የወጪ ንግድ አለማደግ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት አንድ ፈተና ሆኗል – የኢትዮጵያ ፕላን ኮሚሽን

7 Feb

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) የኢትዮጵያ ፕላን ኮሚሽን በ2009 በጀት ዓመት አጋማሽ የኢኮኖሚ አፈፃፀም ላይ የወጪ ንግድ እድገቱ ተጨባጭ ለውጥ አለማሳየቱ ገለጸ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ይናገር ደሴ የምጣኔ ሃብታዊ እድገት በታሰበው መልኩ እንዳይራመድ ስጋት ከሆኑት መካከል የወጪ ንግድ እድገት በታቀደው መልኩ አለመፈፀሙ ዋነኛው ነው ብለዋል።

ይህም ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ፍጥነት እየገታው መሆኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ፥ በ2009 በጀት ዓመት ጅማሮ ላይም ዘርፉ እምብዛም ለውጥ እንዳልታየበት ገልጸዋል።

ከወጪ ንግድ የታቀደውን ያክል ገቢ ሃገሪቱ እንዳታገኝ ካደረጓት ምክንያቶች መካከል፥ የውጭ ገበያ ምርት አቅራቢ አምራቾች ላይ የሚታየው ደካማ የማምረት አቅም፣ የምርቶች አይነት ውስንነት እና በዓለም አቀፍ ገበያ የታየው የፍላጎት መቀዛቀዝ ይጠቀሳሉ፡፡

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ለሰፈሩ አብይ የልማት ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ፥ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የተጠበቁት ሀገራት እድገት መቀዛቀዝም ሌላው ተፅዕኖ አድራሽ ጉዳይ መሆኑን ነው ዶክተር ይናገር ያነሱት።

በንግድ ስርዓቱ እና በአንዳንድ ዘርፎች ላይ የሚታየው ብልሹ አሰራርም ለእድገቱ ስጋት ነው ብለዋል።

የወጪ ንግድ እድገትን ለማፋጠን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እና የአምራች ተቋማትን አቅም ማጎልበት፥ በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች መካከል ይነሳሉ።

በ2009 ዓመት በአገልግሎት ዘርፍ በተለይ በማህበራዊ ዘርፍ በጅምላ ንግድ እና በባንኮች የፋይናንስ ዘርፎች ላይ የተሻለ ውጤት መመዝገብ ጀምሯል ይላሉ ዶክተር ይናገር፡፡

የሃገሪቱ ምጣኔ ሃብት በኢትዮጵያ በ2008 በጀት ዓመት ከ50 ዓመታት ወዲህ የተከሰተውን ከባድ ድርቅ ተቋቁሞ የ8 በመቶ እድገት አሳይቷል፤ የታቀደው የ11 በመቶ እድገትም በድርቁ ሳቢያ አልተሳካም፡፡

በዚሁ ዓመት የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚው የ2 ነጥብ 3፣ ኢንዱስትሪ የ20 ነጥብ 3 እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፍ የ8 ነጥብ 7 በመቶ እድገት አስመዝግበዋል።

በሌላ በኩል፥ የ2009 ዓመት የኢኮኖሚ እድገት ትንበያን በተመለከተ በበጀት ዓመቱ ማብቂያ፥ ምጣኔ ሃብቱ በመሰረታዊ የእድገት አማራጭ በ11 በመቶ እንደሚያድግ፥ በዚህም በ2008 በጀት ዓመት የነበረውን ጫና እንደሚያካክስ ይጠበቃል።

በከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት አማራጭም ምጣኔ ሃብቱ በ12 ነጥብ 2 በመቶ የማደግ እድል እንዳለው የገለጹት ዶክተር ይናገር፥ ይህ እንዲሳካ ደግሞ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እድገት አፈፃፀም ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪው ዘርፍ እያደገ ሲሆን፥ አሁን ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ 16 ነጥብ 6 በመቶ ሆኗል።

ዘንድሮ በተለይ በግብርና ምርቶች በታየው የምርት ጭማሪ ሳቢያ የዋጋ መውደቅ እንዳይከሰት፥ በከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የተዋቀረ ቡድን ክትትል እያደረገ መሆኑም ተነግሯል።
 

%d bloggers like this: