“የጥቁር ፈርጥ”፡ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊያዩት የሚገባ ኢትዮጵያዊ ፊልም!

17 Mar

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)
 
ከምወዳት ሃገሬ ከወጣሁ ከሶስት አሥርታት በላይ አስቆጥሬያለሁ። ኢትዮጵያን በየቀኑ ስለምናፍቃት ቀንም ሆነ ማታ ፍቅራችንና ናፍቆታችን እንደተጠናከረ ነው። ረዘም ያሉ ምዕተ ዓመታት ያሳለፈች ሃገር ብትሆንም፣ በተለይም በስተርጅናዬ ለኔ አሁንም ቆንጆና ተወዳጅ ናት! አዳሬም ከኢትዮጵያ ጋር ነው። አሁንም ማራኪ ናት – እንደ ሃገር መጎሳቆሏና በሕዝቧ ላይ ያለመቋረጥ የደረሰው መጎሳቆል እንደቀጠለ ቢሆንም!

አሁን በጡረታ ሕይወቴ በየቀኑ ስለኢትዮጵያ አነባለሁ፤ ጽፋለሁ! በራሳቸው ምርጫ ለሕወሃቶች እሬት ካደረጉኝ ሰንበት ብሏል – ምንም እንኳ ይህ የኔ ዓላማ ባይሆንም! እንደተማረ ሰውና ከማንም ጋር በፖለቲካ ባልቧደንም፣ ሃገራችን ሃሣብን በነጻ የመግለጽ መብት የተገፈፈባት በመሆኗ ሃሣቤን በጡረታ ዘመኔ በነጻነት መግለጽን ሙያዬ ማድረጌ ከገዥው ቡድን ጥርስ ከቶኛል። በመሆኑም እነሆ ሃገር ኖኝ ሳለ፡ ከሕግ ውጭ ተፈጥሮአዊ ሃገርና ዜግነት የሌለው የቀድሞ ዜጋ አድርጎኛል – ለመታደስ የተላከውን ፓስፖርቴን ውጠው ጭጭ በማድረግና ጠብቄ የኖርኩትን ዜግነት በሕገ ወጥነት በመግፈፍ! በዚህም የብዙ ኢትዮጵያውያን ዕጣ ፈንታ ተካፋይ ሆኛለሁ!


የኢትዮጵያን ፊልሞች ማየት ከጀመርኩ ሁለት ወራት ያህል ሆኖኛል። ይህ ለኔ ኮለምበስ አሜሪካን እንዳገኛት በታሪክ ያነበብነውን ዐይነት ስሜት ፈጥሮብኛል!

ለነገሩ፣ በሰላሙም ቀን እኔም ሆን ባለቤቴ ፊልምና ሙዚቃ እንወዳለን። የኢትዮጵያን ፊልሞች ማየት ከጀመርኩበት ጊዜ ወዲህ፡ በእነዚህ ወራት ውስጥ ሁለት ሶስት የውጭ ፊልሞች አይቼ ሊሆን ይችላል። በየቀኑ ከሥራዬ በኋላ የውጭ ፊልም የማየት ልምድ ያለኝ ሆኖ አሁን በእነዚህ ሁለት ሶስቶች በመወሰኔ ጸጸት የለኝም! ይህ ማለት ግን የውጭውን ማየት ትቼያለሁ ማለት አይደለም! ልተው አልችልም!

ከጠቀሜታዎቹ አንዱ – ለምሣሌ ያህል፣ – ውጭ ሃገር ብዙ ዘመናት በመኖሬ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አዲስ አባባ ምን እንደምትመስል አላውቅም ብል ማጋነን አይደለም – በፈጣን ለውጧ ምክንያት! ነገር ግን አሁን ማየት በጀመርኳቸው እነዚህ የኢትዮጵያ ፊልሞች አማካይነት፡ አዲስ አበባ ምን እንደምትመስል የተሻለ ሥዕልና በፖለቲከኞች ያልተበከለ ግምት አግኝቻለሁ!

ከእነዚህም መካከል፣ ከተማዋ ያልተገራ ዘመናዊነትን ተላብሳለች – ከታላቁ ጦርነት በኋላ የነአበርኩርምቢ ፕላን (Sir Leslie Patrick Abercrombie) መሠረቷን ለአያሌ አሥርታት አላብሷት ሳለ፣ ሕወሃት ደግሞ ከ15 በላይ የፕላን ትርምሶችን ጭኖባት – አንዱም ልማትና ሰላምን ላያመጣላት – ለዛሬው ግራ መጋባቷና የመሬት ዘረፋዎች ምክንያት አድርጎባታል!

ስለሆነም፣ አዲስ አበባ ዛሬ ጥቂቶች ብቻ እንደከበሩና ብዙዎች እንደተገፉ መገመት የሚያስችል መሆኑ ነው። በዚህም አንድ ሌላ የተማርኩት ነገር በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ የተወሰኑ ግለሰቦችና ቤተሰቦች አኗኗርና ሕይወት ተለዋውጧል። የአዲስ አበባ ቤት አያያዝና ውስጡ ሁሉ የአንደኛ ደረጃ ዓለምን ምቾትና አኗኗር ከተፎካካሪነት አልፏል። እጅግ በተቃወሰ የሃብት ክፍፍል ምክንያት አዲስ አበባም ከዜጎች የኔነቷና መናገሻ ከተማነቷ ይልቅ የጥቂቶች ደሴት መሆኗን ማንም ከእነዚህ ፊልሞች በመሳቀቅ መመልከት ይችላል።

አዲስ አበባ እንደ ከተማ መስፋፋቷና የሕንጻዎቿ ብዛት በግልጽ ቢታይም፡ የወደፊቱ ሲታሰብ ግን ከልማት ይልቅ በዘፈቀደ የተስፋፋች መሆኗ፡ የነገዋ የነዋሪዎቿ የኑሮ ሸክም መሆኗን በቀላሉ ማየት ይቻላል። ይህ ማለት ለሕይወት አስፈላጊዎቹ ዋና ዋና መሠረተ ልማቶች ባለመተግበራቸው ከዛሬ ይልቅ፥ ነገ አዲስ አበባ በተባበሩት መንግሥታት ጥናት መሠረት የውሃ ጥማት ጭምር ወደፊት የሚጎዳት የአፍሪካ ከተማ መሆኗ ሲታሰብ የነገው ችግሮቿ ግዙፍና አሰፈሪ ናቸው!

ዛሬ መንገድና ሕንጻዎች እስካማሩ ድረስ ለሌላው ግድ የለም የተባለ ይመስል፡ ለምሣሌ ኋላ ቀር በመሆናችን የሕዝቡ ጤና አንዱ ችላ ከተባለበት፡ መንግሥትም በባሕሪው አድሎአዊ በመሆኑ፣ ከቤት ሲወጣ ከተማዋ ውስጥ መንገድ ላይ የሚቦነው አዋራ ለምን ሃገራችን በሣንባ ነቀርሣ ከ22ቱ ቀዳሚ ሃገሮች (22 high burden countries (HBCS)) አንዷ እንዳደረጋት ከፊልም ፊልም ሁኔታውን ያለስስት ያጋልጣል!

ክተለያዩ ፊልሞች እንዚህን ከተገነዘብኩ በኋላ ነው ‘የጥቁር ፈርጥን’ (Black Pearl – በእውነት ላይ የተመረኮዘ ታሪክ – (Sodere 2017 ምርት/ Addis Tesfa Entertainment and Director Addis Tesfa) በማየት ራሳቸውን ለኢትዮጵያ መከበር ያዋሉ እንደ መቶ አለቃ ሲራክ ዐይነት ዜጎች በንጹህ ኅሊና ለሃገራቸው ሲታገሉ አይቼ ዐይኔን በእምባ ለማባስ፣ ልቤም በኩራት እንድትሞላ ያደረገኝ!

ካለወትሮው አፋኙ ሕወሃት ይህ ፊልም ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ዝግጅቱ ተጠናቆ እንዲታይ መፍቀዱ አስገርሞኛል – ሕወሃት እንደመጣ የተፈጸም የሃገር ቅርስ ዘርፋ ታሪክ በመሆኑ – በወቅቱ የነበረው ሃሜታ ሕወሃቶች የሃገሪቱን ቅርስ እየዘረፉ በመቸርቸር ላይ ናቸው የሚል ነበርና! ሃሜታውን ለማክሰም ታስቦም ከሆነ፣ ከፊልሙ ላይ ምንም አይቀንስበትም።

ፊልሙ የተለያዩ ትምህርቶች ይሠጣል። ይህ ትክክል ከሆነ፣ ምናለበት እንደ ሃገርና እንደ ዜጎቸ – አንዱ ባለቤት ሌላውን ባዕድ ከማደረግ ይልቅ – የጋራ ሃሤቶቻችንን ብናዳብርና ይበልጥ የተሻለች ሃገር እንድትኖረን ፖለቲካው ሥነ ጥበብን ከማፈን የማይታቀበው! ከታሪክ እንደምንረዳው ከሆነ፣ ዘወትር አፍኖ፣ አሥሮና ገድሎ በሥልጣን የፈለገውን ያህል የሕዝብ ልብና መንፈስ ይዞ ለመዝለቅ የቻለ መንግሥት የለም!

ይህን ታሪክ ዘንግተው ያንን ለማሳካት የሞከሩት ሁሉ፣ ግባቸውን ሳያሳኩ ከሥልጣን ተወግደዋል! ሌሎችም ለፍርድ ቀርበው በእሥራት ላይ የሚገኙባቸው ሃገሮች ነበሩ። ዛሬም አሉ!

በሌላ አባባል ይኸው ሃሣብ ሲገለጽ፣ ታሪክና ውሰጠ ጥሩነት ያለውን ሕዝብ ማፈን ወደከፋ ደረጃ እንጂ ወደ መሻሻል መሸጋገር አያሰቻልም! አሁን እንደሚታየው (Human Development Index and environmental protection መለኪያ ሆኖ) የሃገሪቱ ማሽቆልቆል ደግሞ በትረ ሥልጣኑን ለጨበጡት የቀድሞ ‘ነጻ አውጭዎች’ የዛሬዎቹ የራሳቸውን ፕሮፓጋንዳ ያመኑትን ባለሥልጣኖችና ሃብታሞች አመቺ ሁኔታ አይፈጥርላቸውም!

ለምሣሌም ያህል፣ ክሼር ኢትዮጵያ ደች አበባ አምራቾች የዝዋይን ሐይቅ መበከልነ እያየ የጥቅም ተባባሪ የሆነ አስተዳደር፡ በቆዳ ፋብሪካዎች መስፋፋት ተሳክሮ ወንዞችን የበከለ መንግሥት አባቶቻችን ጦር ግንባር ዘምተው ያቆዩልንን ሃገር ለውጭ ምንዛሪ አሳልፎ መስጠቱ ሕወሃትን ለመጭ አያሌ ትውልዶች ተጠያቂ ያስደርግዋል!

ለጥቃቅን ዘላቂውን የሃገርን ደህንነትና ሏዓላዊነት የመቸርቸሩ ሁኔታ በተለያየ መንገድ እንደቀጠለ ነው!

ይህንን ፊልም ላዘጋጁት ደራሲያን ባለ ሕልሞች፡ ተዋንያን ተባባሪዎች ሁሉ ከልቤ የመነጨ ከፍተኛ ምሥጋናየን አቀርብላቸዋለሁ!
*Updated
 

%d bloggers like this: