልነበርንም፣ አልሰማንም፡፡ ሥራ አስኪያጁ አቶ ኃይሉ ቀንዓም አብረውኝ ናቸው፡፡ ምንም የሰማነው ነገር የለም፤›› በማለት ድርጊቱን ከመግለጽ ይልቅ መሸፈን መርጠዋል፡፡

ባለሙያዎች እንደሚሉት አንድ ሲኖትራክ በፋብሪካው ትዕዛዝ መሠረት 150 ኩንታል ብረት የሚጫን ሲሆን፣ እዚህ አገር ግን እስከ 200 ኩንታል ብረት የሚጭኑበት አሉ፡፡ 15 ሲኖትራኮች ላይ ተጭኖ ጠፋ የተባለው ብረት በምን ያህል መጠን እንደተጫነ ለጊዜው ባይታወቅም፣ ከፍተኛ መጠን እንደሚኖረው ግን መጠራጠር አይቻልም ሲሉ ባለሙያዎች ያክላሉ፡፡

የ40/60 የቤቶች ግንባታ መርሐ ግብር መሠረት 39 ሺሕ ቤቶች በግንባታ ላይ ይገኛሉ፡፡ በ2005 ዓ.ም. በተደረገው ምዝገባ 163 ሺሕ ነዋሪዎች ሲመዘገቡ፣ ከ13 ሺሕ በላይ ተመዝጋቢዎች ሙሉ በሙሉ ክፍያ አጠናቀዋል፡፡ በቅርቡም የ1,292 ቤቶችን ዕጣ ለማውጣት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ባንኩ በራሱ ዕጣውን የሚያወጣው ከአዲስ አበባ አስተዳደር ቤቶቹን በመረከብ ነው፡፡
 

%d bloggers like this: