ጣናን እናድን — በይሁኔ አየለ

12 Jul

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

የተክሎችና የሰዎች ጦርነት- እንቦጭን እንደማሳያ፡፡

በኢትዮጵያ ተማርን የምንል ሰዎች ፈተና እየመጣብን ነው፡፡ በእኔ ፍረጃ የተማርን ስንል ቢያንስ 12ኛ ክፍልን ያጠናቀቀን ሁሉ ይይዛል፡፡ የፈተናውን ስጋቴን ባለፈው በደቡብ ክልል በተለይ በጌዲዮ ዞን የይርጋ ጨፌ ቡና በውርጭ በተመታበት ወቅት ገልጨ ነበር፡፡ የችግሩ መፍትሄ ምንድን ነው ብዬ ሳስብ ያለው አማራጭ ውርጭ መቋቋም የሚችል ዝርያ ማግኜት መቻል ነው፤ ያ ደግሞ የሚጠበቀው ከተማረው ነው፡፡ አሁን ደግሞ ከአሜሪካ መጣ የተባለ ትል(ተምች) እያራወጠን ነው፡፡ በእሱ ላይም ዘመቻ ጀምረናል፤ ምን አማራጭ አለን፡፡ እንደምነሰማው “እንቦጭም” በጣና ሀይቅ ላይ የተደቀነ አደጋ ሆኗል፡፡ የችግሩ ሁሉ ቀስት የሚያመለክተው ወደ ተማረው ይመስለኛል፡፡ በእውነት ተማርን ለምንል ትልቅ ፈተና እየመጣብን ነው፡፡ አንዳንድ ደፋር ሰው “ወይ ፍረድ ወይ ውረድ” እንደሚለው አይነት እንዳይሆን እፈራለሁ፡

ወራሪ አረም (invasive weeds) ተብለው የሚታወቁ የተክል ዘሮች በሽ ናቸው፡፡ በያንስ ሶስቱን በጥቂቱ እንመልከት፡፡

በሀገራችን በጣም የሚታወቀው በአፋርና ድሬደዋ አካባቢ ተሰራጭቶ የሚገኘው በተለምዶ “ወያኔ ዛፍ” በሳይንሳዊ አጠራሩ Prospis juliflora (ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ) ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡ የዚህ ዛፍ ምንጩ ወደ ደቡብ አሜሪካ ነው፤ ሜክሲኮ አካባቢ፡፡ ይህ ተክል ምርጥ የምግብ ምንጭ ነው፡፡ በሜክሲኮ ከመጠን ያለፈ ጥቅም ላይ በመዋሉ ሊጠፋብን ይችላል ብለው እንክብካቤ እያደረጉ እንደሆኑ በአንድ ጥናት ላይ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ ፕሮሶፒስ ለእኛ መርገም ለሜክሲኮ በረከት ነው፡፡

ሌላው ወራሪ የተባለው አማራንተስ(Amaranths) ነው፡፡ አማራንተስ የእንግሊዝኛ ስሙ ነው፡፡ በሀራችን በተለያዩ ስሞች ይጠራል፡፡ የፈረንጅ ጤፍ፣ አሉማ፣ ሊሻሊሾ፣ ገገብሳ የሚሉና ሌላም ብዙ ስሞች አለት፡፡ በነገራችን ላይ ተክሉም ዘረ ብዙ ነው፤ ወደ 60 የሚጠጉ ዝርያዎች አሉት፡፡

ይህ አረም ምንጩ ደቡብ አሜሪካ አካባቢ ነው፡፡ እዚያ ያሉ ህዝቦች እኛ ለጤፍ የምንሰጠውን ክብር ያህል ለአማራንተስ ይሰጡት ነበር፡፡ ግን “ቀኝ ገዥዎች ወደ ቦታው በሄዱ ጊዜ የሆነ ባህል እናጠፋለን ብለው ይህን ምርጥ እህል ከእህል ተራ አወረዱት” ይሉናል ታሪክ አጥኝዎች፤ ያሳዝናል፡፡

በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋም ይሁን በግብርና ሚኒስቴር(እርግጠኛ መሆን አልቻልሁም) ባዛር አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚያ ባዛር አንድ ድንኳን ውስጥ የተለያዩ የእህል ዓይነቶች በብልቃጦች እየሆኑ ተደርድረዋል፤ ከድርድሮች ውስጥ በአንዱ ብልቃጥ አማራንተስ (ቀዩ) ፍሬ ተሞልቶ ተቀምጧል፡፡ ለማስረዳት ቦታውን የያዘቸውን ልጅ ስለምንነቱ ስጠይቃት “ወራሪ አረም ነው” ነበር ያለችኝ፡፡ ወራሪ አረም መባሉን ያን ጊዜ ተረዳሁ፡፡ በእርግጥ ይህ ተክል በጫካና በማሳ ዳር የሚበቅል ችግር ተቋቋሚ፣ ምርታማ፣ በተባይ በብዛት የማይጠቃ ልዩ ሰብል ነው፡፡ በደቡብ ክልል በተለይ በሚኒት ማህበረሰብ በደንብ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ እህልነቱ ከጤፍ ጋር ሲወዳደር ብልጫ ያለው ነው፡፡ አማራንተስ የማይበቅልበት ቦታ የለም በተለይ ሞቃታማ በሆኑ ቦታዎች ለጉድ ይበቅላል፡፡

“ዳን ቸርች” የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በአንድ ወቅት ሴሚናር አዘጋጅቶ ነበር፡፡ አማራንተስንና ኩይኖዋ የተባለውን አዝርት በኢትዮጵያ ለማላመድና ለማምረት፡፡ እኔም ተካፍዬ ነበር፤ አሁን ግን ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ አላውቅም፡፡እንዲህ አይነቱ ነገር መበረታታት አለበት፡፡

ዶክተር እንዳለ አማረ ይህን ጽሁፍ የምታነብ ከሆነ ስለ አማራንተስ ጥሩ መረጃ ትሰጠናለህ ብዬ ስለማስብ እንድትጽፍና መረጃውን እንድታካፍለን አደራ እልሀለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ብዙ ጥረት እንዳደረግህ ስለማውቅ ነው፡፡

አሁን ደግሞ ወደ ዋናው ትኩረቴ ወደ ሆነው እንቦጭ ልግባ…….

እንቦጭ በሳይንሳዊ ስያሜው Eichhornia crassipes ይባላል፡፡ ሕይወታዊ ሀብት(bioresource) መሆኑን ሳልረሳ ይህ ተክል ለእኔም አሸባሪ ሆኖብኛል፡፡ ለምን ብባል፣ እያጠፍ ያለው ትልቁ ሀይቃችንን ጣናን ነው፡፡ ጣና ብዙ ነገራችን ነው፡፡ ጣና የጥንታዊ ገዳማት መገኛ መንፈሳዊ ቦታችን ነው፡፡ ጣና የሃይል ማመንጫ ውሃ ቋት ነው፡፡ ጣና የመዝናኛና የቱሪስት መሳቢያ ትልቅ ገመድ ነው(ቱሪዝምና ዲያስፖራ የኢኮኖሚው ዋልታ እየሆኑ እንደሆነ እያየሁ ነው)፡፡ ጣና በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብዙ ፍጥረታትን(በተለይ ዓሳዎችን) የያዘ የብዝሀ ሕይወት በረት ነው፡፡ ጣና የአካባቢውም ሆነ የሀገሪቱ ህዝብ ታላቅ ተስፋ ነው፡፡ የእንቦጭን ጥፋት ከዚህ ሁሉ ነገር ጋር ይያያዝብኛል፡፡ ለችግሩ ቶሎ መፍትሄ መምጣት እንዳለበትም ይሰማኛል፡፡ ለአረሙ በቶሎ መፍትሄ ካልተበጀለት ጣና ታሪክ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከጣና ጋር የተቆራኙት ተስፋዎችና በረከቶችም እንዲሁ እንደ ጉም በነው ይጠፋሉ፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ ውድመት ነው፡፡

ከበረታን በዚህ መጥፎ አጋጣሚ ውስጥ በረከትም የሚገኝ ይመስለኛል፡፡ በረከቱ የሚገኘውም በአረሙ አወጋገድ ላይና ለአረሙ አገልግሎት የሚውልበት ስራ ስንፈጥር ነው፡፡

በአወጋገዱ ላይ ጥቅም መፍጠር ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡ አለበለዚያ ከችግሩ በቀላሉ የምንወጣ አይመስለኝም፡፡ አወጋገዱ እንዴት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል? የሚለው ትልቁና ከባዱ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ እዚህ ላይ መላምቶችን መደርደር ይቻላል፡፡ ለእኔ የሚታዩኝን ልጠቁም፡

አንደኛ፣ በዚህ ተክል ላይ ጠለቅ ያሉ ምርምሮች የተሰሩ አይመስለኝም፡፡ ጥልቅ ምርምሮች መሰራት አለባቸው፤ ለዚህ ደግሞ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ሀላፊነቱን ከተጠያቂነት ጋር መውሰድ አለበት፡፡

ጥናቶች የሚያተኩሩባቸው ነገሮች ደግሞ፤ ተክሉ(አረሙ) ለምግብነት የሚውልበትን መንገድ ማዘጋጀት ነው፡፡ በተለይ ለከብት፣ ለዶሮና ለአሳማ የሚሆን ምግብ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ ለዚህም በአካባቢው የመኖ ማቀነባበሪያ ፍብሪካዎችን በጥንቃቄ መትከል፡፡ በተለይ ለሰው ምግብ የሚሆንበትን ዘዴ እንደ ዋና ግብ አድርጎ መያዝ፡፡ ለምግብ ፍጆታነት ሲባል የዘረመል ጥናትንም ሊያካትት ይችላል፡፡ በዚህም የተክሉን ተፈጥሮ ማጥናትና ጠቃሚ ነገሮች እንዲኖሩት ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ ከሆነ ቶሎ የመባዛት ባህሪው

አጥፊነት ሳይሆን በረከት ይሆናል፡፡ በ2042 ዓ.ም ወደ 200 ሚሊዮን እንደምንጠጋ ትንቢታዊ ጥናቶች እያመላከቱ ነው፤ እንደዚህ ላለው ወፈሰማያት ህዝብ እንደ እንቦጭ በቶሎ የሚራባ ተክል ያስፈልጋል፡፡

ሁለተኛ፣ ለነዳጅ ማማረቻነት መጠቀም፤ ባዮጋዝም ሆነ ከሰል ማማረት ይቻላላ( ለምሳሌ ብሪኬት)፡፡

ሦስተኛ፣ ለማዳበሪያነት፤ ለልበስና ለሌሎች ቁሳቁሶች መስሪያነት መጠቀም፡፡

ሌላው ጥያቄ ጥናቶች አስኪደርሱ ምን እናድርግ? የሚለው ነው፡፡

እንደ 2, 4 D- ያሉትን ፀረ አረም ኬሚካሎች መጠቅም ይቻል ይሆናል፡፡ ይህ ግን ለውሃ አካላት ተመራጭ አይመስለኝም፤ የውሀውን ስነ ምህዳር ሊረብሸውና ያልተጠበቀ ሌላ ውድመት ለያመጣ ይችላላ፡፡

በሀይቁ ዙሪያ የሚካሄደውን የግብርና ስራ ማጥናትና ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ሌላው የመፍትሄው አካል ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ፣ አርሶ አደሮች ማዳበሪያ በሚጠቀሙበት ወቅት ማዳበሪያው በጎርፍ እየታጠበ ወደ ሀይቁ በሚገባበት ወቅት አረሙ የሚያፋፋውን ምግብ አገኘ ማለት ነው፡፡ በዚህም በኩል የሚሰራ ስራ ይኖራል፡፡

ሌላውና የተሻለው ነገር በጉልበት(በእጅ ወይም በመሳሪያ ) ማስወገድ ነው፡፡ ለዚህ ችግር የሚሆነው ለሰራተኛ የሚከፈል ገንዘብ እጥረት ነው፡፡ የሰው ሃይል ችግር የሚኖር አይመስለኝም፡፡

ለዚህም መፍትሄ የምለው፣ ያገባኛል የምንል ሁሉ መረባረብን ነው፡፡ የክልሉ መንግስትና የፌደራሉ መንግስት በጀት በጅተው በቂ የሰው ሃይል ቢያሰማሩ ጥሩ ነበር፡፡ ካልሆነ ግን የችግሩ ጥልቀት የተገነዘበውና አቅም ያለው ሰው ልክ ለታላቁ ግድብ እንዳወጣን ሁሉ በዚህ ስራ ለሚሰማሩ ሰዎች ክፍያ የሚሆን ገንዘብ ማዋጣትና ቶሎ ስራውን ማስጀመር፡፡ እኔ በበኩሌ በደስታ ፈቃደኛ መሆኔን ልገልጽ እወዳለሁ፡፡ ለዚህ አረም ማጽዳት ለጉልበት ስራ የሚከፈል የወር ደመወዜን እከፍላለሁ፡፡ ይህንም የማደርገው “ጣናን እናድን” ወይም ሌላም ሊሆን ይችላላ ማህበር ተቋቁሞ ስራውን ሲጀምር የመጀመሪያው ከፍይ እሆናለሁ፡፡
 
====================000========================

Lake Victoria water hyacinth weevils (Neochetina spp. ) on common water hyacinth .


 

እምቦጭ አረም በቪክቶሪያ ሐይቅ፤

የእምቦጭ አረም በአፍሪካ ትልቁ የሆነውን የቪክቶሪያ ሐይቅ መውረር የጀመረው በ1980ዎቹ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ የእምቦጭ አረም (Water hyacinth) ከ1992 እስከ 1998 ባለው ጊዜ የቪክቶሪያ ሐይቅን ቀላል የማይባል ክፍል መሸፈን ችሎ ነበር፡፡ በ1998 እ.ኤ.አ ከ20 ሺህ ሔክታር በላይ (77 ስኩየር ማይል) የሚሆነው የሐይቁ ክፍል በእምቦጭ አረም ተይዞ ነበር፡፡ እምቦጭ ሐይቁን ከመውረሩና የአካባቢውን ብዝሃ ሕይወት ከማዛባቱ በተጨማሪ ለወባ ትንኝና ለብላሃርዚያ በሽታ አምጭ ተኅዋስ ሺስቶሶማዎች መራቢያ በመሆን የጤና ጠንቅም ሆኖ ነበር፡፡

የታንዛኒያ፣ የኬንያና የኡጋንዳ መንግሥታት በመተባበር ከ1998 ጀምሮ ሐይቁን ለማዳን ተረባረቡ፡፡ የምዕራብ ለጋሽ አገራትም ሐይቁን ለማዳን በገንዘብና በቴክኖሎጅ ጭምር ረድተዋል፡፡ በ2000 መግቢያ ላይ የእንቦጭ አረምን ማጥፋት ባይቻልም መቆጣጠር ችለዋል፡፡

በቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ ያለውን የእንቦጭ አረም ለመቆጣጠር የተንሠራፋውን አረም በተለያዩ ቴክኖሎጅ አገዝ መሣሪያዎች ማረም (መንቀል)፣ Neochitina weevil የተባሉ አንበጣ መሣይ ነፍሳትን በማራበት በአካባቢው መበተንና እንቦጭ አረሙን ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማዋል የመሣሰሉ ዘዴዎች ነበሩ፡፡ መንግሥታቱ ከእንቦጭ አረም ባዮጋዝን ጨምሮ የተላያዩ ነገሮችን ማምረትም እንደመፍትሔ ወስደውታል፡፡

እምቦጭ አረምን መቆጣጠር ቢቻልም ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ብዙም ስኬታማ የሆነ አገር የለም፡፡ የቪክቶሪያውን ጉዳይ ስናየው በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረ ቢሆንም በ2007 አካባቢ መልሦ ሐይቁን አልብሶት ነበር፡፡ መንግሥታቱ እንደገና አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ መልሰው ወደነበረበት በመመለስ አስጊ እንዳይሆን አድርገውታል፡፡

ወደኛው ጣና ስንመጣ ሐይቁ በእምቦጭ መወረር የጀመረው በ2004 ዓ.ም (የጣና በለስ ኃይል ማመንጫ በተሠራ ማግስት) ሆኖ ይህን ያክል ሲስፋፋ ዩንቨርሲቲዎችም መንግሥትም ከዚህ ግባ የሚባል እርምጃ አልወሰዱም፡፡ አረሙ በእኛ አገር ብቻ የተከሠተ አዲስ ክስተት ቢሆን ምርምር እስኪደረግ ድረስ ብዙ ዘመን መውሰዱ ላይደንቅ ይችል ነበር፡፡ በቅርብ ርቀት እነኬንያና ኡጋንዳ የቪክቶሪያ ሐይቅን ለማዳን የተጠቀሙበትን ልምድ በመቅሰም በቶሎ አረሙን መቆጣጠር ያን ያክል ከባድ የሆነ ጉዳይም አይደለም፡፡ ችግሩ ያለው ከሕዝብና ከአገር የተጣላ ሥርዓት ስላለን ብቻ ነው፡፡
 

%d bloggers like this: