ESAT News! ኢሣት ዜና! የድርቅና በሽታ መስፋፋት በኢትዮጵያ፤ በአማራ ክልል ከ50ሺ በላይ እሥረኞች ያለፍርድ ለዓመታት መታጎር

21 Apr

በምቾት ውልውል ያሉት ኮሚሽነሩ ምትኩ ካሳ (Fana Credit)

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

ኢትዮጵያውያንን በየአካባቢው ርሃብ እየቆላቸው ቢሆንም፣ ይህንን ችግር ለመፍታት በኃላፊነት የተሰየሙት ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ – ከወገን መርገፍ በላይ የራሳቸውን ተቀባይነት ለማስፋፋት– “ሃገሪቱ በዋናነት በራስ አቅም የድርቅ አደጋን እየተቋቋመች መሆኗ” ትልቅ ስኬት እንደሆነ መናገራቸውን ዛሬ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በድርቅና ርሃብ የተገረፉ ዜጎች ወደ የአካባቢው በመፍለስ ላይ ናችው። ያልቻሉትም በየአካባቢያቸው ተደፍተው ቀናቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው –ከእዚህ በታች የቀረበው የዜና ቪዲዮ እንደሚያስረዳው! ይርጋ ዓለም ተወለድኩ የሚሉት አቶ ምትኩ ካሣ፡ ከሁሉም በላይ በሕወሃት አባልነታቸው ይኩራራሉ – የወገኖቻቸውን መርገፍ እስኪክዱ ድረስ!
 

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሀገሪቱ በዋናነት በራስ አቅም የድርቅ አደጋን እየተቋቋመች መሆኗ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነሩ ምትኩ ካሳ ተናገሩ፡፡

በድርቁ የተጎዱ ወገኖችን ለመታደግም መንግስት የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ በየወሩ ምግብና ምግብ ነክ እርዳታ ሳይቆራረጥ እየሰጠ እንደሆነ አቶ ምትኩ ገልፀዋል፡፡

ሆኖም ከችግሩ ስፋት አንፃር በራስ አቅም መንግስት ከሚሰራው የእርዳታ ስራ ጎን ለጎን የውጭ የረድኤት ተቋማትና የአለም አገራት የሚያደርጉት ድጋፍ አናሳ በመሆኑ ድጋፋቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

ኮሚሽነሩ በያዝነው ዓመት ጥር ወር ላይ መንግስት የድርቅ አደጋውን ለመታደግ 948 ሚሊዮን ዶላር የውጭ እርዳታ ያስፈልጋል ቢልም 93 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መገኘቱን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የአየር መዛባት ክስተትን ተከትሎ በሀገሪቱ በተፈጠረው የድርቅ አደጋ የአንድም ሰው ህይወት ሳያልፍ እርዳታ እየተሰጠ መሆኑ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ድርቁ የተከሰተው በደቡብና በደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ሲሆን፥ በቀጣይ ድርቁን ለመቋቋም ዘላቂ የልማት ማዕቀፍ ስራዎችን ማዕከል ተደርጎ መሰራት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ፣ የመስኖ ልማት፣ የውሃ ማቀብ እና የደን ልማት ስራዎች እንዲሁም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት አጠናክሮ የማስቀጠል ስራዎች በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚተገበሩ ነው ያመላከቱት ኮሚሽነሩ፡፡

ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ተጎጂ ወገኖችን ለመታደግ መንግስት 100 ሚሊየን ዶላር ገደማ ወጪ ማድረጉን ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
===============
 

የተቅማጥ (አተት በሽታ) በመላ አገሪቱ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል

ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም (ኢሳት ዜና):- በአገሪቱ ከሚታየው ድርቅና የንጽህና ጉድለት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ከፍተኛ ስጋር ፈጥሯል። በአዲስ አበባ የበሽታው ስርጭት እየቀነሰ ነው ቢባልም፣ በዚህ ሳምንት ብቻ 25 በሽተኞች ህክምና ማግኘታቸውን ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአማራ ክልል በ21 ወረዳዎች ፣ በትግራይ 5 ወረዳዎች ፣ በኦሮሚያ 16 ወረዳዎች ፣ በደቡብ 12 ወረዳዎች ፣ በኢትዮጵያ ሶማሊ 12 ወረዳዎችና በአፋር 3 ወረዳዎች በያዝነው ሳምንት በሽታው በስፋት ተሰራጭቷል። በሽታው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ መከሰቱ ነው። በሶማሊ ክልል በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በበሽታው ህይወታቸው ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል።

በሌላ ዜና ደግሞ በኢትዮጵያ ኦጋዴን አካባቢ ነዋሪዎች ድርቁ ባስከተለው ረሃብ ምክንያት እንስሶቻቸው በማለቃቸው መኖሪያ ቀያቸውን በመተው እየፈለሱ መሆኑን የረድኤት ድርጅቶች አስታውቀዋል። አርብቶ አደሮቹ በምግብ እና ውሃ እጥረት ክፉኛ በመጎዳታቸው ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉ ወደ መጠለያ ካንፖች አመርተዋል።

የ82 ዓመቱ አዛውንት አቶ አብዱከሪም ”አሁን አካባቢያችን በከፍተኛ ድርቅ ተጠቷዋል። እኔ በእድሜዬ እንደዚህ ዓይነት ርሃብ አይቼ አላውቅም’ ብለዋል። የዓለም ሕጻናት አድን ድርጅት (Save the Children) የሰብዓዊ ጉዳዮች ዳሬክተር የሆኑት ቻርሊ ማሶን በበኩላቸው ”አብዛሃኞቹ የቤት እንሳስቶቻቸው ሞተውባቸዋል። የቀሩዋቸውን እንስሣት ሕይወት ለማትረፍ ሲሉ ያላቸውን ጥቂት ገንዘብ እያፈሰሱ ነው። እነዚህ ሁሉ ሁለመናቸውን ያጡ ዜጎች በመንግስት አስፈላጊውን የምግብ እና የውሃ እርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል” ሲሉ ተማጽኖዋቸውን አሰምተዋል።

በምስራቅ ኢትዮጵያ በድርቁ ምክንያት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋቸው የሚተመን የቤት እንስሳት አልቀዋል። በአሁኑ ወቅት ከ5.6 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ጠባቂዎች ሲሆኑ፣ይህ ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል ሲል ዩኒሴፍ አስጠንቅቋል። በምስራቅ እና ደቡብ ኢትዮጵያ በድርቅ ለተጠቁ አካባቢዎች እርዳታ የሚውል በዚህ ዓመት ብቻ 948 ሚሊዮን ዶላር ቢያስፈልግም እስካሁን ግን የተገኘው 23.7 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።

የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ዳሬክተር የሆኑት ኤድዋርድ ብራውን በበኩላቸው ”ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በመንግስት እና እረድኤት ድርጅቶች የተሰጠው ምላሽ ሰፊ ክፍተት አለው። በርሃብ የተጎዱ ዜጎችን ሕይወት በአፋጣኝ ለመታደግ ከተመድ እና የአሜሪካ መንግስት አፋጣኝ እርዳታ ያስፈልጋል።” ብለዋል።

በአገር ውስጥ ብቻ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ 400 ሽህ ኢትዮጵያዊያን የሚውሉ 222 ጊዜያዊ መጠለያዎች በዓለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ተዘጋጅተዋል። በመጠለያዎቹ ውስጥ ከተጠለሉት መካከል 44 በመቶ የሚሆኑት በቂ ምግብ የማያገኙ ሲሆን 31 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከ20 ደቂቃ ጉዞ በኋላ በእግር ተጉዘው ውሃ ያገኛሉ።

አንድ ከፍተኛ የረድኤት ሰራተኛ በአካባቢው የተፈጠረውን ረሃብ ሲገልጸው፣ ”ያላቸውን ጥሪቶች በማውጣት ሕይወታቸውን ለማትረፍ የቻሉትን አድርገዋል። አሁን ግን ምንም ዓይነት ነገር የላቸውም” ሲል የሰብዓዊ ቀውሱ የከፋ መሆኑን አስረድቷል። በምስራቃዊ ደቡብ ኢትዮጵያ ከዶሎ አዶ ከተማ 70 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የሚገኙት መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ከ650 በላይ ቤተሰቦች ምንም ዓይነት እርዳታ እንዳልደረሳቸውም አክሎ ገልጿል።

በምስራቅ እና ደቡብ ኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የቤት እንሳሳት ከመሞታቸው በተጨማሪ ያሉትም ቆዳቸው በላያቸው ላይ የተጣበቀ የመሞቻ ጊዜያቸውን የሚጠባበቁ ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት እና ዓለምአቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ሰብዓዊ ቀውሱ በሰው እና በቤት እንሳስት ሕይወት ላይ የከፋ ቀውስ ከማስከተሉ በፊት በአፋጣኝ ሕይወት የማዳን ሥራዎችን ላይ ሊሳተፉ ይገባል ሲል ኢርኒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
===============
 

በአማራ ክልል ብቻ ከ66 ሺ በላይ ዜጎች በማረሚያ ቤት ውስጥ ይገኛሉ

ሚያዝያ ፲፪ ፪፲፻፱ ዓ/ም (ኢሳት ዜና):- የክልሉ ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እንዳስታወቀው በክልሉ 66 ሽህ 102 ዜጎች በፍርድ እና ያለፍርድ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ። በክልሉ የእስረኛው ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ በመሄዱ የክልሉ ባለስልጣናት መፍትሄ እንዲሰጡበት ጠይቋል። እስረኞቹን ለማስተናገድ የተበጀተው በጀት ማለቁንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

እስረኞቹ በአማካኝ ከ5 እስከ 10 ዓመታት በፍርድ ወይም ያለፍርድ በእስር እንደሚማቅቁ የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ክልሉ ለ 22 ሺ 26 እስረኞች በቀን 9 ብር በድምሩ 203 ሺ 139 ብር፣ በአመት ደግሞ 73 ሚሊዮን 130 ሺ 40 ብር ወጪ ቢያደርግም፣ አሁን የእስረኞች ቁጥር በ3 እጥፍ በመጨመሩ ለማስተናገድ አለመቻሉን የክልሉ የማረሚያ ቤት ኮሚሽን ገልጿል፡፡

የክልሉ ማረሚያ ቤት ለእስረኞች ህክምና ያወጣውን 2 ሚሊዮን 246 ሺ ብር ለመክፈል አልቻለም። የሁለት አመት ውዝፍ የህክምና ወጪ ለመክፈል ባለመቻሉም የጤና ተቋማት ለማስተናገድ ፈቃደኛ አንሆንም እያሉት መሆኑንም ገልጿል።

እያንዳንዱ እስረኛ በአማካኝ 5 ዓመት በእስር ቤት ቢቆይ በጠቅላላው 1 ቢሊዮን 365 ሚሊዮን ፣ 200 ሺ ብር ምንም እሴት በማይጨምር ነገር ላይ ወጪ የደረጋል በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ገልጿል።
የእስረኞች ቁጥር በአንዴ ያሻቀበው በ2008 ዓም የታየውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ያለምንም የፍርድ ውሳኔ የታሰሩ ወጣቶች መበራከታቸውን ተከትሎ ነው።

ይህ አሃዝ በማረሚያ ቤት አስተዳደር ስር የሚገኙ እስረኞችን እንጅ በየወረዳው እና በየቀበሌው ታስረው የሚገኙትን ዜጎች ቁጥር አያካትትም። በክልሉ በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ለአመት፣ ለወራት ወይም ለሳምንታት የሚታሰሩት እስረኞች ቁጥር ቢደመር በክልሉ የሚገኘው እስረኛ ቁጥር ከተጠቀሰው በብዙ እጅ ይልቃል።

በአማራ ክልል ያለውን የእስረኞች ቁጥር ግምት ውስጥ በማስገባት በመላ አገሪቱ በሚገኙ ህጋዊ በሚባሉ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች እንደሚኖሩ ዘጋቢያችን አስተያየቱን አሰፍሯል።
 

%d bloggers like this: