አብርሃም ጓዴ: የኢትዮ-ቴሌኮም አቅርቦትና ፋሲሊቲ ኃላፊ ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በመሩት ምርመራ በሙስና ተጠርጥረው ተያዙ ይባላል

13 Jan

የአዘጋጁ አስተያየት

    ሕወሃት ራሱን ለማዳን ብዙ ጭዳ ዶሮች ሳይስፈልጉት አይቀርም! ስለሆነም በየቀኑ ስለሚታሠሩት ግለሰቦች ገና ብዙ እንሰማለን! እነዚህም እንደቱባዎቹ የሕወሃት ሰዎች ሃገራችንን የቦጠቦጧት አይደሉም። የሕዝቡ ትግል ወላፈን የጋለና ኮማንድ ፖስቱም ሊያበርደው የማይችል በመሆኑ፡ የሃገራችንን ደም የመጠጡት ዜጎቻችን ያሠቃዩና ደማቸውን ያፈሰሱት ለሃቀኛ ፍርድ እስኪቀርቡ ድረስ፣ የሕዝቡ ቁጣ ይቀጥላል፡ ሕወሃትም፣ መካከለኛና አንዳንዶችን እንደነአብርሃም ጓዴ ዐይነትን መሃል ላይ ጣል እያደረገ ሙስናን የሚታገል ለመምሰል ወህኒ ይሰዳቸዋል። ዜጎች በዚህ መወናበድ የለባቸውም።

    ሙስናን መመንጠር ተጀመረ ለማለት የሚቻለው፣ ሃገራችንን በብድር ጭምር ከውጭ የመጣውን ገንዝበ ሠልቅጠው ንብረት ያፈሩትን፣ ዜጎችን አፈናቅለው በንብረት ላይ ንብረት፣ ፋብሪካዎች፣ ፎቅ ቤቶች፣ የውጭ ባንክ ማልሚያ የሆኑትን ገንዘቡን እንዴት አገኝኸው ተብለው የሕወሃት ውስጠ ንጽህናው በተጨባጭ ሲረጋገጥ ነው!

    እስከዚያ ድረስ ግን በጋንቤላ የመሬትና የልማት ባንክን ዘረፋ በተመለከተ እነማን እንደተቀጡ ስለምናውቅ፣ ከሌሎች ብሄረሰቦች የወጡትን ጥቃቅን ሃብታሞችና በቢሮክራሲው ዝቀተኛ ደረጃ የማሠርና ማሳደድ – እንደተሃድሶው ሁሉ –ማደናበሪያና የነኃይለማርያም አልቅላቂነት ማሳያ ብቻ ሆኖ ይቀራል!

==============
 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
ሠንደቅ የመነጨ
 

ሁለት የቡድን መሪዎች ከሀገር ኮብልለው ወጥተዋል

የኢትዮ-ቴሌኮም አቅርቦትና ፋሲሊቲ ቺፍ በሙስና ተጠርጥረው መያዛቸውን የሰንደቅ ምንጮች ገለፁ።
የኢትዮ-ቴሌኮም አቅርቦትና ፋሲሊቲ ኃላፊ የነበሩት አቶ አብርሃም ጓዴ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የተያዙት፣ በድርጅቱ ውስጥ በሌሉ መኪኖች የነዳጅ ግዢ በመፈጸምና በማወራረድ፤ ለድርጅቱ አገልግሎት ለመስጠት በሚቀርቡ መኪናዎች ላይ ሕገወጥ የመኪና ኪራይ በመሰብሰብ እና ለአገልግሎት የሚቀርቡ መኪናዎች ከተቀመጠላቸው የአገልግሎት ዘመን ውጪ በኪራይ መልክ እንዲቀርቡ አድርገዋል ተብሎ ነው።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ እና የመገናኛና የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ዶክተር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ሰብሳቢነት በቅርቡ ተካሂዶ የነበረው የኢትዮ-ቴሌኮም የሥራ አፈፃጸም ግምገማ፣ በፍሬምዎርክ የጨረታ ግዢ፣ ተቋሙ በኪራይ የሚጠቀምባቸው መኪናዎች እና ለኢትዮ-ቴሌኮም አገልግሎት መስጫ በሚቀርቡ ቁሳቁሶች ግዢ ላይ የአሰራር ችግር እና ሙስና የሚፈጸምባቸው መሆኑን በወቅቱ ከተሳታፊ ኃላፊዎች በግምገማ መድረኩ ላይ መቅረቡ የሚታወስ ነው።

በጊዜው በግምገማው መድረክ ላይ የተገኙ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ኃላፊው እንደገለፁልን፤ “የቀድሞ የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን ኮርፖሬሽን ወደ ኢትዮ-ቴሌኮም ሲቀየር ብዙ የመዋቅር ሥራዎች ተደርገዋል። ከሚጠቀሱት መካከል ተቋሙ በራሱ መኪናዎች እና ጋራዦች ሲያገኝ የነበረውን አገልግሎቶች በአጠቃላይ በሚባል ደረጃ ከሶስተኛ ወገኖች በሚገኝ አገልግሎት እንዲተካ ተደርጓል። ይህንን አሰራር ተከትሎ በርካታ ተሽከርካሪዎች በይፋ ጨረታ እንዲሸጡ ተደርገዋል። በመቀጠልም መስሪያቤቱም ለሚያከናውናቸው ሥራዎች መኪናዎች እየተከራየ እንዲጠቀም አሰራር ተዘርግቷል።

ለኪራይ የሚቀርቡ መኪናዎች እ.ኤ.አ. ከ2000 በኋላ የተመረቱ መሆን እንዳለባቸውም በግልፅ ተደንግጎ እያለ ከመስሪያቤቱ በሽያጭ የተወገዱ መኪኖች የተለያዩ የተጭበረበሩ ሊብሬዎች እየተዘጋጀላቸው እንደአዲስ ለተቋሙ የኪራይ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። መኪናዎቹ ለመከራየት ሲቀርቡ የሚደረግባቸውን የቴክኒክ ፍተሻዎች ለማለፍ 3ሺ ብር እጅ መንሻ ይሰጣሉ። እንዲሁም የተቋሙ ከፍተኛ ኃላፊዎች የራሳቸውን የግል መኪናዎች ለተቋሙ አገልግሎት እንዲሰጡ በኪራይ መልክ ያቀርባሉ። እራሳቸው ተከራይ እራሳቸው መኪና አቅራቢ የሆኑበትን ሕገወጥ አሰራር በስፋት ዘርግተው ኪራይ ሰብሳቢ ሆነዋል” ሲሉ ማጋለጣቸው የሚታወስ ነው።

ግምገማውን የመሩት ዶክተር ደብረፂዮን በርግጥም የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች የራሳቸውን የግል መኪናዎች ለተቋሙ በኪራይነት የሚያቀርቡበትን የአሰራር አግባብነት ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ለመድረኩ ጥያቄ አቅርበው የነበር ሲሆን፣ ለዶክተሩ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዱአለም አድማሴ የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የራሳቸውን የግል መኪናዎች ለተቋሙ በኪራይ እንደሚያቀርቡ አምነው ተናግረዋል።

አቶ አንዱአለም አያይዘውም “ይህን አሰራር ለማቆም ብፈልግም ከተቋሙ የህግ ክፍል የተፃፈልኝ ደብዳቤ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ መኪናቸውን የማከራየት መብት እንዳላቸው የሚገልጽ በመሆኑ አሰራሩን ለማስተካከል እርምጃ ለመውሰድ አልቻልኩም” ሲሉ የገጠማቸውን የአሰራር ክፍተት ለሚኒስትሩ ማሳወቃቸው ይታወቃል።

ዶክተር ደብረፂዮንም በበኩላቸው ከሕግ ክፍል ተፃፈ የተባለው ደብዳቤ ከማብራሪያ ጋር እንዲቀርብላቸው በጠየቁት መሰረት በተሰጣቸው ምላሽ መነሻ አቅርቦትና ፋሲሊቲ ኃላፊ የነበሩት አቶ አብርሃም ጓዴ ጉዳይ በሕግ እንዲጣራ መወሰናቸውን ምንጮቻችን ገልጸውልናል።

በቀጣይ ከፍሬምዎርክ ጨረታ አሰጣጥ ሥርዓት እና ሌሎች ለኢትዮ-ቴሌኮም አገልግሎት መስጫ በሚቀርቡ ቁሳቁሶች ዙሪያ ከኢትዮ-ቴሌኮም የሥራ ኃላፊዎችና ከአቅራቢዎቹ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ በሚፈጸሙ ሙስናዎች ተጨማሪ እርምጃዎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እስካሁን ባለን መረጃ በኢትዮ-ቴሌኮም በአቅርቦትና ፋሲሊቲ ዘርፍ ስር የነበሩ ሁለት የቡድን መሪዎች ከሀገር መኮብለላቸው ታውቋል። ኢትዮ-ቴሌኮም እንደአስፈላጊነቱ በዓለም አቀፉ ፖሊስ ሊያድናቸው ይችላል ተብሏል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ፈልገን ለኢትዮ-ቴሌኮም ኮሙኒኬሽን ቢሮ ደጋግመን ብንደውልም ስልካቸው አይነሳም።
 

%d bloggers like this: