ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ገንዘብ እንዲጠናቀቁ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ይገባል ይላሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ ሕወሃትና የንግድ ድርጅቶቹ እያሉ የማይሆነውን?

6 Jul

የአዘጋጁ አስተያየት፡

  የ2010 ፌዴራል በጀት ከሐምሌ 1 ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ስላለበት ከፓርላማ ጋር ቅርብ ውይይት ሲደረግ ክርሟል፡ ምንም እንኳ ፓርላማው ምንም ማድረግ የማይችል ቢሆንም። ለነገሩ ጥሩ ጥሩ ዙፋን ንግግር ብዙዎቹ መልሶቻቸው “በይሆናል”ና “አይሆንም” መወሰናቸው ምን ያህል ተጠያቂነትና ኃላፊነት ሃገራችን ውስጥ እንደሌለ የሚያሠምርበት ልውውጥ ሆኖአል!

  በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ የሃገሪቱ የውጭ ዕዳ ጣራ መንካቱ እየታወቀ፡ ጠቅሎ ለመሄድ እንደተዘጋጀ አስተዳደር፡ በየሣምንቱ ተጨማሪ የውጭ ብድሮች ፓርላማው እኒድያጸድቅ እየታየ ነው። ፓርላማው ይህን እንዲያደርግ የሚሆንበት ምክንያት የመጠየቅና የመክልከል ሥልጣን ኖሮት ሳይሆን የውጭ አበዳሪዎች የፓርላምውን ውሣኔ ገንዘባቸውን ስለማይሠጡ ነው!

  እንደሌሎቹ የሕወሃት ሥራዎች ሁሉ፡ የዶ/ር አብርሃም ከፖርላማው ጋር የነበራቸው የሃሣብ ልውውጥ ቀልድና ጨዋታ መሆኑ፡ ሕወሃት ለሃገሪቱና ለሕዝቡ ያለውን ንቀት የሚያሳይ በመሆኑ፣ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል!

  በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡ በግብር ዙርያ የሚያሰማው ቁጣና ምሬት አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ፡ በተለይም ግብር ላለመክፈል መሻቱን ገንዘቡን በመያዝ የፓለቲካ እርምጃ መውስደ መጀመሩን አስመልክቶ፡ ችግሩን በሃቅና በሕጋዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ፡ አሁንም ዜጎችን ማስፈራራታና ማሠር መጀመሩ፡ የኢትዮጵያውያን ሕልውናና ሕይወት አደጋ ላይ መሆኑን በብርቱ ልንገነዘብና አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ የሚገባበት ደረጃ ላይ መደረሱ ከራሱ የአስተዳደሩ የዜና አውታሮች የሚወጡት ዜናዎች ግለት ምሥክርነት ይሠጣሉ!

 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 29፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በጀት የተያዘላቸው ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና ገንዘብ እንዲጠናቀቁ ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።

አባላቱ ለ2010 ዓ.ም በተያዘው 320 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር፥ ረቂቅ በጀት ላይ ዛሬ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተመደበው በጀት አግባብነት፣ ለወሎ ተርሸሪ ሆስፒታል የተመደበው በጀት አነስተኛ መሆን፣ ባለፈው አመት በጀት ተይዞላቸው ባልተጠናቀቁ የተለያዩ ፕሮጀክቶች፣ በሰራተኞች ዘንድ የሚታየውን የወጭ መጋራት አለመክፈል ጉዳይ፣ የበጀት ጉድለት እና ለጤናው ዘርፍ በተመደበው በጀት አነስተኛነት ላይ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተም ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዋል።

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የበጀት ድልድል ጋር ተያይዞ ለቀረበው ጥያቄም፥ የሚፈለገውን የሰው ሃይል ለማፍራት በየአመቱ ከፍተኛ በጀት እየተመደበ መሆኑን ጠቁመዋል።

በቀጣይ ጥራት ላይ ያተኮረ የበጀት ድልድል እንደሚኖር የጠቀሱት ሚኒስትሩ፥ በነባር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የያዟቸውን ፕሮጀክቶች በጊዜ ከማጠናቀቅ ባለፈ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች አይኖሩም ብለዋል።

የመደበኛ በጀት ድልድሉ ተቋማቱ በያዟቸው ተማሪዎችና መምህራን ቁጥር እንዲሁም ሌሎች የግመታ ዘዴዎችን በመጠቀም እንደሚወሰን ጠቁመው፥ የበጀት ድልድሉም መስፈርቱን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለወሎ ተርሸሪ ማስፋፊያ ሆስፒታል የተያዘው 72 ሚሊየን ብር አነስተኛ ነው በሚል ለቀረበው ጥያቄም፥ ገንዘቡ የሃገሪቱን በጀት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተመድቧል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ባለፈው አመት በጀት ተይዞላቸው ሳይጠናቀቁ የቀሩ ፕሮጀክቶችን በተመለከተም ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል ያሉት ሚኒስትሩ።

ከዚህ ባለፈም ከመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው ከወጡ በኋላ የወጭ መጋራት የማይከፍሉ ሰራተኞችን ጉዳይ ለመከታተል በሚኒስቴሩ በኩል እቅድ መያዙንም አንስተዋል።

በወጭና ገቢ ላይ የሚታየው ክፍተት ለበጀት ጉድለት መንስኤ እንደሆነም ነው ሚኒስትሩ በምላሻቸው የጠቀሱት።

ሚኒስትሩ በምላሻቸው ለጤናው ዘርፍ የተያዘው የአምስት በመቶ በጀት፥ ክልሎች በጤናው ዘርፍ ከያዙት በጀት ጋር ተዳምሮ በዘርፉ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

የሃገሪቱ የጤና ፖሊሲ መከላከልን መሰረት ያደረገ በመሆኑም በጀቱ ከዚህ አንጻር የተቃኘ እንደሆነም አስረድተዋል።

ከአዋሽ ወልዲያ የባቡር ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ የካሳ ክፍያ ያልተፈጸመላቸውን ግለሰቦች ጉዳይ እልባት ለመስጠትም ክትትል እየተደረገ ነውም ብለዋል በምላሻቸው።
 

ተዛማጅ:

  ትልቁ የኢትዮጵያ ‘ፌደራል’ በጀት ድክመቱ፣ገጽታዎቹና ውስብስብ ችግሮቹ

  ድንገተኛ የገንዘብ ሚኒስትሩ ትውስታ? የግብር ገቢ አሰባሰብና የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛነት የ2010 በጀትን ለማሳካት እንደሚያዳግት የገንዘብ ሚ/ሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ አመኑ!

  በቀን ገቢ የግብር ግመታው ላይ ቅሬታ ያለው ማንኛውም አካል ቅሬታውን ማቅረብ ይችላል- ባለስልጣኑ

 

%d bloggers like this: