የዓሣ ግማቱ ከአናቱ:                               የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የዘመነ ሕዋሃትን ባዶነት ያጋለጡበት ድምጽ!

30 Mar

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

 
መጋቢት ፲፰ ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም (ኢሳት ዜና):- ከወራት በፊት የህወሃት ኢሕአዴግ አገዛዝ በጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ ስብሰባ ላይ መመህራን የያዙት አቋም ካስደነገጠው በሁዋላ፣ ድጋሜ ጥልቅ ተሃድሶ እንዲካሄድ ባሳሰበው መሰረት በቅርቡ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች መምህራን ለብቻ ስራ አቁመው ውይይት ሲያካሂዱ ቢሰነብቱም፣ መምህራን ግን ቀደም ብሎ ያሳዩትን ጠንካራ አቋም አሁንም አሳይተዋል።

በጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረማርቆስ፣ ደብረታቦርና በሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በተካሄደው ስብሰባ መምህራን የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎት እንደሚገኝ ተናግረዋል።
“ሕዝቡ እያለቀ ነው፣ እያንዳንዱ አመራር ለሞቱት ኢትዮጵያውያን ተጠያቂ ነው” በማለት የተናገሩት ምሁራኑ፣ ኢህአዴግ በሚከተለው የመከፋፈልና የጥላቻ ፖሊሲ የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተከፋፍሎ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

“እንደ ኢሕአዴግ ዘመን ወጣት ያለቀበትን ዘመን አናስታውስም” ሲሉ ምሁራኑ ተናግረዋል።

ምሁራኑ “ የኢሕአዴግን አመራሮች የምናደንቀው ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ይህን ሰነድ አዘጋጅታችሁ ፣ የዩኒቨርስቲ ምሁራንን ሰብስባችሁ ለመቀለድ፣ ይህን ስነልቦና የሰጣችሁ፣ ይህን “ኮንፊደንስ” የሰጣችሁ፣ ይህን ድፍረት የሰጣችሁ፣ ይህን ሁሉ ፊት ተቋቁሞ ለማወያየት መቻላችሁ ነው።” በማለት በመድረክ መሪዎች ላይ ተሳልቀውባቸዋል።

እኛ የምንኖርበት አገርና ኢሕአዴግ የሚነገርን አገር የተለያዩ ናቸው ሲሉም ምሁራን ተገኘ የሚባለውን የኢኮኖሚ እድገት አጣጥለውታል፡፡ “በሚኒሊክና በነገስታቱ ዘመን የተሰሩት ድልድዮችና መንገዶች በጥንካሬ እናንተ ከሰራችሁዋቸው የተሻሉ፣ እስካሁን ድረስ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ፣ እናንተ የምትሰሩዋቸው መንገዶች በማግስት የሌሉ” ናቸው በማለት፣ በነገስታቱ ዘመን የተገኙት እመርታዎች፣ እናንተ ብትኮንኑዋቸውም፣ ከእናንተ የተሻሉ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

ኢህአዴግ ለመምህራኑ ባቀረበው ሰነዱ ላይ ሊጋቡ የማይችሉት ትምክህት እና ጠባብ በአንድነት ተጋብተው እየረበሹን ነው ብሏል፡፡

ምሁራኑ ስለመከላከያ ሰራዊት፣ በአንድ ብሄር ቁጥጥር ስር ስለሚገኘው ኢኮኖሚ እና ሌሎችም ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዮች እያነሱ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
 

%d bloggers like this: