በሀገሪቷ ተከስቶ የነበረው የሕዝብ ቁጣ ኢንቨስትመንቶች ማሸሹን ሕወሃት አመነ

27 Feb

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በአዲስ አድማስ
 

ባለፈው ዓመት በሀገሪቷ ተከስቶ በነበረው ተቃውሞና ግጭት የውጪ ኢንቨስተሮች ንብረት ኢላማ ተደርገው መውደማቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ የምትፈልገው የውጪ ኢንቨስትመንት በ20 በመቶ መቀነሱን መንግስት አስታውቋል፡፡

የ2000 ዓ.ም ግማሽ አመትና የዘንድሮውን ግማሽ ዓመት ሪፖርት በማነፃፀር መረጃውን ለብሉምበርግ የዜና ወኪል የገለፁት የኢትዮያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ ባለፈው ዓመት እስከ ታህሳስ ድረስ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ ችላ የነበረ መሆኑንና በዘንድሮ ተመሳሳይ ወቅት 1.2 ቢሊዮን ዶላር መሳብ መቻሏን አስረድተዋል፡፡

ይህም መንግስት በዚህ ዓመት የውጪ ኢንቨስተሮችን በመሳብ አሳካዋለሁ ብሎ ያሰበው እቅዱ እንደማይሳካለት ከወዲሁ ያረጋገጠ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡

በዚህ አመት በጠቅላላው 3.5 ቢሊዮን ዶላር የውጪ ኢንቨስትመንት እቅድ መንግስት ይዞ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ፍፁም ይህ አሁን ላይ እንደማይሳካና 3.2 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል ለብሉምበርግ፡፡

በተቃውሞና ግጭቱ ወቅት ንብረት ለወደመባቸው ኢንቨስተሮች 100 ሚሊዮን ብር ካሣ መክፈሉንም ኮሚሽነሩ አስታወቀው የታክስ አፎይታ ጊዜም ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡

የትኛውም የውጪ ኢንቨስተር በችግሩ ተደናግጦ የፕሮጀክት እቅዱን እንዳልሰረዘና አሁንም በሃገሪቱ ተስፋ ማድረጉንም የጠቆሙት አቶ ፍፁም ምንም እንኳ ከመንግስት እቅድ 20 በመቶ ባይሳካም በቀጣይ 6 ወር የውጭ ሃገር ግዙፍ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች የሃገሪቱን ኢንዱስትሪ ይቀላቀላሉ ብለዋል፡፡ አያይዘውም በአፍሪካ ትልቁ ነው ያሉት የሃዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክም በመጪው ሃምሌ ስራ እንደሚጀምር ነው የገለጹት፡፡

በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የቻይና፣ የህንድ፣ የቤልጂየም፣ የስፔን፣ የፈረንሳይ፣ የሆንግ ኮንግ፣ የሴሪላንካ እና የኢንዶኔዥያ ኩባንያዎች ኢንቨስት እንደሚያደርጉ አቶ ፍፁም ጨምረው አስታውቀዋል።

በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነቡ ነው ተብለው ከሚጠቀሱ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን የጠቆመው ብሉምበርግ የዜና ወኪል አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ሀገሪቱ ባለፉት 5 ዓታመት በተከታታይ የ9.1 በመቶ ሀገራዊ እድገት እያስመዘገበች መዝለቋንና በዘንድሮ ዓመት ግን ይህ ወደ 7.5 በመቶ ዝቅ እንደሚል መተንበዩን አስቀምጧል፡
 

%d bloggers like this: