የኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ትምህርት ይሁኑን! ሕወሃት የጣላቸው አርበኞቻችን ይከበሩ! ከሕግ ውጭ የሚረገጡት ዜጎቻችን ፍዳ ያብቃ!

10 Apr

በከፍያለው ገብረመድኅን Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
በሕይወት ዘመናቸው ከሃገር ጠላቶች ጋር 3,500 ዘማቾች አስከትለው በመፋለም – በአምስቱ ዓመታት የጣልያን ወረራ ወቅት አንዴም ሳይማረኩ – ከሞት ጋር ተፋጠው የኖሩ ሰው በመሆናቸው፣ ከዚያም በኋላ 17 ጊዜ በተለያዩ ጊዜያት ቀዶ ጥገና የተደረገላቸው ስለሆኑ፣ እንደገናም በተላኩባቸው የሃገር ሰላምና ደኅንነት ማስከበር ሥራ ከጠላት ጋር መፋለምን አልፈው፣ ከሰባት ዓመት በፊት በነበሩበት ሁኔታ ምን እንደተሰማቸው በሸገር ጋዜጠኛዋ ኅሊና አዘዘ ለተደረገላቸው ጥያቄ በ2010 የ89 ዓመቱ ‘የበጋው መብረቅ’ሌ/ጂነራል ጃገማ ኬሎ የሠጡት መልስ የሚከተለው ነበር:-


“እንግዲህ እግዚአብሄር የሠጠኝን ጸጋ በትዕትሥት ሕመሜን እየቻልኩ እየታገስኩ እሄዳለሁ፤ ምንም ችግር የለም፤ አሁን ደግሞ ሥቃይ የለም ዋናው ነገር – ከዚህ [እግሬ] ማንከስ በስተቀር -… እበላለሁ፤ እጠጣለሁ፤ ሌሊት እተኛለሁ! ፈጣሪዬን አመስግናለሁ!”

ሚያዝያ 9/2017 የሕወሃቱ ፋና ስለኢትዮጵያዊው ጀግና ሌ/ጄኔራል ጃገማ ኬሎ በ96 ዓመታቸው ሕይወታቸው ማለፉን ምክንያት በማድረግ የተዘገበው ዜና በዜናነቱ መቅረቡ ብቻ አስደስቶኛል።

ምክንያቱም ለሕወሃቶች ትግራዊ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ አርበኛ ይህን ያህልም መዘገቡ በእነዚህ 26 ዓመታት ያልተለመደ ነው። በአንድ በኩል ሃገራችን ባለውለታ ዜጎቿን የማከበርና የመንከባከብ ባህሉ የሌላት መሆኗ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ መሆኑኑ እየታወቀ፣ ይህ ዜና የተጠናቀረው ይባስ ብሎ በዘረኛው ዘመነ ሕወሃት የዘረኝነቱ ችግር ከምንጊዜውም በላይ በተጠናከረበት ወቅት ነው።

ከዚህ በታች የሠፈረው የጆሲ ቪዲዮ ጥር 15/2017 ዓ.ም. የተቀረጸ ሲሆን፡ መነሻውም የገናን በዓል ጄኔራሉ በተኙበት ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ውስጥ ስጦታዎችን በማበርከት ለማክበር የታቀደ የሚያስደስት የሚያሳዝንም ዝግጅት ነው።

ከአሳዛኙ ነገሮች መካከል፡ በሕይወታቸው ዘመን በተለይም በጡረታ ተገልለው በነበሩባቸው 36 ዓመታት – እርሳቸው ለሃገራቸው ካደረጉት አስተዋጾዖ አንጻር ለጤናቸው እንኳ እምብዛም እንዳልተደረገላቸው፣ ለአምስት ዓመታት አስታማሚያቸው የነበረችው የመጨረሻ ልጃቸው ምህረት ጃገማ ኬሎ የሚሰማትን ቅሬታ ከዚህ በታች ባለው ቪዲዮ ውስጥ በጨዋነት ታሰማለች!


 
በ1,398 ብር ጡረታ የአርበኞች ማኅበር ደግሞ ብር 600 እየከፈላቸው ከእጅ ወደ አፍ የኑሮ ትግል ሕይወት እንደመሩ የመጨረሻ ልጃቸው ቅሬታዋን በኩራት በመዋጥና ኃዘኗን የኅብረተሰባችንን ውድቀት በሚያሳይ መልክ – ማንንም ሳትወነጅል – አሰምታለች!

ድህነት ነውር አይደለም! ትልቁ የሃገራችን ነውር ግን ሃገራችን የልጆቿን ውለታ በልታ ልጆቿ ችግር ውስጥ እንኳ ሲወድቁ ጀርባዋን የምትሰጥ መሆኗ ነው።

ምነው ለጂነራል ጃገማ መንገድ ወይም ትምህርት ቤት ወዘተ በስማቸው አልተሰየምም ለሚለው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ እንደማይኖር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል! ለዚህ ነው የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ያለበት – በጎ ፈቃዱ ካለ – ፖሊሲውን በአስቸኳይ መቅረጽና አስፈላጊውን የመንግሥት ተቋም መመሥረት ያስፈልጋል!

ድርጊቱ ቀርቶ በምኞት ደረጃ እንኳ ሃገራችን ትልቅ ብትሆን፣ ዛሬም በዚህ በዘገየ ወቅት ጀግናው ጄኔራል ጃገማ ላይ ከደረሰው ትምህርት በመውሰድና የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ባለታሪክ አስተዋጽዖ በቅንነትና በሕጋዊ መመሪያነት ሃገሪቱ ወሮታ ለመክፈል እንድትችል ወደ ፖሊሲ መሸጋገሩ ግድ ይላል!

እስከ መቼ በግለሰብ ዜጎች ዕርዳታ፣ ጥቂቶች በጎ ፈቃድ የጎደላቸው በሕዝብና ሃገር ንብረት ፈላጭ፡ ቆራጭ ሆነው በዘረፋቸው በሚንደላቀቁባት ሃገር?

በሌላ በኩል፣ ሃገር አገልግለው በጡረታ የተገለሉ ግለሰቦች ልዩ አሰተዋጾዖች ታሳቢ አለመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፡ ዜጎች በኢትዮጵያ መብቶቻቸውን የተገፈፉ መሆናቸውን እናውቃለን፤ በምሬት ስንመሰክርም ኖረነናል! ይህ ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ እጅግ በማስቆጣቱ ላለፉት 16 ወራት የተነሳውን ገሃድ ግብግብና አሁን ደግሞ – ‘የጥልቅ ተሃድሶ’ ፖለቲካ ትያትሩ ቀርቶ – ውስጥ ለውስጥ የሚግመው ቁጣ ልብ ሊባል ይገባል!

ለምሣሌም ያህል፣ የሕግ እሥረኛ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ሆኖ ሲረገጥና ሲደበደብ እንዲሁም ሕክምና ሲከለከል፣ በሕይወት ያሉት የሕወሃት ባለሥልጣኖቻቸው፡ ዘመዶቻቸውና ጓደኞቻቸው በመንግሥት ወጭ ውጭ ሄደው እንዲታከሙ ሲደረግ፡ ለውጭ ፖለቲከኞች (ደቡብ ሱዳንና ሶማልያ) በመንግሥት ወጭ ቤቶች ተሠጥተዋቸው ተደላድለው እንዲኖሩ ሲደረግ የዜግነት ትርጉሙ ምን ይሆን?

በቅርቡም ሌሎች ዐይኖቻችንን ያስረጠቡ ሁኔታዎችን እናስታውሳለን። ለምሳሌም ያህል፦

  (ሀ) ለሃገራቸው በደማቸውና በውድ ሕይወቶቻቸው ዳር ድንበሮቻችን የዋጁ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ዛሬ በመንገድ ላይ ለማኝ እንዲሆኑ የተደረጉት ለቁጥሮቻቸው ማነጻጸሪያ የሚሆነው፥ እዚያ የደፋቀቸው የሕወሃት ክፋትና ተንኮል ጥልቀት ብቻ ነው። የሚገርመው ነገር ሃገር ላይ ባዕዳን ኃይሎችም ሆኑ የውስጥ ተጻራሪ ኃይሎች በሕውሃት ላይ ክንዳቸውን ሲያነሱ፡ ሕወሃት አሁንም ጭምር ለልመና ለዳረጋቸው የቀድሞ መከላከያ አባላት የእናት ሃገር ጥሪ ያቀርባል።

  (ለ) ብዙ የሃገር ጀግኖች ውጭ ሃገር ተሰደው ከርመው፡ ሬሣቸው ሃገራቸው መጥተው እንዲቀበሩ የሕወሃትን ፈቃድ ጠየቀው ለአፈራቸው የበቁት ቁጣራቸው ጥቂት አይደለም! ለአሜሪካ F-5E የጦር አውሮፕላን ታላቁ ማስታወቂያ የተሠራው – ኒውስዊክ እንደዘገበው – በ1970ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ሲሆን፣ ይህም የሆነው ብርቅዬ የሆኑት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዋጊዎች ባከናወኑት የአየር በአየር ውጊያ ጀግንነት ነበር። ስማቸው ከሚጠቁሱት መካከልም ብሔራዊ ጅግናው እነጄኔራል ለገሠ ተፈራ (የአየሩ ነብር) ጭምር ይጠቀሳሉ! በጋራም ሆነ ከጄነራል ተፈራ መማረክ በኋላ፥ የሶማልያን የመጨረሻዋን የጦር አውሮፕላን ደምስሰው ሶማልያ ሁለተኛ ኢትዮጵያን በአየር ኃይል እንዳትተናኮል ያደረጉት አብራሪ ጄኔራል ባጫ ሁንዴ ካሃገራቸው ርቀው ሬሳቸው እንኳ በ2015 የሃገራቸው መሬት ላይ ሳያርፍ ቀርቶ አሜሪካን ሃገር በካሊፎርኒያ ኦክላንድ ውስጥ ተቀብረዋል።

  (ሐ) እኔ በሥራም ሆነ በስም የማላውቃቸው አያሌ የቀድሞ ጦር አባሎችና ሲቪል ሃገር ወዳዶች ለሃገር ከፍተኛ መሥዋዕትነት ቢከፍሉም፡ አብዛኞቹም ምናልባት፡ ሃገራቸው በውስጧ ብታነባላቸውም እንደወጡ ቀርተዋል። ይህ መቆም አለበት! ሃገር የሁሉም ዜጎች ናት!

ምነው ሃገራችን የወላድ መካን ለመሆን ተገደደች? ይህ ዛሬ በኛም ሆነ በሃገራችን ሕዝብ ፊት ወንጀል ነው፤ በተለይም፡ የሕወሃት ሹማምንት ሥልጣን ስለተቀራመቱ – ብዙ ጥፋቶችንና ወንጀሎችንም ፈጽመው – በ$25 ሚልዮን የግል የሚሆኑ የጡረታ ዘመናዊ ቤቶች ሲሠራላቸውና ሃገሪቱም አይታ በማታውቀው መጠን የአንደኛው ዓለም ያህል ጡረታ እንዲከፈላቸው፡ የጤና ኢንሹራንስ ፖሊሲ ሲሠላላቸውና መኪናዎች ከነሾፈሮች እንዲመደቡላቸው የጡረታ መብቶቻቸው ሲደነገጉ – የጄኔራል ጃገማና ሌሎች መሰሎችን መጣል የታዘበ ዜጋ ‘ሃገሬ የቀበረሽ በላ …’ የሚለውን ቢያስታውስ ምን ያስደንቃል!

እውነቱን ለመናገር – ከላይ ከአጀማመሬ እንዳልኩት – ዛሬ በሕወሃቶች አንደበት ጂኔራል ጃገማ ኬሎን በዚህ የሕየውታቸው ዕልፈት ወቅት “በኢትዮጵያ ታሪክ ታላቅ ሥፍራ ያላቸው” – ፋና እንዳስቀመጠው – ተብሎ መዘገቡ በእውነትም ያንን አንጸባራቂ የጀግንነትና መሥዋዕትነት ትግል ታሪክ በመቀበል ይሆን፡ የፖለቲካ ጨዋታ መለየት አስቸጋሪ አድርጎታል።

ሕወሃት ሰብዓዊነት የሌልው ድርጅት ስለሆነ፡ ምናልባትም የሞተ ሰው አይመለስም በሚለው አባባል በመጽናናትም ሊሆን እንደሚችል አልጠፋኝም። ሆኖም በደፈናው ከመራገም፣ እኔም እስቲ ይሁን ብዬ ደስ ብሎኝ ዜናውን እሁድ ጠዋት ሚያዝያ 9/2017 አነበብኩት!

መሻሻላችሁን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በዚያ አስቀያሚ ‘ጥልቅ ተሃድሶ’ ቅጥፈት ሳይሆን፡ እስቲ ለአንዴ እንደ ‘መንግሥት’ ለመናገር፣ ለማስተዳደርና ሃገርንና የሕዝብን ሕይወት ለማሻሻል ፍላጎት እንዳደረባችሁ በተግባር አሳዩ!

ሁለት ጉዳዮችን ነው ያነሳሁት፦

  (ሀ) ሁሉንም ዜጎቻችንን በኢትዮጵያውያነታችው ብቻ አክብሯቸው

  (ለ) ለአርበኞቻችንና ለባለአስተዋጾ ከዋንያን ዜጎች ድራጎቶቻቸው ሕዝብ በከበሬታ መንግሥት መብት ላይ በተመሠረተ የወሮታ ክፍያ በሕግ ይክፈላቸው

  (ሐ) ሕወሃቶች በዜጎቻችን ላይ የምትፈጽሟቸውን አረመኔያዊ ተግባሮች አቁሙ፤ በእሥር ቤት በሕግ እሥረኞች ላይ የሚፈጸሙትን ማሠቃየቶችን ጭምር። ጠላቶቻችሁን አላቆማቸውም፡ እናንተንም ከመጠላት ውጭ ያተረፈላችሁ ነገር የለም። አሁን ባለው ሁኔታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሕወሃቶች ላይ የቁጣውን እሳት ለመለኮስ ቀን ጠባቂ ሆኗል ከደረሰበት ጥቃትና ዘረፋ በመነሳት – ምንም እንኳ ይህ ከታሪካችን ጋር የማይሄድ ባህሪ ቢሆንም!

ምናልባትም ሁኔታዎች ተለዋውጠው ሕወሃቶች እንደዜጋ ማሰብ ከቻሉ፡ በዚህ ረገድ የሚወጣውን ፖሊሲና ሕጎች ከጄኔራል ጃገማ ኬሎ ስም ጋር አያይዙት! ለሁሉም ነገር መንስዔ አለው!መሻሻልም በዚህ ምክንያት የምንፈልገው ለውጥ ሊመጣ ይችላል።

ጎሲ እግዚአብሔር ውለታህን በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ይከፈልህ፡ ከበሬታህ ይብዛ ይዳብር!
 

%d bloggers like this: