የጋምቤላ ሙስና ደረጃ በዛሬው ዜና ሲታይ፣ ለሕግ የሚገዛ አስተዳደር የሌላት ኢትዮጵያ ሃገሪቷን በየደረጃው ‘መረን የለሿ ምዕራብ’ – (Wild West) አድርጓታል!

23 Apr

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
በጋምቤላ ክልል ተገቢ ያልሆነ የኢንቨስትመንት ፍቃድና የመሬት ካርታ በመስጠት ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ያፈሩ ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው
 
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 13 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ከ28 በላይ ለሆኑ ባለሃብቶች ተገቢ ያልሆነ የኢንቨስትመንት ፍቃድና የመሬት ካርታ በመስጠትና በባንክ ካዝናቸው ምንጩ ያልታወቀ ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ሃብት ያፈሩ ከ25 በላይ ሰራተኛ እና ሃላፊዎች ላይ ክስ ተመሰረተ።

በጋምቤላ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት የቀረበው ክስ፥ የክልሉ የመሬት አስተዳደር ባለስልጣን፣ የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ እንዲሁም በሕገወጥ ተግባሩ አገናኝ የነበሩ ደላሎች ላይ የተመሰረተ ነው።

የክልሉ ስነ ምግባርና ጸረሙስና ኮሚሽን አቃቢ ሕግ ክስ እንደሚያመላክተው ተከሳሾቹ ድርጊቱን የፈጸሙት ከ2005 እስከ 2009 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ነው።

በዚህ መልኩም በክልሉ ለ13 ባለሃብቶች ተገቢ ያልሆነ የመሬት ካርታ ሰጥተዋል የተባሉት የክልሉ መሬት አስተዳደር ባለስልጣን የካርታ ባለሙያ አቶ ሃይለማርያም በሃይሉ፣ ለአራት ባለሃብቶች ካርታ ሰጥተዋል የተባሉት የባለስልጣኑ የዳታ ሲስተም ባለሙያ አቶ አበራ ምርከናን ጨምሮ አራት ባለሙያዎች በአጠቃላይ 18 የመሬት ካርታ በሕገወጥ መልኩ መስጠታቸው በክሱ ተጠቅሷል።

በተመሳሳይም የኢንቨስትመንት ፍቃድ ካለምዝገባ ከአሰራር ውጪ ሰጥተዋል የተባሉት የክልሉ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡጁሉ ኒጎ፣ የኤጀንሲው የፍቃድ ዘርፍ የስራ ሂደት ባለቤትና የስራ አስኪያጁ ተወካይ አቶ ኡኪያ ቲያንግ እና የፍቃድ ዘርፍ የስራ ሂደት ባለቤት የሆኑት አቶ ሳምሶን ዳክን ጨምሮ አምስት ሰራተኞች በድርጊቱ ተሳትፈዋል ነው የተባለው።

ግለሰቦቹ እያንዳንዳቸው ከሁለት በላይ ሕገወጥ ፈቃድ መስጠታቸውና ከጋምቤላ ክልል ውጪ በደቡብ ክልል የተካለለ ተጨማሪ ካሬ ሜትር ይዞታን መስጠታቸውም በክዙ ተዘርዝሯል።

በክሱ በዚህ ህገ ወጥ ተግባር የተሳተፉ 11 ደላሎችም ተካተዋል።

በተጨማሪም በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን የመሬት አስተዳደር የፍቃድ ዘርፍ የስራ ሂደት አቶ ሳሀሊ ብዛን ጨምሮ ስድስት የመሬት አስተዳደሩ ባለሙያዎችና ስድስት ግለሰቦች በጎደሬ ወረዳ በህገወጥ አሰራር ለተለያዩ ባለሃብቶች መሬት በመስጠት ተሳትፈዋል ተብሏል።

በዚህ መልኩ በተፈጸመ ሕገወጥ ሂደት በአጠቃላይ የመንግስት ሰራተኞቹን ጨምሮ ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ምንጩ ያልታወቀ ሃብት በማፍራት በካዝናቸው መገኘቱን አቃቢ ሕግ በክሱ ጠቅሷል።

ተከሳሾቹ በጋምቤላ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሶስት ክስ ማለትም ምንጩ ያልታወቀ ሃብት በማፍራት፣ የኢንቨስትመንት ፍቃድ በመስጠትና የመሬት ካርታ በመስጠት የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

የፊታችን ሰኞ ሚያዚያ 16 ቀን 2009 ዓ.ም ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ ተነቦ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጣል።

በዚህ ተግባር ዋና ተዋናዮች ናቸው የተባሉ ስድስት ባለሃብቶች እና ስድስት ደላሎች ጉዳይ በፖሊስ ተይዞ እየተጣራ ነው።
 

%d bloggers like this: