የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት 40% ድርሻ ለመሸጥ ድርድር መጀመሩ ተሰማ: የሃገር የባሕር በር በማስረከብ የሚታወቀው ሕወሃት መርከቦቹን ለቻይና ቀርቶ ራሱ ቢገዛስ/ቢዘርፍ ምን ያስገርማል?

4 Jan

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
ሪፖርተር
 
*  የሕወሃት ኢትዮጵያን ማራቆት

*   የመርከብ አገልግሎት ዋነኛውን ድርሻ ይይዛል

ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ በግዙፍነታቸው ከሚጠቀሱ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ፣ 40 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ለመሸጥ ድርድር እየተካሄደ ነው፡፡

አራት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በመዋሀድ እንደ አዲስ የተቋቋመውን ኢንተርፕራይዝ 40 በመቶ የሚሆነውን የባለቤትነት ድርሻ በመሸጥ ማኔጅመንቱን በጋራ ለማስተዳደር ከመንግሥት እየተደራደረ ያለው፣ አንድ የቻይና ኩባንያ መሆኑን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ ከሆነ መንግሥት የእዚህን ግዙፍ ተቋም የተወሰነ ድርሻ ለመሸጥ ጀመረ የተባለው ድርድር ያልተጠበቀ ሲሆን፣ ወደዚህ ሐሳብ የተገባበት ምክንያት ግልጽ አለመሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይገልጻሉ፡፡ ድርድሩም በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተያዘ ስለመሆኑ የሚጠቁመው የምንጮች መረጃ፣ በተለይ ከ60 ዓመታት በላይ የቆየውን የመርከብ አገልግሎት ዘርፍ ያጠቃልላል ተብሏል፡፡ ይህ ደግሞ በዚህ አገልግሎት ዘርፍ አገሪቱ ይዛ የቆየችውን ተጠቃሚነት ሊያሳጣት ይችላል የሚል ሥጋት እንደፈጠረባቸው የሚናገሩት ምንጮች፣ የሽያጭ ድርድሩ ከአጠቃላይ የኢንተርፕራይዙ ሀብት በመቶኛ ተሰልቶ የሚደረግ ነው ይላሉ፡፡

የኢንተርፕራይዙን የባለቤትነት ድርሻ በተወሰነ ደረጃ በሽያጭ የማዛወሩን ዕቅድ በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራናቸው የኢንተርፕራይዙ የሥራ ኃላፊዎች ደግሞ፣ ስለጉዳዩ ምንም መረጃ የሌላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ጉዳዩን በወሬ ደረጃ ከመስማት ውጪ የሚያውቀው ነገር አለመኖሩን ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ከኢንተርፕራይዙ የባለቤትነት ድርሻ ላይ የተወሰነውን ለማስተላለፍ ንግግሮች እየተደረገ ስለመሆኑ የተለያዩ ወገኖች እየገለጹ ሲሆን፣ ይመለከታቸዋል የተባሉ አካላት በጉዳዩ እንዳይሳተፉ መደረጋቸውንም ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደ ቴሌ፣ አየር መንገድና ባንኮች ሁሉ ኢንተርፕራይዙ የውጭ ኩባንያን ለማስገባት ፍላጐት እንዳልነበረው ቢገመትም፣ አሁን የ40 በመቶ የባለቤትነት ድርሻውን ለማስተላለፍ ተደረሰበት የተባለው ደረጃ አስፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ፡፡

ኢንተርፕራይዙ በሥሩ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብን፣ የኢትዮጵያ ደረቅ ወደብ አገልግሎትን፣ የማሪታይምና በቅርቡ ግዙፉን የትራንስፖርት ድርጅት ኮሜት ትራንስፖርት አገልግሎትን አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡ በአትራፊነቱ የሚጠቀስ የመሆኑን ያህል አገራዊ ምልክትም በመሆኑ ከመንግሥት ባለቤትነት መውጣት አይኖርበትም በማለት የሚከራከሩ አሉ፡፡ በእርግጥ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ ከሆነ ማኔጅመንቱን በተወሰነ ደረጃ መስጠት እየተቻለ፣ ለምን ወደዚህ ሐሳብ እንደተገባ ግልጽ አለመሆኑን የሚገልጹም አልጠፋም፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ብቻ ከ1.3 ቢሊዮን ብር ትርፉ እንዳስመዘገበ የሚጠቁሙት መረጃዎች በየዓመቱ ትርፍ እያደገ መምጣቱን ያስረዳሉ፡፡

ኢንተርፕራይዙ በ2008 በጀት ዓመት ብቻ ወደ 17 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ያስገባ ሲሆን፣ ይህ ገቢ ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር በየዓመቱ እያደገ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ኢንተርፕራይዙ በአምስት ዋና ዘርፎች የተከፋፈሉ አገልግሎቶችን የሚሰጥ በመሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ በተለይ የመርከብ ዘርፍን የባለቤትነት ድርሻ ማካፈል ላይ ከተደረሰ አገራዊ ጉዳቱ ያመዝናል በማለት ሥጋታቸውን የሚናገሩ አሉ፡፡ በተለይ ኢንተርፕራይዙ ከሚያገኘው ገቢ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ከመርከብ ዘርፍ አገልግሎት መሆኑ ደግሞ፣ የመርከብ ዘርፉን የባለቤትነት ድርሻ ማስተላለፍ በአገር ገቢ ላይም ተፅዕኖ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያን የወጪና የገቢ ንግድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋ በሚወስኑ የመርከብ አጓጓዦች እጅ እንዳይወድቅ፣ አገሪቱ ለአገልግሎቱ ከፍተኛ የሆነ ወጪ እንዳታወጣ ያገዛት የራሷ መርከቦች ባለቤት በመሆኗም ጭምር መሆኑንም ያወሳሉ፡፡

ከ60 ዓመታት በላይ የዘለቀው የንግድ መርከብ አገልግሎት በውጭ ተቋማት ሥር ከወደቀ አገራዊውን ጥቅም ሊጎዳ ይችላል የሚል ሥጋት ያላቸው ወገኖች፣ በዚህ ዘርፍ አገሪቷ ይዛ የቆየችውን ጥንካሬ ሊያሳጣት እንደሚችልም ሥጋታቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ዛሬ የባህር በር ከሌላቸው አገሮች የራሷን መርከቦች በመጠቀም የገቢና የወጪ ዕቃዎችን በማስተናገድ የምትታወቅ ሲሆን፣ በተለይ ገቢ ዕቃዎችን ከውጭ ኩባንያዎች ተፅዕኖ ውጪ ለማስገባት መቻሏ በራሱ ለኢኮኖሚውም ትልቅ ጥቅም አለው በማለትም ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ አሁንም ሆነ ቀደም ብሎ በራስዋ መርከቦች መገልገል በመቻሏ፣ በቀይ ባህር አካባቢ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ ቀውሶች የመርከብ አገልግሎት ዋጋን በሚያንሩበት ወቅት ተጠቃሚ ሲያደርጋት ቆይቷል፡፡ አሁንም አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚታዩ ውጥረቶች በተከሰቱ ቁጥር የመርከብ አገልግሎት ዋጋ ሲጨምር፣ ኢትዮጵያ በራስዋ መርከብ ማጓጓዝዋ ከከፍተኛ ወጪ ስለሚያድናት የመርከብ ዘርፍን ባለቤትነት ድርሻ ማካፈል ጎጂ ሊሆን ይችላል የሚል ሐሳብ ይሰማል፡፡

በሌላ በኩል ግን የንግድ መርከቡን ዘርፍ የባለቤትነት ድርሻ ማስተላለፍ ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል የሚል አቋም ያላቸው ወገኖች ደግሞ፣ እንዲያውም መንግሥት ዘግይቷል የሚል እምነት አላቸው፡፡ የአገሪቱ የገቢ ዕቃዎች በኢንተርፕራይዙ ብቻ እንዲስተናገዱ የሚያስገድድ በመሆኑ፣ ለገቢ ዕቃዎች ኢንተርፕራይዙ የሚያስከፍለው የማጓጓዣ ዋጋ ከፍተኛ መሆን የገቢ ዕቃዎች ዋጋ እንዲንር አንድ ምክንያት እንደነበር ይጠቁማሉ፡፡

ኢንተርፕራይዙ ለሚያጓጉዛቸው ዕቃዎች የሚጠይቀው ዋጋ ፈጽሞ ከሌሎች ጋር እንደማይገናኝ የሚጠቁሙት እነዚህ ወገኖች፣ የባለቤትነት ድርሻውን ካከፈለ ግን በውድድር የሚስተናገድ በመሆኑ በአማራጭነት ተገልጋዮች ሊጠቀሙ ይችላሉ ይላሉ፡፡ የባለቤትነት ድርሻ በውስጡ አስገዳጅ ነገሮችን ያስቀራል የሚል እምነትም አላቸው፡፡

ኢንተርፕራይዙ በአሁኑ ወቅት 11 አዳዲስ የሚባሉ መርከቦች ያሉት ሲሆን፣ በዓመት የጭነት ማመላለስ አቅሙን ከአምስት ሚሊዮን ቶን በላይ አድርሷል፡፡ ከ220 በላይ መዳረሻዎች ያሉት የአገሪቱ የመርከብ አገልግሎት 60 በመቶ የሚሆነውን ወጪና ገቢ ዕቃዎች ያጓጉዛል፡፡ ቀሪውን ደግሞ ከሌሎች የመርከብ ድርጅቶች በኪራይና በሽርክና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ኢንተርፕራይዙ በአሁኑ ወቅት በሥሩ ከ260 በላይ የዕቃ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች አሉት፡፡ ሰባት የደረቅ ወደቦችን ያስተዳድራል፡፡ የኢንተርፕራይዙ አጠቃላይ ሀብት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ይገመታል፡፡

%d bloggers like this: