ድንገተኛ የገንዘብ ሚኒስትሩ ትውስታ?         የግብር ገቢ አሰባሰብና የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛነት የ2010 በጀትን ለማሳካት እንደሚያዳግት የገንዘብ ሚ/ሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ አመኑ!

23 Jun

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 16 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2009 ዓ.ም ደካማ የግብር ገቢ አሰባሰብ እና እያሽቆለቆለ ያለው የወጪ ንግድ ገቢ ሳይስተካከል የ2010 በጀትን ማሳካት ከባድ እንደሚሆን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ተናገሩ።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር እቅዱን ለማሳካት በሚያስችሉ ጉዳዮችና በአጠቃላይ በጀት አጠቃቀሙ ዙሪያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከነዋሪዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ፥ በግብር ገቢ አሰባሰብና በወጪ ንግድ አፈጻጸም ዙሪያ የታዩ ክፍተቶችን በውይይቱ ወቅት አንስተዋል።

ለቀጣዩ በጀት አመት የቀረበው ረቂቅ በጀት ከዘንድሮው በጀት አመት አንጻር የ9 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ ሲኖረው፥ 196 ቢሊየን ብሩን ከግብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል።

ይሁን እንጅ በዘንድሮው በጀት አመት ከታየው የግብር ገቢ አሰባሰብ ክፍተት አንጻር ይህን እቅድ ማሳካት አስቸጋሪ እንደሚሆን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

እየተጠናቀቀ ባለው የ2009 በጀት አመት ከግብር ገቢ 171 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ቢታቀድም፥ በ11 ወራቱ 120 ቢሊየን ብር መሰብሰቡ ለዚህ ማሳያ አድርገው አንስተዋል።

ከዚህ አንጻርም በእቅድ ልክ ገቢ መሰብሰብ፣ የወጪ ንግዱን አፈጻጸም ማሳደግ እና የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓቱን በአግባቡ መምራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

በግብር ገቢ አሰባሰብ ላይ የሚስተዋለው ችግርና በጀት ለታለመለት አላማ አለመዋሉም በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።

ይህም በተቋማት ውስጥ የበጀት ጉድለት ቢስተዋልም በጊዜ ኦዲት አለመደረግ ለችግሩ መንስኤ መሆኑም ነው የተነሳው።

ከወጪ ንግድ አፈጻጸም ጋር ተያይዞም በተወሰኑ የምርት አይነቶች ላይ ብቻ የተገደበውን የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ማስፋት ይገባል ተብሏል።

ሚኒስትሩ በመንግስት ተቋማትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የቁጠባ ባህልን ማሳደግ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም የመንግስት አካላት ውጤት አልባ የውጪ ሃገራት ጉዞ እንደ አስፈላጊነቱ ታይቶ እንደሚቀነስ ጠቅሰዋል።

ለበጀቱ መሳካት የግብር አሰባሰቡን ካለበት ዝቅተኛ አፈጻጸም በማውጣት መስራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት፤ ሁሉም አካል የድርሻቸውን ሊወጣ እንደሚገባ በመጥቀስ።
 

ተዛማጅ፡

ትልቁ የኢትዮጵያ ‘ፌደራል’ በጀት ድክመቱ፣ገጽታዎቹና ውስብስብ ችግሮቹ
 

%d bloggers like this: