የሠራተኞች አመለካከት ባለመቀየሩ ምርታማነታችን ቀንሷል ይላሉ ምሥራቅ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የሚገኙ የኩባንያ ባለቤቶች

4 Jan

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2009 (ኢዜአ) ሠራተኞች ለስራ ያላቸው አመለካከት ባለመቀየሩ ምርታማነታችን እንዲቀንስ አድርጓል ሲሉ የኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን የሥራ ኃላፊዎች ገለፁ።

ሠራተኞች በበኩላቸው የሚከፈላቸው ክፍያና የሚሰሩት ስራ ተመጣጣኝ አለመሆኑ በሥራቸው ውጤታማ እንዳይሆኑ ማድረጉን አንስተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ዛሬ የኢንዱስትሪ ዞኑን የስራ እንቅስቃሴ የጎበኘ ሲሆን ከኩባንያዎቹ ኃላፊዎችና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ተወያይቷል።

በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩት የቻይና ኩባንያ የስራ ኃላፊዎች በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት ሰራተኞች ያለበቂ ምክንያት ከሥራ ስለሚቀሩ የሚፈለገውን ያህል ምርት በብዛትና በጥራት ማግኘት አልተቻለም። ይህም ኩባንያዎቹ ትርፋማ እንዳይሆኑና በሰራተኞች ክፍያ ላይም ጭማሪ እንዳያደርጉ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው።

የኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ጂኦ ዮንግሹን እንደሚሉት ሰራተኞቹ ያለ በቂ ምክንያት ከሥራ ገበታቸው ላይ በመቅረታቸው የሚፈለገው ምርት በፍጥነትና በጥራት እንዳይመረት አድርጓል።

መንግሥት ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የውጭ ባለሃብቶችን እየሳበ ቢሆንም የሰራተኞችን አመለካከት ለመቀየር ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅበት ነው የተናገሩት። ሠራተኞች በሥራቸው ውጤታማነት እየተለኩ ክፍያቸው የሚጨምር ቢሆንም አብዛኞቹ ክፍያው አነስተኛ ነው በሚል ሥራቸውን በአግባቡ እየሰሩ አለመሆኑንም ነው የተናገሩት።

ከኩባንያዎቹ ሠራተኞች መካከል የሌንድ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኛ ወጣት ፀሃይ አባዲ ክፍያው አንስተኛ በመሆኑ ወርሃዊ ወጪዎቹን ለመሸፈን እንደሚቸገር ገልጾ ይህም በሥራ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያስከትል ተናግሯል፡፡

አየሉ ተክሌ የተባለው የልብስ ስፌት ሠራተኛም እንዲሁ አምሽቶ ቢሠራም የሚከፈለው ክፍያ ከሚሰራው ስራ ጋር እንደማይመጣጠን ነው የገለጸው፡፡

የቢ ኮኔክትድ የአልባሳት ፋብሪካ ሰራተኛዋ ትቅደም አማረ እንደምትለው ደግሞ የአብዛኛው ሰራተኛ ደመወዝ ከ600 ብር እንደማይበልጥ ተናግራ ይህም የቤት ኪራይዋን እንኳን በአግባቡ እንደማይሽፍንላት ተናግራለች፡፡

የቢ ኮኔክትድ ኩባንያ የሰው ኃብት አስተዳደር ኃላፊ ወይዘሮ ናሆሚ አዋሽ ሠራተኞቹ ስራቸውን በአግባቡ ከሰሩ የተለያዩ ማበረታቻዎች እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል፡፡

ለዚህም አንድ ሠራተኛ በሥራ ሰዓቱ ከተገኘና የሚጠቀምባቸውን መሳሪያዎች በአግባቡ ከያዘ 300 ብር ተጨማሪ የማበረታቻ ክፍያ የሚሰጥ መሆኑን በአብነት አንስተዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተወካይ አቶ መከተ ነጋ መንግስት የሠራተኛውን አመለካከት ለመቀየር ስልጠናዎችን እንደሚያመቻች ገልጸዋል።

ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን በ2000 ዓም ሥራ የጀመረ ሲሆን ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የተለያዩ ምርቶችን ያመርታል። ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የስራ ዕድል ፈጥሯል።
 

%d bloggers like this: