ሆ! ሆ! ሆ! በኢትዮጵያና በሳዑዲ አረቢያ መካከል የሠራተኛ ስምሪት ስምምነት ተፈረመ! ፈቃድ የሌላቸው አብዛኞ ዜጎች መመለስ እንደማይሹ ይሰማል!

26 May

የአዘጋጁ ቅሬታ

  የሕወሃት ባለሥልጣኖች ስለሳኡዲ-ኢትዮጵያ አዲስ ስምምነት ይህንን ሰሞን ሲደሰኩሩ ይሰማል። ይኽውም አፍንጫቸውን ተይዘው (እነርሱ እንደሚሉት ደግሞ ለዜጎቻችን ተቆርቁረው) በሳውዲ ነባርና ግትር አቋም ላይ ተስማምተው ጀብዱና የዜጎችን መብት የሚያሰክር ሙያ እንደሠሩ ነው የሚናገሩት በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተሩን ላዳመጠ!

  ‘በፈጣን የዕድገት ጎዳና’ ላይ የምትገኘው ሕወሃቶች የሚመዘብሯት ኢትዮጵያ ግን፣ ሕወሃት — ትራምፕ ሳውዲዎቹን ሲያቅፍ በማየታቸው — እምቢ ሲሉ የኖሩትን አንፈርምም ያሉትን ስምምነት ተፈራረምን ብለው ሲደሰኩሩ መስማቱ ያማል። ወደ መቶ ሺ የሚጠጉትንና ገና ሃገር ለቀው የሚሰደዱትን ወጣቶቻችን ጭምር ለሳኡዲዎቹ ግርድና ስምምነት አሳልፈው ሠጥተዋል ማለት ነው!

  ልዩነቱ ተጠያቂነቱ ለአስቀጣሪ ድርጅቶችም በመጠኑ ተላልፏል — ዜጎቻችን በሰብዓዊነታቸው ባለመብት መሆናቸው ተቀባይነት ሳይኖረው ማለት ነው!

  አሁን አሁን እንዳለው የተስማሙት፣ አንደኛ ሳኡዲዎቹ የፈለጉት የነበረውን ነገር ነው — ባርነቱ እንዲቀጥል ማለት ነው። ሁለተኛ አሁንም ሠራተኛይቱ ከአሠራዊዋ ጋር ባትስማማ፡ ከሥራዋ መሰናበት አንዳትችል፡ እንደ ደረሰች ፓስፖርቷን ተነጥቃ በአሠሪዋ እጅ ይቆያል፡፡ ይህንን የዓለም የሠራተኛና ሥራ ድርጅት (ILO) እንደ ዘመናዊ ባርነት ብቻ ሣይሆን የሠራተኛዋን ሰብዓዊ መብት የሚጥስ ነው ማለቱ ይታወሳል።

  የተሻሻለው የሳኡዲ የሠራተኛ ሕግና (Ministerial Decision No. 1982) አፈጻጸም (6 April 2016) ፓስፖርት መያዝ ቀርቷል ቢልም — በሠራተኛዋ ፈቃድ ብቻ በሚል ሃረግ እንዲቀጥል መደረጉ ሊሉ ይገባል! በተሻሻለው ሕግ የቅጥር ስምምነቱ በአረብኛ ብቻ ሣይሆን በተቀጣሪዋም ቋንቋ እንደሚሰጥ ይደነግጋል።

  ልብ መባል ያለበት፥ ይህ ሕግ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት በሚያዝያ 2016 ከመውጣቱ በፊት ቀደም ብሎ የሳቁዲ መንግሥት ፓስፖርት በሚይዙ አሠሪዎች ላይ 2,000 የሳኡዲ ሪያል መቀጫ ጥሎ እንደነበርም ሊታወስ ይገባል!

  ደሞዝ አለመክፈለም መቀጫ እንደሚያስጥል የሳኡዲ መንግሥት ከደነገገ ስንበት ቢልም፡ እነዚህ ችግሮች በዜጎቻችን ላይ ለምን በ2017 እንደደረሱ ትዝ ይበለን!

  ሕወሃት ተስማምቶ የመጣው ዜጎቻችን ጉልበታቸውን እንዲሸጡ ስምምነት ስትፈራረሙ፣ወርቅነህ ገበየሁ ምንነው ፓስፖርታቸውን ተነጥቀው ለአሠሪዎቹ እንዳይሰጥ ይደረግ ያለውን እንኳ ማስከበር ሳትችሉ፡ አሁን የተቆርቋሪነታችሁንና አስመሳይነታችሁን ለኢትዮጵያና ሕዝብ ስትቸረችሩ ትንሽ ሃፍረት አይሰማችሁም? ስምምነቱ “ኢትዮጵያውኑ በአሠሪዎቻቸው በደል ቢደርስባቸው በሕግ አግባብ መብታቸውን ማስከበር እንደሚችሉ የሚደነግግ ” የሚያሰኘው ምኑ ነው?

  ዳሩ ግን ቅጥፈት የዘረፋ መሣሪያችሁ ቅሌትንም የሙያ ብቃታችሁ መለኪያ ማድረጋችሁ ሲነገር ሰንበት ብሏል!

  በሰበብ አስባቡ ለሕወሃት ባለሥልጣኖችና ለትግራይ ልማት ከሚውለው የተረፈው ሃገር ለማልማት ስለማይበቃ፡ ወጥቱ ትውልድ በዕጦቶች ተመናምኖ ዕድል ፈንታውን — በተለይም ወጣት ሴቶቻችን —የአረቦች መጫወቻ ተደርገዋል። ይህም ዕድሜ ለሆዳሙ ሕወሃት የዜጎች ሁሉ ውርደት ሆኖአል!በሃገራችን የመንግሥት በጀት ተብሎ በሕግና ደንብ ይጸድቃል። በተጨባጭ እስከምናውቀው ድረስ፡ ይህ ለሕወሃት የንግድ ድርጅቶች የጥጃ ሣር ሆኖ ከርሟል። ሃገሪቱ እንድታድግና እንድትለማ የሚያስፈልጋት መሰል ገንዘብ ግን ከውጭ ዕርዳታና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የቴክኒክ ተራድዖ ይጠየቃል፡ ይለመናል። ጥቂት የምትገኘውም ለባለሥልጣኖች መኪናና ቢሮዎች ማድመቂያ ከዋለ በኋላ፡ ተራፊው ቅድሚያ የትግራይ መሆኑ አልጠፋንም!

  ታዲያ በሥነ ሥርዓት ጥጃዋ ላሚቷም አተላ በሚቀብላት ሃገር፡ ወጣቱ ሥራ አጡ እያላችሁ የምታላዝኑለት፡ በስሙ ገንዘብ እየሰበሰባችሁ ቪላዎቻችሁን በምታሠሩባት ሃገር፡ ምን ተስፋ እንዲኖረውው ነው ፊቱን/ቷን ሕወሃት ወደሚረጋግጣት ሃገር የሚጣረው? ወይንስ እንዳለፈው ጊዜ ለተመላሾች ሳኡዲዎች የአውሮፕላን ወጭ ከፍለው አስመጥተዋቸው ገንዘቡን እንደበላችሁ፡ አሁን የሳኡዲን ዕርጥባት ሕወሃት ፈልጎ ይሆን?

 
Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

Credit Fana

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለረዥም ጊዜያት ድርድር ሲካሄድበት የቆየው የሠራተኛ ስምሪት ስምምነት በኢትዮጵያ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና በሳዑዲ አረቢያው አቻው መካከል ትናንት በጄዳ ከተማ መፈረሙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች በሁለቱም ሀገራት ፈቃድ በተሰጣቸው የስራ ስምሪት ኤጄንሲዎች አማካኝነት በሚፈፀም ውል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተሠማርተው መሥራት ይችላሉ።

ስምምነቱ ኢትዮጵያውያኑ በአሠሪዎቻቸው በደል ቢደርስባቸው በሕግ አግባብ መብታቸውን ማስከበር እንደሚችሉ የሚደነግግ ሲሆን፥ በህገወጥ መንገድ ከሀገራቸው ወጥተው ከፍተኛ ችግር ላይ እንዳይወድቁም ያግዛቸዋል ተብሏል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በሳዑዲ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ኢትዮጵውያን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ዙሪያ ከሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አደል አል-ጁበር ጋር ሪያድ ላይ ተገናኝተው ተወያይተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያለ ህጋዊ መኖሪያ እና ስራ ፈቃድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከቅጣት ነጻ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ በመፈቀዱ የሳዑዲ አረቢያን መንግስት አመስግነዋል።

ኢትዮጵያውያኑን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ሰብዓዊ ክብራቸውና መብታቸው ተከብሮ ያፈሩት ንብረት ተጠብቆ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የሳዑዲ መንግስት የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግም ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።

ዜጎችን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የሚፈጠሩ እንቅፋቶችን ለማስወገድ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ነው የጠየቁት።

የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አደል አል-ጁበር በበኩላቸው፥ በህገወጥ መንገድ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መንግስት ያወጣውን የእፎይታ ጊዜ በማክበር ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል፡፡

የሳዑዲ አረቢያ መንግስትም፣ ኢትዮጵያውያን ያለምንም እንግልት ወደሃገራቸው እንዲመለሱ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ለንጉሱ የተላከ ደብዳቤንም አድርሰዋል።
 

%d bloggers like this: