ትልቁ የኢትዮጵያ ‘ፌደራል’ በጀት ድክመቱ፣ገጽታዎቹና ውስብስብ ችግሮቹ

21 Jun

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)
 
ለኢትዮጵያ አስተዳደራዊ ሥራ ማስፈጸሚያ በከፍተኛነቱ የመጀመሪያው የሆነውና በ2010 ዓ.ም (2017/18) ተግባራዊ የሚሆነው ብሔራዊ በጀት ብር 320.8 ቢሊዮን ($14 ቢሊዮን) የተመደበለት መሆኑን የፋይናንስና ኤኮኖሚ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ የፓርቲያቸው ብቻ ለሆነው ፓርላማ ለወጉ ረቂቁን እንዲያጸድቅ ሰኔ 1/2009 ማቅረባቸው በሕዝብ መገናኛ ተገልጿል።

የራሱ ውስጣዊ ችግሮቹ እንዳሉ ሆነው፡ ከሕዝባዊው አመጽ ወዲህ የመጀመሪያው የሆነው ይህ በጀት፡ በሕዝብ ቁጣ ወላፈን መለብለቡን በብዙ መልኩ ያሳያል። በተለይም ዛሬ ኤኮኖሚው ካጋጠመው የገንዘብ ችግሮች፣ የዕዳ ጫና፥ የምርቶች መቀነስና፣ የዋጋ ግሽበት አደጋ የኤኮኖሚው ማሽቆልቆ ከድህነት መስፋፋት ሁኔታ፣ ዜጎች በየጊዜው በሚታፈኑባትና ያለፍርድ በሚታሥሩባት እንዲሁም የሃገሪቱ ሰላም በአፈሙዝ ከሚጠበቅበት አንጻር ሲታይ — የበጀቱ አዘጋጆች በዚህ ትንተና ባይስማሙም — እነዚህ ከሃገሪቱ ፊት የተጋረጡ እውነታዎች ናቸው።

ለማንኛውም፡ ዘንድሮም በየዓመቱ በጀቱ በሚቀርብበት ወቅት እንደሚባለው ሁሉ፣ የ2010 በጀት ቅድሚያ ትኩረቶች — ትምህርት፣ የመንገድ ሥራ፣ ግብርና፣ የውሃና የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ የጤናና የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራሞች — እንደሚሆኑ ለፓርላማው በፋይናንስ ሚኒስትሩ ተገልጿል።
 

በጀቱ በቅርበት ሲታይ

የፋይናንስ ሚኒስትሩ ለፓርላማ ባቀረቡት መረጃ መሠረት፥ በጀቱን ከሃገር ውስጥ በሚሰበሰብ መንግሥታዊ ገቢ ለመሸፈን ታስቦ የተደረገው ጥረት ያስገኘው ውጤት አመርቂ ባለመሆኑ፣ የካፒታል ወጪዎችን ለመሸፈን የታቀደው “ከሀገር ውስጥ ከሚሰበሰብ ገቢና ከውጭ ሀገር በሚገኝ ዕርዳታና ብድር ነው” ይላሉ። ይህም እንደሚከተለው እንደሚሆን ለፓርላማው ተገልጿል፦ ከመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ (80.3 ቢሊዮን ፣ ከዕርዳታ (14.3 ቢሊዮን)ንና ከብድር የ20.2 ቢሊየን ብር ነው።

የአሁኑ በጀት ረቂቅ የብሩ ዕድገት የኤኮኖሚውን ደርዝ መስፋት የሚያመለክት በሆነና እንዴት በተደሰትን! ነገር ግን በተለይም ባለፉት ቅርብ ዓመታት አስተዳደሩ ይሰበስብ የነበረው ገቢ (State Revenue: ከግብር፥ ከታክስ፥ ከሽያጮችና የግምጃ ቤት ሰነድ (Treasury Bills)፣ ሎተሪ ትኬት፣ ንብረት፣ መቀጫ፣ ወዘተ፣ ከአገልግሎቶች (ኪራይዎች — መሬት፣ ቤቶች — ከልማት ድርጅቶች ዱቪደንድ፣ ትራንስፖርት ወዘተ) ካሁኑ ላቅ ማለቱን ማስታወስ ከላይ የተባለውን ያጠናክራል!

ይኽው የመጭው ዓመት ‘ፌዴራል’ በጀት የተዘጋጀው ከሃገር ውስጥ የሚጠበቀው ምርት ተዳክሞ የውጭ ንግድ ገቢው — ዶ/ር አብርሃም እንዳመለከቱት — ሃገሪቱን 17 ከመቶ የውጭ ግዥዋን ለመሸመት የሚያስችል ብቻ የውጭ ምንዛሪ በተገኘበት ዓመትና መንግሥታዊ ገቢ (ግብር፥ ታክስና ሽያጮች) ክፉኛ ባሽቆልቆሎበት ወቅት የቀረበ ሆኖ፣ የበጀቱ የገንዘብ ጥያቄ ካለፈው ጋር ሲነጻጸር፡ በ16.9% ወይንም በ46.4 ቢሊዮን ብር ማሻቀቡ ለብዙዎች (እኔንም ጨምሮ) እንቆቅልሽ ሆኖብናል።

የረቂቅ በጀቱ ክፍፍል ሲታይ፣ 114.7 ቢሊየን ብር ለካፒታል ወጭ (Capital budget — ማለትም — መንገድ ሥራ፡ ሕንጻ፥ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፥ መስኖና ግንባታ ወዘተ) መሸፈኛ ተይዟል። ከቀሪው ውስጥ 81.8 ቢሊየን ብር ለመደበኛ ወጪ (recurrent expenditures — ደሞዝ፡ ሥራ ማስኬጃ፥ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ወዘተ) እንዲውል ታቅዷል።

እንዲሁም ብር 117.3 ቢሊየን ለክልሎች ድጋፍ ተመድቧል (የ36.6%)። መዘዘኛው ‘የክልሎች ድጋፍ‘ ገንዘብ እንደተባለው ሳይሆን፥ ብዙ ጊዜ ልማትን ከማገዝ ይልቅ ፈላጭ ቆራጮቹ ለፈለጉት ጉዳይ ይውላል።

ሁኔታውን ለራሱ ሲያመቻችም፣ መለስ ዜናዊ “ክልሎች ቢፈልጉ ገንዘቡን ያቃጥሉት” ብሎ ኦዲተር ለማ አርጋው ያዘጋጁትን ኦዲት ሪፖርት አንቋሾ ግለሰቡንም አዋርዶ፡ በጀት እስከዛሬ በአንደኛ ደረጃ ለሕወሃቶች፣ ቀጥሎም ለሙሰኛ ፖለቲከኞች/ትናንሽ ፖለቲካ ካድሬዎች እንደፈለጉ ለፈንጠዝያ እንዲሆን በር መክፈቱና ተጠያቂነትን አሳውሮ መሄዱ የአደባባይ ምሥጢር ነው።

በተጨማሪም፡ ጨቋኙ መለስ ዜናዊ በሞተ ጥቂት ቀናት እያንዳንዳቸው የክልል ሹሞች እስከ ሚሊዮን ብር ድረስ — የማንም ፈቃድና የሕዝብ ይሁንታ ሳይጠየቅበት – በሟቹ ባለቤት በተከፈተ አካውንት ( Meles Foundation) ገቢ ተደርጎ (የቀረጥ ነጻ መብት ሁሉ ተሰጥቷት) የነበረውን ስናስታውስ፥ አሁንም ሃገሪቱ ወደ ብርሃን አለመሸጋገሯንና ዜጎቿን በከፈሉት ግብራቸውና በጀታቸው እንኳ እንዳማታከብር በግልጽ ለማሳየት መቻሉ፡ 320 ቢልዮን ብር (ገንዘቡ በአካል ካለ) ሃገራችን ወደከፋ ሁኔታ እንዳይገፋት ያስፈራኛል።

ስለሆነም፥ በዋና መ/ቤት ደረጃ ቁጥጥር በሌለበት ሃገርና ራሱ የክልሎች የፖለቲካ ክፍፍል (Decentralization) በሕግና ፌዴራሊዝም አሠራር ሳይሆን በዘፈቀደና በማስፈራራት በሆነበት፣ይህንን ከፍተኛ ገንዘብ በክልሎች ድጎማ ስም (ከጠቅላላው በጀት 36.6%) እንደዚህ መወርወሩ፡ አሳሳቢ ያደርገዋል — የሚባክነው ገንዘብ መጠን በመገመት። ለአንዳንዶች ምናልባትም ይህ ጉዳይ ልዩነቱ ገንዘቡ ዋናው መ/ቤት ቢባክን ወይንስ በክልሎች ደረጃ የሚለው ምርጫ ብቻ ሊሆን ይችላል።

ሆኖም እንዳለፉት ዓመታት ጉልበተኛው ሕወሃት አንጀታችንን የሚያሳርረው፡ ከካፒታል በጀት ውስጥ 50.7 ቢሊዮን ብር በተለያዩ ፕሮጀክቶች ሰበብ አስባብ (መንገድ ሥራ፡ ሕንጻ፥ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፥ መስኖና ግንባታ ወዘተ) ለሕወሃት የንግድና ተዛማጅ ድርጅቶች በመንግሥታዊ ድርጅቶች በኩል በልዩ ልዩ ኮንትራቶች ስም የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚያስገብርበትን ሕጋዊ-መሰል ድንጋጌዎችን አስቀምጦና መዋቅሮችን ዘርግቶ ኢትዮጵያን የሚሞሸልቅበት አንዱ የገንዘብ ምንጫቸው ነው።

በተጨማሪም፡ እንዴት ነው ገንዘብ ሚኒስቴር ለሕወሃት የንግድ ድርጅቶች ከአፍሪካ ልማት ባንክ (African Development Bank) ጋር እየተደራደረ፡ — ለአልሜዳ ቴክስታይል እንደተሠጠው $76.1 ሚሊዮን ብድር — የኢትዮጵያ ግብር ከፋይ የብድሩን ዋናና ወለዱን እንዲከፈል የሚደረገው?

‘የልማት ባንኩ’ ዶኪመንት ስለተወሰደው ወንጀለኛ እርምጃ የሚከተለውን ማብራሪያ ይሠጣል፦

  Increased availability of water should also result in increased employment opportunities for women, through increased investments, as in the case of Almeda textile factory in Adwa, which employs a large proportion of women.

  Ethiopia has boldly committed to achieve universal water supply and sanitation services to its citizens by 2020. Water is one of the priority sectors to help achieve inclusive, accelerated and sustained economic growth and to eradicate poverty.

  The total cost of the project is USD 114 million, co-financed by the AfDB (67%) and the Ethiopian Government (33%).

ዋናው ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ በዘንድሮው ሪፖርታቸው 20 ቢሊዮን ብር መባከኑን መዘገባቸውን ሳስታወስ — ገንዘቡ የት ወጣ የት ወረደ የሚለው ጉዳይ ትርጉም አይኖረው ይሆናል። የሚያሳዝነው ጉዳይ፣ ያገባኛል ብሎ የሚቆጣና የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሕጎች እንዲከበሩ የሚያስደርግ የተማረ ሃገር ወዳድ መጥፋቱ ነው! ይህ ብልግናም ከዓመት ዓመት እየባሰበት ለመሄዱ ሃያ ቢልዮኑ ብር በቂ ማስረጃ ነው!

በመጨረሻም ቅንጣቢ ለዘለቄታ ልማት! ኢትዮጵያ የዘለቄታ ልማት ጉባዔን (Sustainable Development Conference) በ2015 ያሰተናገደች ሃገር ሆና — ከአሜሪካ ምርጫ በኋላ — የፋይናንሲንግ ሜካኒዝሙ አደጋ ላይ በወደቀበት ወቅት እጅግ አናሳ የሆነው 7.0 ቢሊየን ብር በጀቱ ውስጥ መያዙ ምናልባትም ከመጀመሪያውም ለነገሩ በአዲስ አበባ በኩል ለፕሮፓጋንዳ እንጂ እምነት አለመኖሩን ያሳያል።
 

የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ዕድገት ዕውነተኛ መሠረት አለውን?

ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች፥ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ወይም ተገኘ የሚባለው ዕድገት አዘናጊ ነው። በአንድ በኩል ዜጎች አይደሉም የያድጉትና የሚበለጽጉት — ሕንጻዎች፡ መንገዶችና ባለሃብቶች ብቻ (ለዚያውም ሃገር ውስጥ ያሉት በልጽገው ኅብረተሰቡን የማያበለጽጉ)! ነጠላ ይሁን ጥንድ ዕድገት፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኪሣራን እያሠፋ የሚመጣ የፖንዚ ስኪም (Ponzi scheme) የሚባለው ዐይነት የውሸት ዕድገት ነው።

ይህ የሆነበትና የሚሆንበትም ምክንያት — ይህ 2010 በጀት ረቂቅ እንደሚያሳየን — ዕዳን፡ ብድርንና ሃገራዊ ኪሣራን እያሰፋፋ (debts, both domestic and external, fiscal and current account deficits — የመንግሥት ወጭዎች ከፍተኛና ገቢው ዝቅተኛ) በራሱ ቀጣይነት የሌለው በአርቲፊሻል ሣንባ የሚተነፍስ ዕድገት አድርጎታል።

እነዚህ ዋና ዋናዎቹ ችግሮችም በጀቱ ተግባራዊ በሚሆንበት (Budget Implementation) ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ በገሃድ የማይነገሩ የውስጥ ለውስጥ የአቅጣጫ ለውጦችን ሊያስገድዱ ይችላሉ። ይህም ሁኔታውን እስካሁን ሃገሪቱን አጥንቷን ሲግጡ ለነበሩ ይበልጥ ያመቻቻል። በእነዚህም ምክንያቶች በጀቱ የታለመለትን ዓላማና ግቦች መምታት እንዲሳነው ማድረግ እንደሚችሉ ከወዲሁ መገመት ይቻላል። ከእነዚህ ችግሮች መካከል፣ ከበጀቱ ዝግጅት አንስቶ በነበሩ ስህተቶችና ታላላቅ ጉዳዮችን በዘፈቀደ በመውሰድ አሁን ለፓርላማውም እነዚያ አለመጠቀሳቸው ከወዲሁ ከሃገሪቱና ሕዝቡ በተደበቁ ችግሮች መተብተቡን መገንዘብ ውስጥ አዋቂነትን አይጠይቅም።

እረ ለመሆኑ፣ ከ2012 ጀምሮ ለምን ይሆን የኢትዮጵያ የሰው ኃብት ልማትስ (Human Development Index (HDI)) ከ187 ሃገሮች 174ኛ ሆኖ የቀረው በ2016 መለኪያ? ከላይ ከተገለጸው ጋር ያለውን ዝምድና ልናገነዘብ ይገባናል — መለኪያዎቹ፦ ለሁሉም ዜጎች ምግብና መጠለያ (Food and shelter)፣ ጤንነትና (Health) የትምህርት ዕድል (Education) መሆናቸውን የተከፋፈሉት ውጤት ዝቅተኛነት መሆኑን በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ(Multidimensional Poverty Index (MPI)) ቅርብ ምልከታ ሠጥቶናል።

በዚህ ኤኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን ከነበረባቸው፣ ከ15-29 ዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉት ዜጎች መካከል የሥራ አጡ ብዛት መጨመር፡ ገቢ መጥፋትንና ድህነት መስፋፋት፣ ቀድሞውንም ኤኮኖሚው በዚህ ረገድ ያከናወናቸው ሥራ የመፍጠር አቅሙ አናሳ መሆኑን የተ.መ.ድ. ልማት ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ላይ ባደረገው ብሔራዊ ጥናት አረጋግጧል። ይህም ሪፖርት የሥራ አጥነትንና ድህነትን መስፋፋት ሁኔታ ኤኮኖሚው ዐይኑን የጨፈነባቸው ኅልቆ መሣፍልት መሆናቸውን እንደሚከተለው ነው ያስቀመጠው፡-

“Despite double-digit economic growth and substantial decreases in the percentage of the population below the national poverty line, the absolute number of the poor is roughly the same as 15 years ago and a significant proportion of the population hovers just above the poverty line and is vulnerable to shocks.”

ይባስ ብለው፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ የመንግሥታቸው ኢኮኖሚውን አስተዳደር ክንውን እንደሚከተለው ነበር የገለጹት ለፓርላማው:

  (ሀ) “የገንዘብ ፖሊሲው ኢኮኖሚውን በማሳደግና የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን በመፍጠር የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉን”

  (ለ)”ኢኮኖሚያዊ እድገቱ አጠቃላይ የዜጎችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ያረጋገጠ መሆኑን፥ የሃገሪቱ ዜጎች አማካይ የመኖር እድሜም ወደ 64.2 ከፍ ማለቱን”

  (ሐ)”የነብስ ወከፍ ገቢ በ2003 ዓ.ም ከነበረበት 396 የአሜሪካ ዶላር ባለፈው በጀት ዓመት ወደ 794 የአሜሪካ ዶላር ከፍ ማለቱን” ነው።

ስለማን ይሆን ሚኒስትሩ የሚናገሩት? ኢትዮጵያ የዜጎች ሁሉ መሆኗ ጉዳይ ጊዜው ያለፈበት ሆኗልን አብዛኛውን ታሪካችንን የሕወሃት ሰዎችና ደቀ መዛሙርቶቻቸው ሲሉት እንደኖሩት ሁሉ? በሌላው ዓለም ባልታየ ሁኔታ፣ የተሻሻለ ኤይድስ መድሃኒት በመገኘቱ ይህንን የሕይወት ዘመን ቁጥር መሻሻልን አስመልክቶ WHO እንደገለጸው በመላ አፍሪካ ውስጥ ከ2000-2015 በነበረው ጊዜ ውስጥ የ9.4 ዓመት ጭማሪ ምክንያት መሆኑን እንኳን ሚኒስትሩ ለመመልከት አለመሞኮራቸው አስገርሞኛል — የአስተዳደራቸው ጥረት ከማድረጋቸው በፊት!

Graphic source: Addis Fortune

በበጀቱ ዝግጅት ደረጃ በግድ የለሽነት ወይንም በግልጽነት መጉደልና ኋላም በአፈጻጸም ወቅት (Budget Implementation) የተወሰዱ አንዳንድ ግንዛቤዎች (Assumptions) መሰናክል ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ቀላል ነው። በምሣሌነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት ውስጥ የዋጋ ግሽበቱ አሃዝ አንዱ ነው። ለበጀቱ የተሳካ ተግባራዊነት፡ በበጀቱ ዓመት የዋጋ ግሽበቱ 8.0% እንደሆነ መቆየቱ አስፈላጊነት ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ ቢሠመርበትም፣ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ መረጃ እንደገለጸው፥ የዓመቱ አማካይ የዋጋ ግሽበት ከወዲሁ አሻቅቦ ሁለት ወር የበጀት ዓመቱ ከመጀመሩ በፊት በግንቦት 2009 ዓ.ም. 8.7% ገብቷል — ተንከባላዪ ወርሃዊ አማካይ ቁጥር 7.1% ቢሆንም።

በልበ ደፋርነት በበጀት አፈጻጸሙ ወቅት ይስተካከል ይሆናል የሚል አስተሳሰብ ካለ፡ አሁን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኤኮኖሚ ባለበት ሁነታ፡ ይህ አባባል ሊመነጭ የሚችለው በድፍረት ከተዓምር ሠሪነት ብቻ ነው ማለት ይቻላል!

ለነገሩ የሕውሃቱ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም ተከሰተ እንዲህ ያለ ከፍተኛ የበጀት ጥያቄ ያለበቂ ዝግጅትና ግልጽነት ይዘው ፓርላማ መቅረባቸው፡ ምናልባትም የፓርላማው አባላት ጥያቄና ንትርክ እንደማያነሱባቸው አውቀው ነው ቢባል እንኳ፣ ፓርላማ ውስጥ የሌሉ ነገር ግን ጉዳዩን በሚገባ በሚገነዘቡ ዜጎች ዘንድ ሚኒስትሩ ራሳቸውን እንደ ተዓምር ሠሪ አይተው ይሆናል የሚል ጥርጥር ያጭር ይመስለኛል።

ቀጥሎም፡ አስተዳደሩ ተገቢውን ለግብርና በታክስ የሚያስፈልገውን ገንዘብ አሠራሩን አስተካክሎ መሰብሰብ ሲገባው፣ ኤኮኖሚው ለበጀቱ የመክፈል አቅሙ እየተመናመነ ሄዷል። የሃገሪቱ ብድር ክምር መድረሱን በትክክለኛ ሚዛን ላይ ለማስቀመጥ አለመቻል፡ የውጭ ምንዛሪ ችግሮች በሃገሪቱ ገንዘብና ሸቀጦች ልውውጥ ላይ የሚኖራቸው አሰናካይነት ወዘተ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

በእኔ ዕይታ የዋጋ ግሽበቱ የሕወሃትን እጅ እስካላሰረ ድረስ፣ የሚፈለገው የሃገር ውስጥ ብድርና የውጭ ዕርዳታ መጠን እዚህ ከተጠቀሰው እንደሚበልጥ ጥርጥር የለኝም።
 

የዕዳ ጫና አደጋ

የገንዘብ ሚኒስትሩ የወቅቱ ችግር ግንዛቤ እንዳላቸው በሚያሳይ መንገድ፥ “የግብር ገቢ አነስተኛነት ከሃገር ውስጥ ሃብት አንጻር ያለው ድርሻ ዝቅተኛ” መሆኑን ከማመን ባሻገር “የግብር ሥርዓቱ አለመሻሻል [ለችግሩ] ዋናው ምክንያት ነው፤ ከዚህ ባለፈም ከፋዩም ሆነ በአስፈጻሚው አካል ያለው የአመለካከት ችግር ዋናው ምክንያት ነው” የሚል ስሞታ አስምተዋል።

በዚያ ዙሪያ ሚኒስትሩ ሃሣባቸውን ዘርዘር ስላላደረጉ ብዙ ማለት ባይቻልም፣ እንደ ብዙ ሌሎች ጉዳዮች ሁሉ፥ ግብርና ታክስ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሕወሃት የፖለቲካ መሣሪያ በመሆናቸው፡ ምን ማለታቸው እንደሆን ግልጽ አይደለም።

ይህም የሚነገረን፣ በዚህ ረቂቅ በጀት ዓመትና ቀጥሎም የኢትዮጵያ የሃገር ውስጥና የውጭ ዕዳ ጫና ከቁጥጥር ሊወጣ እንደሚችል ነው — ፖለቲከኛ ያልሆኑ ስም ያላቸው ኤኮኖሚስቶችና ዓለም አቀፍ የገንዘብና የልማት ድርጅቶች በዚህ ወር እንዳስታወቁን።

ነገር ግን ሚኒስትሩ “የውጪ ብድር የሃሪቱን ዕዳ የመክፈል አቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ ይፈጸማል” ቢሉም፣ የሁኔታውን አስገዳጅነት ያልሳቱት ሚኒስትር አብርሃም የውጭ ዕዳው ከዝቅተኛ ወደ መካከለኛ መሸጋገሩን ለመጀመሪያ ጊዜ በአገዛዙ ስም ሃገሪቱን በአንድ በኩል ለኢትዮጵያ ሕዝብ እያረዱ፡ በሌላ በኩል ደግሞ “አሁን ላይ ሃገሪቱ ያለባት ዕዳ ጤናማ” ነው ማለታቸው ኤኮኖሚው በአፍንጫው ቢደፋም፡ ሕወሃት ተጨማሪ ብድሮችን ከማሰባሰብና ሃገሪቷን ከማራቆት እንደማይቆጠብ የማያጠራጥር ማረጋገጫ ነው!

ይህ የሕወሃት አስተዳደር እየሄደበት ያለው አቅጣጫ፣ ለወዳጃቸው ለዓለም ባንክ ስላልጣመው፣ የዕዳው ጫና በደረሰበት ደረጃ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ያየችውን ልማት በአዲስ ማየት ሙትን አንደገና እንደመቀስቀስ እንደሚከተለው አስመስሎታል: –

“…[S]ome countries (e.g., Ethiopia, Côte d’Ivoire) may not reach the high growth rates of the recent past. Many countries need to contain debt accumulation and rebuild policy buffers…borrowing to finance large public investment projects underpinned the rise in public debt in Ethiopia.”

ከዚህ ውጭ፡ የአስተዳደሩን ገቢ (State revenues) በተመለከተ፣ በተዓማኒነት በፖሊሲና በአፈጻጸም ደረጃ መግባባትንና መገነዛዘብን ለመገንባት አሰተዳዳሪዎቹ ያደረጓቸውን ጥረቶችና ዝግጅቶች ምን እንደሆኑ ማየት አይቻልም — ምንም እንኳ በቅርቡ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምዝገባና ውይይት አካሂዶ 52 ቢሊዮን ብር በግብር ለመሰብሰብ ዝግጅት ማድረጉን ብሰማም — ሕወሃት በርዕዮተ ዓለማዊ አመለካከቱ እንደሚያስቀምጠው ‘የሃብታም ነጋዴዎችተዘረፍን ባይነት’ ስሜት ጠንካራ በሆነበት ሁኔታ መሆኑ ቢታወቅም!

የዚህ ጽሁፍ ዓላማም እነዚህኑ ከላይ ያነሳኋቸውን የፖለቲካ ኤኮኖሚውን አንኳር ችግሮች መመልከትና ማሳየት ይሆናል።
 

ግልጽነትና የዜጎች በኩልነት ተጠቃሚነት ለግብር አሰባሰብ ወሳኝነት አለው

በመንግሥታዊ በጀት በሁለት አቅጣዎች ግልጽነትና ተዓማኒነት ይጠበቃሉ፤ይለካሉ!

  (ሀ) የሕዝቡን ገንዘብ በግብር መልክ ሰብስቦ: ፕሮግራም ቀይሶ “ለእነዚህ ዓላማዎች ላውላቸው ነው” ብሎ ሥራውን እንዲያከናውን በፖለቲካና በሕግ ሥልጣን ከተሠጠው አስተዳደር ቃሉን የማከብርና ለማከናወን በጽሁፍ ያመለከታቸውን አገልግሎቶች በመሥጠት የሕዝቡን ሕይወት ባሻሻለበት መጠን ይለካል፤ ለምንስ ሙሉ ለሙሉ ማሳካት እንዳልቻለ ይመዘናል፤ ኦዲተሮችና ኢንስፔክተሮች ምርመራ አካሂደው ግኝቶቻቸውን ለተገልጋዩ ሕዝብ ያሳውቃሉ

  (ለ) ሕዝቡም ለሚያገኘው አገለግሎት ዋጋውን በግብርና በታክስ መልክ መክፈል ግዴታው ነው። ሕግ በትክክል በማይተረጎምበትና ፍርድ ቤቶች በነጻነት በማይሠሩበት ሁኔታ፡ አስተዳደሩ ብዙ ግኝቶችን ያዳፍናል። ሕዝቡም ጥርጥር ይገባዋል፤ ኪሱን ወደ መቆለፍ ያጋድላል። የተሠራውንና ያልተሠራውን በሥነ ሥርዓት አቅርቦ የሕዝብን ዓማኒነት ማግኘት እጅግ ጠቃሚ ነው። ይህ የጉልበት ጉዳይ ሣይሆን፣ የሕጋዊነት፡ የማግባባት፣ የመግባባትና የመተማመን ሆኖ ሳለ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ መንገድ ለመንቀሳቀስ ስለመቻሉ፡ ምንም ተስፋ የሚሠጥ ምልክት አልነበረም። እስካሁንም አይታይም።

የዚህ ዐይነት አስተዳደራዊ በደል የሕወሃት ዐይነት አስተዳደራዊ በደል (በተለይም በ’ደህንነቱ’) መፈጸሙ ሲሰማ — የአንድም ይሁን የጥቂቶች ጉዳይ — ሕዝቡ ነግ በእኔ ብሎ ያዳምጣል፡ መልዕክት ለማስተላለፍ እንደተለቀቀ ጭስ ለኔም ነው በሚል ተጠራጣሪነቱን ያጠናክራል። መረጃ በምሥጢር ከመሰብሰብ አስፈላጊ ቢሆንም፡ የሕወሃት የማፊያ አሠራር ሕዝቡን ወደ ክፍያ እንዲያደላ ያደርገዋል የሚለው አስተሳሰብ ዶዶማ ነው!

በእነዚህና ተዛማጅ ምክንያቶችና በተለይም ግብርና ታክስን እንደ ፖለቲካ መሣሪያው የሚጠቀምባቸው ያለው አስተዳደር፡ በአንድ በኩል የራሱን ድክመት ሕዝቡ ላይ በማላከክ (ግብር አልከፈሉኝም በማለት) — ማለትም ተገቢውን መዋቅር ባለመዘርጋትና ዘመናዊ የግብርና ታክስ አሰባሰብን ለራሱም ሆነ ሕዝቡን ከማስተማር ይልቅ — በኃይሉ በመተማመንና ብዙ ገንዘብ ለመሰብሰብ ከሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ባለመላቀቁ አስተዳደሩና ሕዝቡ የዐይጥና ድመት ፍልሚያቸውን ሊቀይሩ አልቻሉም።

ከኢትዮጵያ በተሻለ፣ ሌላው ቢቀር መነገጃ መደቧ ንጽሕናው ተጠብቋል (Savyra -Tax adult education course:marketplace)

ይህንን ለመለወጥ ታስቦ ይመስላል፡ በዓለም ባንክ፣ በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የእንግሊዝ የልማት ድርጅትና የአውሮፓ ኮሚሽን ገንዘብ ዕርዳታ ለኢትዮጵያ በተካሄደ ጥናት Financial Transparency and Accountability Perception Survey_June 2009)(June 2009) ሁሉም የድርሻውን ለመሳብ እንዲችል ለማድረግ አንዳንድ ምክሮች ተጠቅሰዋል።

ጥናቱን አሰተዳደሩ በመመሪያነት የተቀበለውና የፋይናንስና ኤኮኖሚ ሚኒስቴር ገጽ ላይ የተለጠፈ ሲሆን፡ ለዚህ ጥናት መረጃ ሲሰባሰብ፡ አዘጋጆቹ ከጻፏቸው አሳሳቢ ነገሮች መካከል፡ ኢትዮጵያውያን እንደ ግብርና ታክስ መሰል ለመንግሥት ያለባቸውን ግዴታዎች መወጣት እንደሚወዱና ለዚህም መልስ የሠጡቱ ተሳታፊዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ሳነብ አንድ ነገር ተሰማኝ። ሁልጊዜም አስተዳደሩን እንዳጭበረበረን እንወንጅላለን እንጂ፡ አሰተዳደሩ ሁልጊዜም ራሱን ማታለል እንደሚወድ የተገነዘቡ ኢትዮጵያውያን ግን ጥቂት ይመስሉኛል።

በወቅቱ ይመስለኛል፣ ከውጭ በነበረውም ሃገሪቱን ለዲሞክራሲ ለማመቻቸት ግፊት ሳቢያ፡ ዛሬ በሃገራችን ያለውን ይህንን የዐይጥና ድመት ግንኙነት ለማሻሻልና ብሎም ግብር አሰባሰብን ጤናማ በማድረግ የሃገሪቱን ዕድገትና ልማት ቀናና ሕጋዊ ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደረግ እንዲሆን ጥናቱ ውስጥ ካሉት ምክሮች መካከል የሚከተለው ይገኝበታል፡ –

  “Even though “quality of life” includes many elements outside the control of the local administration, many local governments around the world find this an important question and often survey citizens on the subject. Satisfaction with the quality of life is for many cities the ultimate aim of governance. Further, if citizens enjoy a good quality of life, they are likely to stay in the city, the city is likely to attract new businesses and investors, citizens will be more willing to pay their fees and taxes, and leaders are more likely to be reelected.”

 

በጀቱ ተግባራዊ የሚሆንበት ዩኒቨርስ

አንኳር ጉዳዮችን አጠር ባለ መልካቸው በተናጠል ለማቅረብ፡ የሕወሃት አሰተዳደር ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ‘ፊዴራል አሰተዳደር’ የ2010 ዓ.ም በጀት ዋና ዋና ገጽታዎችና ችግሮቹ ሉትን ይመስላል፡-

  ◙   የግብርና ታክስ ገቢዎች ከዕቅዱ በብዙ አንሰው መገኘት ስለ ጥንድ
      ቁጥር ዕድገቱ ብዙ የተዘፈነለት ኢኮኖሚ ዛሬም የብድር
      መጠኑን መቀነስ አልቻለም። ለማንኛውም በማይታመን ደረጃ
      በብድርና (14.3 ቢሊዮን) ዕርዳታ (20.2 ቢሊዮን)፣
      በድምሩ 34.5 ቢሊዮን ብር እንደሚፈለግ ተገልጿል። የሚፈለገው
      ሊበልጥ ስለሚችል፡ የዚህ ተዓማኒነት በጣም ዝቅተኛ ነው –
      በግብርና በታክስ የታቀደውን ያህል ለመሰበሰብ ባለመቻሉ ምክንያት

  ◙   በሃገሪቱ የዲክታተርሺፕ ችግሮችና ድፍርስ ፖለቲካ እንዲሁም
      የዓለም ሁኔታዎች መንስዔዎች ሆነው መዋዕለ ንዋይ ቀንሶና ዕርዳታም
      ደርቆ ኤኮኖሚው ተዳክሟል — ሕወሃት ቢክድም። ኢትዮጵያ
      ከሁሉም ለጋሽ ሃገሮች በየዓመቱ ከ$3.6 ቢሊዮን (2014)
      በላይ ስታገኝ የኖረች መሆኗ ምን ያህል ኢኮኖሚውን
      እንደደገፈው ያሳያል። በተከታታይ ዓመታት አሁን ካለው የውጭ
      ንግድ ገቢ በልጦ መገኝቱ፣ ኢትዮጵያ ምን ያህል በዚህ ላይ እንደ
      ቆመች ያሳያል። አሜሪካ ዕርዳታውን በ28%
      ሲቀንስ
  ፡ አንዳንዶቹም ላይ እስከ 100 ከመቶ መቀነሱ (ወሊድ
      ቁጥጥር) ችግሩን ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል

  ◙   10 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝባችን እየተራበ የሕወሃት ጉራ ዕርዳታ
      ወደ ሌሎች
  መዞርን አስከትሏል። ኮሚሽነር ምትኩ ካሣ:
      አቅም ሳይኖር “የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለዕርዳታ ፈላጊዎች
      መድረስ ካቃተው መቶ በመቶ እኛ እንሸፍናለን” ማለታቸው
      (2014) አደጋ አለው

  ◙   ከውጭ ገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ ገንዘብ ለመበደር ኤኮፖኖሚውና
      ፖለቲካው ብቃት አጥቷል

  ◙   ከላይ የተጠቀሰው ዐይነቱ ዕድገት ባስከተላቸው ብድሮች ምክንያት፥
      በ2016 የሃገሪቱ ዕዳ አርባ ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና ይህም
      ከብሔራዊ ምርት አንጻር (GDP) 55% መድረሱ ታውቋል
      የናረ የውጭ ዕዳ ጫና አሳሳቢነት ምክንያት በFitch ምዘና (2017
      Rating) በራሷ ገንዘብም ሆነ በውጭ ምንዛሪ ዕዳዋን የመክፈል አቅሟ
      ለባለ ሃብቶች አደጋ ስላለበት Highly speculative ተብላለች።
      ይህ ከውጭ መበደርን — አበዳሪ ከተገኘ — በጣም ውድ ያደርገዋል።
      ከዚህ ሁኔታ በመነሳት     የዓለም ባንክ፤ IMFም
      ጥንቃቄና የመቆጠብን አስፈላጊነት አስምረውበታል

  ◙   በተለይም ‘አውራ መሪ ፓርቲ ነኝ’ የሚለው ሕወሃት ለራሱ የንግድ
      ድርጅቶች በምሥጢርና በዘዴ ከአፍሪካ ልማት ባንክና ሌሎች
      ምንጮች በኢትዮጵያ ስም ብድር እየወሰደ ዜጎችም ሳያውቁት
      ሕወሃቶች የተበደሩትን ዕዳ ከፋዮች መደረጋቸው ሕገ ወጥና
      በመንግሥት ሥልጣን ስም የማጭበርበር/ክህደት ሥራው ሕዝቡን፥
      ሃገሪቱንና ኤኮኖሚውን ጎድቷል

  ◙   የግንቦት 2017 ዋጋ ግሽበት በበጀቱ ከታለመው ከወዲሁ በልጧል።
      የውጭ ዕርዳታ በር ገርበብ ማለት ብዙ ታዲጊ ሃገሮችን ይጎዳል —
      በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ዐይነቶችን የተፈጥሮ ሃብት የሌላቸውን።
      እስካሁን የሕወሃት አስተዳደር የተፈጠረለትን አጋጣሚ በመጠቀምና
      ተጓዳኝ ስኬቶችን የራሱ ፖሊሲ ውጤት ማስመሰሉ አማንያን
      ያተረፈለት ቢሆንም፡ አሁን አስቸጋሪ ሁኔታ ጋር መጋፍፈጥ ሊኖርበት
      ነው። ከነዚህም አንዱ የዋጋ ግሽበትን በነጠላ አሃዝ አሰቀርቻለሁ ሲል
      የነበረው፡ምርትና ገቢ ዝቅተኛ በሚሆኑበት በዚህ በጀት አፈጻጸም
      ዓመትና ባሻገርም የኑሮ ውድነቱ በቋፍ ያለውን ሕዝባዊ ቁጣ
      ግለት ሲሰጠው በሚከተለው ፖሊሲ ነው

  ◙   በዘርና ዝምድና ላይ የተመሠረተው ፖለቲካ ኢኮኖሚ
      ጥቂቶችን ተጠቃሚ በማድረጉ
  የሥራ ዕድልን ማስፋፋት
      በማይታወቀው ኤኮኖሚ ድህነት ውስጥ ተዘፍቀዋል።

      ካለው ዝርፊያና ባለው ኢፍታሃዊ የሃብት ክፍፍል ሥራ አጥነት
      ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። የዘራፊዎች ፖሊሲዎችና እነዚህም
      ያስከተሉት የገቢ ዕጦት (Lack of sustenance) ድህነትን
      መላቀቅ አዳጋች አድርጎታል።

  ◙   ተከታታይ ድርቁም የገበሬውን ጥሪት ስላሟጠጠ የድህነቱ ጥልቀት
      ዜጎችንም ኤኮኖሚውን እኩል እየጎዳ ነው ሥራ አጥነትና/a>

  ◙   የአስተዳደሩ የኤኮኖሚ ቁጥሮች ክምን ጊዜውም ተዓማኒነት
      አጥተዋል

  ◙   የሕወሃት አስተዳደር በበጀት ላይ የሚያሳየው የሃሣብና የግንዛቤ
      በ26 ዓመቱ ያለመሻሻል በትልምና ዕቅድ የማስፈጸም ድህነት
      ይታይበታል

  ◙   በየደረጃው ተጠያቂነት ጠፍቷል

  ◙   የተንሠራፋ ሙስና ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩ

  ◙   የሕወሃት ቅሌታም ፕሮፓጋንዳ የኢኮኖሚ ፖሊሲውንና ፖሊሲ
      አውጭዎችን በባዶ እንዲሳከሩ እያደረገ ነው

  ◙   የሃገሪቱ ሰላም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ተመሥርቶ ዜጎች
      በእሥራት፡ ግድያና በጠብመንጃ ኃይል መያዛቸው
      የኢንቬስተሮችን ጥርጥር ማጠናከሩ የሃገሪቷን ገጽታና
      አለመረጋጋት ምልክት ሆኖ ኤኮኖሚውን እየጎዳ ነው

  ◙   የሥልጣን ብልግና የሃገሪቱን የፊናንስ ሕጎች በዘፈቀደ በመጣስ
      የበጀት አፈጻጸምን እያሰናከለ ነው

  ◙   አስተዳደሩ ከራሱ ፍላጎት ውጭ ለሕዝቡ ስሜት ስለሃገሪቱ ከሌሎች
      ሃገሮች ጋር ተወዳዳሪነት ደንታ ቢስ መሆኑ ወደ ኋላ እንድትንሸራተት
      እያድረጋት ነው። የሕወሃት አስተዳደር ደካማነትና ለዚህ መልሱ
      ለኅብረተሰቡ ዛሬና ነገነት ደንታ ቢስነት በመሆኑ፣ የብሔራዊ
      ዕርቅ ጥሪ ትርጉመ ቢስ መሆኑን ስሞኑን በፓርቲዎች ድርድር ላይ
      “ኢሕአዴግ ከማንም ጋር ፀብ ላይ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር
      ብሔረሰቦች በከፋቸው ዘመን እንኳን ፀብ ውስጥ ገብተው
      አያውቁም፤” ብሎ አጣጥሎታል

  ◙   ከፍተኛ ብድር ጫና፥ የገንዘብ ችግርና (value loss) የምርት
      በብቃት አለመገኘት (ምንም እንኳ ሚኒስትሩ 290.3 ሚሊዮን
      ኩንታል የእርሻ ምርት ይኖራል ቢሉም) በተለያየ መልኩ እየሠረገ
      ያለው የዋጋ ግሽበት ከወዲሁ የዜጎችን ሕይወት ይበልጥ በማመሳቀል
      (በተለይም ገቢ ያለውን ክፍል) ከባድ አድርጎታል። አሁን
      የሚታየውን የተዳከመ የሸቀጦች ልውውጥ ያባብሰዋል፤ በጀቱም
      ለኅብረተሰብ ለውጥና ዕድሳት በፖሊሲ መሣሪያነት ሊያገለግል
      አይችልም

  ◙   በሕዝብና አስተዳደሩ መካከል መተማመንና በጎ ፈቃድ ከተሟጠጠ
      ስለሰነበተ፡ እንዲሁም የሕዝቡ መብቶች በታፈኑበት ሁኔታና
      አያሌ ቤተሰቦች የሚያዝኑባቸውና የሚያለቅሱባቸው ጉዳዮች
      በመበራከታችው፡ በሕዝቡና አስተዳደሩና መካከል መከባበርና
      ልውውጥ አለመኖር ኤኮኖሚውን ወደ ለውጥ መሣሪያነት ለመጠቀም
      የሚሹ ወገኖች ቁጥር ቢደናደን አያስገርምም

በተግባር የሕወሃት ክንውኖች በአካባቢ ጥበቃ

የበለጸገው ዓለም ለዘላቂው ልማት ግቦች አፋጻጸም መዋጮ ለማድረግ ቃል መግባቱ ሲታወስና አሁን ማፈግፈጉ ቢታይም፡ በሕውሃት አስተዳደር ግን በተባለው በጀት አንቀጽ ሥር የታሰበው ገንዘብ አልተገኘም በሚል ምክንያት ሰባት ቢሊዮን ለስም መድቦ፣ ሁኔታው ሲያመች ደብዛዋን ለማጥፋት የታቀደች ምደባ ትመስላለች!

ለመልክ ግን፣ ሕወሃት የሁሉንም ትኩረት ይስባል ብሎ ለገመተው የአካባቢ ጥበቃ (Environmental Protection) ትኩረት የሰጠ ቢመስልም፡ በነሼር ኢትዮጵያ (ወዘተ) የአበባ እርሻ ኬሚካሎች ምክንያት ከጥቅም ውጭ የሆነው (የማስጠረጉ ሥራ ውድና ገንዘብ፡ በጎ ፈቃድና ዝግጅት ስሌለ የማይታሰብ ነውና) የዝዋይ ሐይቅ ውሃው ጥቅም ላይ እንዳይውል ከታጋደ አያሌ ወራት አልፈዋል። በተለያዩ ፋብሪካዎች ፍሳሽ የሃዋሣ ሐይቅ በመበከል ላይ መሆኑን ነዋሪዎች በከፍተኛ ጭንቀት እንደሚናገሩ ይሰማል። አዲስ ተቋቋመ በሚባለውና በቅርቡ የተመረቀው የሃዋሣ እንዱስትሪያል ፓርክም ጭምር የተመለከተ ሥጋት ተሰምቷል፣ ምንም እንኳ የፓርኩን ፍሳሽ ማስወገጃ የገነባው ‘የውጭ ኩባንያ’ ነው ቢባልም።

ችግሩ መባባሱን በሚያሳይ መንገድ፣ የወሃት ሚዲያ የሆነው ፋና ብሮዲካስት ከኢትዮጵያ የሥምጥ ሸለቆ ሐይቆች ውስጥ የሚመደበው የደምበል ሐይቅ ከተለያዩ ፋብሪካዎች በሚወጣ ፍሳሽ መበከሉንና በተለይም በባቱ ከተማ ነዋሪዎች የውሃ አቅርቦት ላይ ችግር መፍጠሩን ሰኔ 6/2009 ዘግቧል።

በሃገራችን መካከለኛ ክፍልና በተለይም በአማራ ክልልም በቆዳ ፋብሪካዎች ከሚካሎች ምክንያት አያሌ ውንዞቻችን እየተበከሉ ናቸው። ሕወሃት ዐይኑን የተከለው ጊዜያዊ ጥቅሙ የሆነው የውጭ ምንዛሬ ማሰባሰብ ላይ ብቻ በማተኮር (ለዚያውም ላይሳካለት)፣ በመጭው ትውልድ ላይ የጥፋት በትሩን ሠንዝሯል።

ይህንን ጉዳይ በቅርብ የተከታታለው የዋናው ኦዲተር መ/ቤትም፣ የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤን አንድ ገጽታ ብቻ በመምዘዝ የሚከተለውን በቅርቡ አትቷል፦

  “የዓሣ ሀብት የሚገኝባቸው የውሃ አካላት፣ በአካባቢያቸው ዙሪያ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በዓሣ ሀብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከሌሎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችሌ የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶ ተግባራዊ ሊደረግ ሲገባ በናሙና በታዩት በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በሚገኙ የውሃ አካላት አካባቢዎች ከሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የሚወጡ የኬሚካልና ንጥረ ማዕድን እጣቢዎች፣ ፌሳሾችና የእርሻ ኬሚካልች የዓሣ ሀብትን እየጎዱ እንደሆነ ከማሳወቅ ውጪ ችግሩን ለማቃለል በሚኒስቴር መ/ቤቱ የተሠራ የቁጥጥር፣ ክትትል ሥራ አለመኖሩ፣ እንዱሁም በሀይቆችና መጋቢ ወንዞች አካባቢ የኢንቨስትመንት ስራዎች ከመከናወናቸው በፊት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ሲሠራ ሚኒስቴር መ/ቤቱም ሆነ የሚመለከታቸው የክልል አካላት አስተያየት እንደማይጠየቁና ተሰርቶ ሲያልቅም እንዲያውቁት”አይደረግም።

 

ለበጀቱ መሳካት መሟላት ያለባቸው ሁኔታዎች

የዘንድሮውን ረቂቅ በጀት ለየት የሚያደርገው መንግሥታዊ ገቢ (State Revenue) ክፉኛ ባሽቆለቆለበት ሁኔታ ብቻ ሣይሆን: በሕዝባዊ አመጽ ማግሥትና ቀጣዩ አቅጣጫ የማይታወቅበት ወቅት መዘጋጀቱ ነው። በአንድ በኩል — ይህንን በቁጥር አስደግፎ መናገር ባይቻልም — ከተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ አንጻር ሕወሃትና ተባባሪዎቹ በግፍ አያሌ ዜጎቻችን መጨፍጨፋቸውን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ በጀት ነው ቢባል ማገነን አይሆንም። ልቡ ያመረረ፣ ክፉኛ ሲፈራ የነበረ ሕዝብ ለአስተዳደሩ ድጋፉን መንሣቱን የሚያሳይ ለመሆኑ አንዳንድ ምልክቶች ይታያሉ።

ያ ሕዝባዊ አመጽ ባይከሰት እንኳ፡ ሕወሃቶች እያሳዩ ባሉት ‘የማን አለብን’ ባህሪ ምክንያት፡ ሕወሃት እየሠራበት ያለው ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ሁለተኛ ዜጎች የማድረጉ ዓላማ ድምጽ የለሽ ሕዝባዊ አጸፋ እያጋጠመው ነው። ይህና የጥቂቶች ብቻ በዕድገቱ ተጠቃሚ መሆን፡ ሕዝቡ ይህን ሁኔታ እንዳላማቸው ይዘው ለተነሱት ያለውን ጥላቻ በማጠናከር ውስጥ ለውስጥ ውድቀታቸውን መሻቱ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ለመንግሥታዊ ገቢ መቀነስ በምክንያትነት ሊቀመጥ ይችላል። ከላይ እንዳልኩት ይህንን በቁጥር መበታተን አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን በንግድ ዙርያ ያሉትን ውዝግቦችና የ Value Added Tax ሁኔታ መመልከት ይቻላል።!

ተሻሻለ ሲባል በግብርና ታክስ ክፍያ ላይ እንደሚታየው የአስተዳደሩ ገቢ ማዝቀጥ — ሕዝቡ ባመቸው መንገድ ሕወሃትን ገቢ ለመንፈግ የተቻለውን እንደሚሞክር ያሳያል። በዲያስፖራ በኩልም ይህንን ተመሳሳይ ሁኔታ አይተናል። ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሁለተኛው የሩብ ዓመት ሪፖርት ውስጥ እንደዘገበው — የ14.8% በውጭ ምንዛሪ ቅናሽ (Net private transfers — መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን 55.7% ቅናሽ ሳይጨምር) መፈጠሩ ዶላር በቀጥታ በባንኮች ባለመላክ የተፈጠረ ሁኔታ ጭምር መሆኑን ማንም አይስተውም።

በሌላ በኩል ደግሞ፥ አስተዳደሩ ተደፈርኩ የሚለው ስሜት በአማጺው ሕዝብ በኩል እንዳይፈጠር፡ የሕዝቡ ተቃውሞ ኤኮኖሚው ላይ ተጽዕኖ አላሳደረም ብሎ ደጋግሞ ቢከራከርም፡ የቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ ላለመምጣት መወሰናቸው ኤኮኖሚውን ብሎም የሕወሃትን የውጭ ምንዛሪ አቋም ክፉኛ ሰለመታው፣ የውጭ ግዥውን ማዳከም ብቻ ሳይሆን፡ የዓለም ኤኮኖሚ መዳከምና የሃገር ውስጥ የማምረት አቅም መዳከም ጋር ተዳምሮ የምንዛሪ ካዝናውን አራቁቶታል።

በታሪክ እንደምናየው ከሆነ፣ አንድ ሕዝብ በላቀ መጠን የግብርና የታክስ ክፍያውን ከቀኑ መንግሥት ሲይዝ፡ በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን የመሟጠጥ ምልክት መሆኑን ሕውሃትም እንደሚያምን አልጠራጠርም። ልዩነቱ ግን ሕወሃት ችግሩንና ስህተቱን ተገንዝቦ ያርማል ወይንስ ተጻራሪ ብሎ የሚገምታቸውን ወንጀለኛ አድርጎ ትጥቅ ይዞ ስለተነሳ ችግሩን የፈታ ይመስለዋል ላይ ነው!

ያለፉት በጀቶች ማስረጃ ከሆኑ የሃገሪቱን የፊናንስ ሕግ ባለመከተልና ለዜጎች ሰሜት ክብር ባለመስጠት፣ ገንዘቡን ሕወሃት ለፈለገው ጉዳይ የሚያጠፋው ስለሆነ — ኢትዮጵያ ተጠያቂነት ተግባራዊ የማይሆንባት ሃገር መሆኗ እየታወቀ — የረቂቅ በጀቱን ተግባራዊነት ለማረጋገጥ፡ የሃገሪቱ የኤኮኖሚና ፋይናንስ ትብብር ሚኒስቴር የሚከተሉትን እጅግ ጠቃሚ የሆኑ (ከሰባቱ ስድስቱ ማለት ይቻላል) መለኪያዎችን አስቀምጧል።

እነዚህንም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የፋይናንስ ሚኒስትሩ ሰኔ 1/2009 በፓርላማ ንግግራቸው ውስጥ እንደሚከተለው ነካክተዋል፦

  ◙ የኢኮኖሚ ዕድገቱ በበጀቱ ዘመን 11.1% ከሆነ

  ◙ የዋጋ ግሽበቱ በአማካይ 8% ላይ ከቆየ (አንባብያንን አይግረማቸውና በግንቦት 8.7% ገብቷል)

  ◙ የውጭ ብድር ልጓም ከተደረገለት

  ◙ የገቢ ዕቃዎች ዋጋ የ12.5% ዕድገት እንዲኖረው ከተደረገ

  ◙ የሃገር ውስጥ ምርት ዕድገት 19.1% ሲረጋገጥ

  ◙ ሴፍቲ ኔት ሥራ አጡን በተገቢው መጠን ከደገፈ፣ እንዲሁም

  ◙ ሕጋዊነትንና ፈጣን ተጠያቂነትን በመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ውስጥ ማረጋገጥ እሚቻልበት ሁኔታ ከተፈጠረ

ከላይ እንደሚታየው፣ ሥራ መፍጠር የማይችል ኤኮኖሚ ሥራ አጥ ዜጎች በሴፍቲ ኔት የመታቀፋቸው ጉዳይ ለበጀቱ ተፈጻሚነት አንዱ መለኪያ አድርጎ ሲያቀርብ፡ በጦርነትና በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ሃገሮች ተቀባይነት ያለው አሠራር ሆኖ ሳለ — ዕጥፍ ድርብ ኤኮኖሚው አዳጊ ሃገር ነው የምመራው ለሚል አስተዳደር ግን — የዚህ ዐይነቱን ድፍረት ለመጀመሪያ ጊዜ መመልከቴ ነው — በመስኩ ካለኝ ዓለም አቀፍ ልምድ አንጻር።
*Updated.
 

%d bloggers like this: