ለአፈር ምርመራ የሚያገለግሉ ከ30 በላይ ማሽኖችን ተቋሙ ከ15 ዓመታት በላይ ያለ ሥራ አስቀምጧቸዋል

4 May

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 26 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ዋጋቸው በሚሊየን ብሮች የሚገመትና ለአፈር ምርመራ የሚያገለግሉ ከ30 በላይ ማሽኖችን ከ15 ዓመታት በላይ ያለ ስራ አስቀምጧቸዋል።

ጉርድ ሾላ በሚገኘው የመብራት ሀይል ግቢ ውስጥ በላሜራ ቆርቆሮ የተሸፈኑ ከ30 በላይ ግዙፍ ማሽኖች ያለምንም ስራ ተከማችተው መቀመጣቸውን ባደረግነው ቅኝት መታዘብ ችለናል።

ማሽኖቹ ለኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ከውጭ ሃገር በእርዳታ የተሰጡ የአፈር መመርመሪያ ማሽኖች ሲሆኑ፥ በሚሊየን ብሮች ዋጋ ወጥቶባቸው ላለፉት 15 አመታት ያለሥራ የተቀመጡ ናቸው።

የመንግስት ንብረት አስተዳደር መመሪያ የመንግስትን ንብረት ዘመናዊ በሆነ መልኩ መያዝ፣ መጠበቅ እና መጠቀም፤ ይህ ውጤታማ ሳይሆን ሲቀርም እንዲወገድ ማድረግ እንደሚገባ በግልጽ ደንግጓል።

ይህ ድንጋጌ ግን በተቋሙ እየተተገበረ አይደለም።

የመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የንብረት ማስወገድ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ዓይንይማር፥ ተቋማችው ይህንን ማረጋገጡን ይናገራሉ።

በተቋሙ ከመሬት መመርመሪያ ማሽኖች በተጨማሪም፥ ስምንት የጋራዥ አገልግሎት የሚሰጡ ማሽኖችም ለ15 ዓመታት ያለ ጥቅም ተቀምጠው ይታያሉ።

ኬፈደራል ዋና ኦዲተር የተገኘው መረጃም መስሪያ ቤቱ ይህንን ማረጋገጡን ያሳያል።

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ገብረስላሴ፥ ማሽኖቹ ረዘም ያለ ጊዜ የቆዩ መሆናቸውን ያነሳሉ።

ከዚህ ቀደም በ2006 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ደግሞ፥ ወደ ስራ ያልገቡት ማሽኖች ወደ ስራ እንዲገቡ ያገለግሉትም በተገቢው መንገድ እንዲወገዱ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ይሁን እንጅ ተቋሙ ይህን ማስጠንቀቂያ ሳይተገብረው ቆይቷል፤ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ማስረሻም ማሽኖቹ በአቅም ማነስ ምክንያት ጥቅም ላይ አልዋሉም ይላሉ።

የመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ንብረት ማስወገድ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን፥ ተቋሙ እነዚህን ማሽኖች ከብክነት ለመታደግ በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገባ ትእዛዝ እንደተሰጠው ገልጸዋል።

ወደ ስራ የሚገቡትን ማስገባትና ለሌላ ተቋም መተላለፍ ያለባቸውን በማስተላለፍ የሃብት ብክነቱን እንዲያስወገድም ትዕዛዝ ተላልፏል።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ መሳሪያዎቹን በተቀመጠው ጊዜ መሰረት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ወደ ስራ ለማስገባት እየሰራን ነው ብለዋል።

በዚህ መልኩ ማሽኖቹ ወደ አገልግሎት እንዲገቡና አገልግሎት የማይሰጡትን ደግሞ እንዲወገዱም ተብሏል።
 

%d bloggers like this: