ሰኔም መጥቶ ሄዷል! የህዳሴ ግድብ የማመንጨት አቅም ግን ወደ 6,450 ሜጋ ዋት አደገ ይላል ምኑንም ለማመን የሚያስቸግረው ደብረጽዮን

26 Feb

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)</em>
 

“ኅብረተሰቡ ለግድቡ የሚያደርገው ተሳትፎም ዛሬም በተጠናከረ መንፈስ እየቀጠለ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ደብረጽዮን፥ አርሶ አደሩ በአካባቢ ጥበቃ ስራው በመሳተፍ፣ ሰራተኛውም በየአመቱ የቦንድ ግዥ በማከናወን ተሳትፎው ተጠናክሮ እሰካሁን 9.4 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።”

ሕዝቡ ደግሞ ወደሽ ነው በግድሽ ይላል በየወሩ ከደሞዙ ሲቆረጥ፤ መዋጮ በየወቅቱ እንዲከፍል ሲገደድ!


አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሃይል የማመንጨት አቅሙን በ450 ሜጋ ዋት በማሳደግ አጠቃላይ አቅሙን 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት ማድረስ የሚያስችል ስራ መሰራቱን የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል ዛሬ የግድቡ መሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 6ኛ አመት ምክንያት በማድረግ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ ከ56 በመቶ በላይ መድረሱን ገልፀዋል።

5 ሺህ 250 ሜጋ ዋት የማመንጨት ግብ በማስቀመጥ ወደ ግንባታ የተገባው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተሰሩት አቅም የማሳደግና የቴክኖሎጂ ማሻሻያዎች ዛሬ ላይ 1 ሺህ 200 ሜጋ ዋት ያህል ሃይልን ለማመንጨት የሚያስችል አቅም ተጨምሮለታል።

ይህም የተከዜ፣ የበለስና የግቤ ሁለት ሃይል ማመንጫ ሶስት ግድቦች ሃይል የማመንጨት አቅም ነው።

የግድቡ ሃይል የማመንጨት አቅም ያደገው የሀገር ውስጥ አቅምን በመጠቀም በግድቡ ላይ ያሉት ጀነሬተሮች ማሻሻያ ስለተደረገላቸው መሆኑንም አንስተዋል።

ግድቡ ቀደም ብሎ 750 ሜጋ ዋት እንደሚያመነጭ የታቀደ ሲሆን፥ ለዚህም የሚያበቁ ስራዎች ከወዲሁ እየተጠናቀቁ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

የመቀበያና የማሰራጫ ጣቢያዎች ግንባታና የማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው የቀረው እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ ሁለት ተርባይኖች የመግጠሙ ሰራ ነው ብለዋል ዶክተር ደብረፅዮን።

በመቀጠልም ግድቡ ውሃ እንዲይዝ የማድረጉ ሂደት ነው የሚከናወነው ያሉት ሚኒስተሩ፥ በመንግስት በኩል ውሃ ለመያዝ የሚያስችል የመጨረሻ ዝግጅት እየተደረገ ነው፤ ከግብጽና ሱዳን መንግስታት ጋር ምክክር ለማድረግም በዝግጅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ምንም ጫና እንደማይፈጥር ያረጋገጡት ዶክተር ደብረጽዮን፥ የግድቡ ውሃ የሚተኛበት አካባቢ ምንጣሮ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

የግድቡ ግንባታ በውጭ ምንዛሬ ምክንያት እንዳይስተጓጎልም ቅድሚያ ተሰጥቶታል ነው ያሉት።

ህብረተሰቡ ለግድቡ የሚያደርገው ተሳትፎም ዛሬም በተጠናከረ መንፈስ እየቀጠለ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ደብረጽዮን፥ አርሶ አደሩ በአካባቢ ጥበቃ ስራው በመሳተፍ፣ ሰራተኛውም በየአመቱ የቦንድ ግዥ በማከናወን ተሳትፎው ተጠናክሮ እሰካሁን 9 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት 6ኛ አመት “ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የሀገራችን ህብረ ዜማ የህዳሴያችን ማማ” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ይከበራል።
 

%d bloggers like this: