“ሰው ምን ዐይነት ነው? ምንን ይመስላል?” ቢባሉ፣ ብልሂቷ መለኩሴ “ኑሮውን!” አሉ!

13 Jul

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)

ሪፖርተር በረቡዕ ዕትሙ (ሐምሌ 5፣ 2009)፣ የሕወሃት አስተዳደር ለአንድ መቶ ሺሕ ስደተኞች የሥራ ዕድል ሊሰጥ ነው በማለት የዘገበው ዜና ሃገሩን እንደሚወድ ዜጋ — እውነት መሆን እንኳ ባይችል — እንደ ሃገር ምን ያህል ስለ ማዝቀጣችን ተራኪ ከመሆኑ ባሻገር፥ የዕለት ኑሮውን ለማሸነፍ ቀን ከማታ ቀና ደፋ የሚለው መሃይም ተደርጎ በሚወሰደው ሕዝባችን ስሜት ውስጥ የሚኖረው ትርጉም በጣም አሳስቦኛል።

ይህንን እዚህ ሳሰፍር፣

(ሀ) በእምነት ደረጃ እነዚህ ስደተኞች ሰው በመሆናቸው ብቻ ያላግባብ እንዳይጎዱ ማናቸውም ጥረት መደረግ አለበት ብዬ አምናለሁ፤

(ለ) አያሌ ወጣት ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ በዓለም ዙሪያ በስደት ተቀባይነት ለማግኘት፣ ተምረው ሥራ ይዘው ራሳቸውን ሊረዱና ዘመዶቻቸውን ሊደግፉ እንደሚሹ፣ ለዕድሉም በየቀኑ ሲሯሯጡ የሰዎች ፊት እንደሚገርፋቸው አውቃለሁ፤ ከኛ በተሻሉ ሃገሮች እንዲሳካላቸውም ምኞቴ ነው!

በሃገራችንም በኩል፥ ቢቻል ራሳችንን ከችግሮች አላቀን፣ አለያም አቃለን፡ ለሌሎች ተገን ለመሆን በጎ ፈቃዱ ቢኖረን ይደገፋል። ይደነቃል። ነገር ግን የሃገራችን ሁኔታ እየተንቦጫቦጨ — ጥቂት የውጭ ዕርዳታና የተሻለ ድጎማ (Sustained ODA support) ለማግኘት በተሰላ ዘይቤ — በኢትዮጵያ ላይ መሸከም የማትችለውንመጫን፡ በተለይም ተጨባጩ ዕውነታ ሊያስተናግደው የማይችለውን የውጭ ፖሊሲ ዓላማ ለመግፋት መውተርተር ውጥረት ጋብዞ ተንገዳግዶ መውደቅና መሰበርን ሊያስከትል ስለሚችል፡ ማምከኛው ሊያስቸግር ይችላል።

እ.ኤ.አ. በ1970ዎች አናት ላይ ለደቡብ ሱዳን አናኒያ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ድጋፍ እየጨመረ መጥቶ፡ ወደ 1972 የአዲስ አበባ ስምምነት ጉዞ ሲታሰብ፥ በጦርነቱ የተፈናቀሉ የደቡብ ሱዳን ዜጎች ተማሪዎችና ሌሎች ስደተኞች አራት ኪሎ ሆቴሎችና የወጣት ወንዶች ክርስቲያን ማኅበር (YMCA) ውስጥ ሁሉ እንዲያርፉ በመደረጉ፣ አንድ ስሞን የአራት ኪሎን መልክ በመቀየራቸው የነበረውን የሕዝብ መንተክተክ መንግሥት በመገንዘቡ ለጥቂት ጊዜ ወደ ኮልፌና ሌሎች አካባቢዎችም በመላክ ለማቀዛቀዝ የተደረገውን ጊዜያዊ እርምጃ አስታውሳለሁ!

ሃገሪቱ አሁን ባለችበት ያልተመቻቸ ሁኔታ፣ ዜጎችስ እስከ መቼ እንደ መንደር አህያ በየቀኑ መጫኑን ሊታገሡ ይችላሉ ብሎ ሕወሃት ማሰብ ቢችል፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያንሰው እንጂ ይበዛበታል ብዪ አላምንም!
 

የዓለም ባንክና የእንግሊዝ ጥንስስ

ባለፈው መስከረም ወር የሕወሃት አስተዳደር ከአውሮፓ ኅብረት (EU)፣ የአውሮፓ የመዋዕለ ንዋይ ባንክና (EIB) ከዓለም ባንክ በሚሰጥና የእንግሊዝ መንግሥት ዕርዳታ ታክሎበት ለ100 ሺህ ስደተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ የመፍጠርና ኢንዲስትሪ ፓርኮቹ የሚቋቋሙበትም ዓላማ ጭምር ይህ መሆኑን ቢቢሲ በዜና መልክ ማሠራጨቱን አስታውሳለሁ።

Theresa May said the $500m project would provide help to poorer countries housing refugees (GETTY IMAGES via BBC) Image caption

ስደተኛ የሚባል ከየትም ይሁን የት ግዛቷ ውስጥ ከሚሠፍርባት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ፍቺዋን (Brexit) የመረጠችው እንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴረሳ ሜይ ስደተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሠፍሩ የተለመደውን የእንግሊዝን እጅ የመጠምዘዝ ችሎታቸውን ሥራ ላይ ካዋሉ በኋላ፣ ወደ አውሮፓ የሚፈልሰውን ስደተኛ ለመግታት የምታስችል ኢትዮጵያ ዐይነተኛ ሞዴል ሃገር እንደምትሆናቸው፣ ሠቅጠጥ ሳያደርጋቸው ነበር ኒው ዮርክ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉባዔ (United Nations Refugee Summit) ላይ ያስታወቁት፦

    We must ensure refugees can live with dignity and self-sufficiency, as close as possible to their home countries, to deter them from making dangerous onward journeys, and to enable them eventually to return home and rebuild.

    That means helping host countries to provide education and employment opportunities…As the president of Ethiopia [Not even aware of her counterpart’s portfolio?] said, as part of this, the government of Ethiopia will now allow refugees to work outside of camps, benefitting from some of the 100,000 jobs that will be created.

    It is a model for how we can support host countries create jobs for their own people and refugees – a mutually beneficial solution and one we must replicate.

የኢትዮጵያንም ሆነ የእንግሊዞችሁንና ሌሎቹ የታከሉበትን ወሳኔ፡ እንደ ግለሰብም፡ ከሙያና ፖለቲካውም አንጻር በሚገባ ተመልክቸው፣ ኅሊናዬ እንዲቀበለው ለማድረግ ያደረግሁት ጥረት አልተሳካልኝም። ሪፖርተር እንደዘገበው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ 800 ሺሕ ያህል የጎረቤት ሃገሮች ስደተኞች በተለያዩ የሃገሪቱ የድንበር አካባቢዎች በተከለሉ ካምፖች (አራት መጠለያዎች በትግራይ፣ ሶማሌ ክልል ዶሎ አዶ (Dolo Ado) እንዲሁም በጋምቤላ ደግሞ 350 ሺሕ ያህሉ የደቡብ ሱዳንን ቀውስ ሸሽተው የፈለሱ በጋምቤላ የስደተኛ ማቆያ ጣቢያዎች ቲየርኪዲና እንጐንዬል (Tierkidi and Nguenyyiel) ውስጥ የተጠለሉ መሆናቸው ታውቋል።

በየሃገሮቻቸው በደረሱባቸው ችግሮች ምክንያት የተሰደዱትን እነዚህን የጎረቤት ሃገሮች ወንድሞች፣ እህቶችና ሕጻናት ኢትዮጵያ ለመርዳት መወሰኗ ያስመሰግናል። ሃገራችን ያለባትን ዓለም አቀፍ ግዴታዎችዋን ለመወጣት የምታደርገውን ጥረት የሚያመላክት ብቻ ሳይሆን፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእምነቱና በባህሉ ርኁርኅ፣ እንግዳ ተቀባይና ያለውን ተካፋይ መሆኑን የሚያድስ ምሥክረነት ተደርጎ ቢተረጎም ተቀባይነት ይኖረዋል።

በተለይም ከውጭ ሆነው ይህንን ለሚመለከቱትና በሃብታም ሃገሮቻቸው ዓለም ባንክ ውስጥ ሆነው፣ ከዚያም በዘለለ መንግሥቶቻቸውም ውስጥ ሆነው ያሰተዳደሮቻቸው የሰደተኛ ፖሊሲዎች ያሳፈራቸው ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም እንደነ ቻንስለር አንጌላ መርከል ዐይነት የሃብታሟ ጀርመን መሪ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የመካከለኛው ምሥራቅ ስደተኞችን ሃገራቸው ውስጥ ተቀብለው በማስተናገድና የውስጥ ባለሥጋቶችና ርዕዮተ ዓለማዊ ተጻራሪዎቻቸው በመሰባሰብ እንደገና የመመረጥ ዕድላቸውን ለማደናቀፍ እንዲሰባሰቡና እንዲጠናከሩ ዕድል መፍጠሩ ሳያሳስባቸው፡ ለእምነታቸው በቆሙ መሪዎች ዘንድ ይህ የኢትዮጵያ እርምጃ በከበሬታ ይታያል ብለን መገመት እንችላለን።
 

በየዓመቱ እየሠፋ የመጣው የኢትዮጵያውያን ሥራ አጥነት

ከሁሉ በፊት ግን፣ ያ ከበሬታ የፖለቲካ ካፒታል (political goodwill) ቢሆንም፣ በሃገራችን በሁሉም የዕድሜ ክልል — ማለትም ከ15-19, 25-29, 30-34 እና 35-39 — ውስጥ ያሉ ዜጎች ሥራ አጥነትን መቅመስ የሚያስገድድ ሁኔታ ሃገሪቱ ውስጥ መስፋፋቱ ግድ ሆኖአል። የዚህ ትርጉም ዛሬ አንድ የኢትዮጵያ ዜጋ ትምህርቱን ሲጨርስ — ከዘመኑ ንጉሣውያን ቤተሰብ ውጭ ለሆኑት — ሥራ የማግኘት ዕድሉ በየወቅቱ እየተመናመነ የሚሄድበት ዘመን ላይ እንገኛለን
በዚህም ምክንያት ጥንድ ዕድገት (double-digit growth) ስታሳይ የነበረችው ኢትዮጵያ ለራሷ ልጆች የጠጠር መንገድ ሥራ (Cobble-stone) ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሁሉ ትልቁ ግኝቷ አድርጋ መኩራራቷ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው — እርሱም በሙስናና በዘር ምልመላ እስከተጨማለቀበት ጊዜ ድረስ!

ከላይ የተጠቀስውን ሥራ አጥነትን አስመልክቶ፡ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ የ2014 መረጃ ይህንኑ ግልጽ ከማድረጉ ባሻገር፡ በተለይ ከ19-29 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ዜጎቻችን ከተሞቻችንንና ገጠሮቻችንን ባጨናነቁበት ሁኔታ ላይ ሆነው ሣለ — ዜጎቻችን እንደ እንስሣ በተጨፈጨፉበት ሙት ዓመት ዋዜማ — የሕወሃት አስተዳደር የዚህ ዐይነት ስምምነት መፈራረሙ እጅግ ይረብሻል!

ምን እንበለው? የራሱ ድረሱልኝ እሪታ፣ ወይንስ የሃገሪቷን ዳር ድንበር ቆርሼ ለሱዳን ከሰጠሁ ወዲህ እንኳ ተቃዋሚና ዲያስፖራ ሁሉ ተጯጩሆ ሁኔታውን ከመቀበል ውጭ ለውጥ አያመጣም ብሎ ይሆን? ከሁሉም የከፋ፣ ሕወሃት እስከዛሬ ለፖለቲካ ፍጆታውና የዕርዳታ ገቢ ስደኞች ካምፕ አስቀምጦ ያቆያቸውን አሁን በኢንዱስትሪ ፓርክ የሚፈጠሩት የሥራ ዕድሎች ተቋዳሽ እንዲሆኑ የዕቅዱ አካል ማድረጉ፥ እጅግ ሚዛናዊነት የጎደለው አስተሳሰብ ይመስለኛል።

ብዙ የተደሰኮረለት የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተመረቀ ዕለት የትግራይ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አዲስ ዓለም ባሌማ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ለትግራይ ነዋሪዎች ብቻ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ማለት እንዳልሆነ ማብራራታቸውን ይኽው የሪፖርተር ዜና ጠቆም አድርጎታል።

ይህ ጉዳይ በጥሞና ሊታይ ይገባል! ድህነት ኢትዮጵያውያንን በሁሉም መልኩ የተጠናወተን ሰብዓዊ ፍጡሮች እንጂ መለኮታዊ ተፈጥሮ ስለሌን፣ በሁለንተናዊ መልኩ ኑሮአችንን የምንመስል ሰዎች ነን! አሁን ለተሰደዱ — ልክ እንደ ሕወሃት ሁሉ — የየሃገሮቻቸው ፈላጭ ቆራጮች በፈጸሙባቸው ወንጀሎች ምክንያቶች የተሰደዱትን፣ በመጀመሪያ አንድ መቶ ሺህዎች አፍሪካውያንን (ሶማሌዎችን፡ ደቡብ ሱዳኖችንና ኤርትራውያን) በኢስንዱስትሪውና በግብርናው ዘርፍ ሥራ ለመሥጠት ተውስኗል!

የሚገርመው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ኔው ዮርክ ላይ የተስማሙት 30 ሺህ ስደተኞች ሥራ እንደሚይዙ ነበር — ከዚያ ወዲህ ባለቤት በሌላት ሃገር ላይ ያ ቁጥር ወደ 100 ሺህ ከፍ ተደርጓል— ከላይ የተጠቀስው የቢቢሲ ዜና እንዳመለከተው። ኢትዮጵያ የሕዝብ ድምፅ የሚከበርባት ሃገር ሆና ምርጫ ቢካሄድ፡ ድምጼን በዚህ ዐይነት ፓርቲ ላይ አንደማላባክን ካሁኑ ሊታወቅ ይገባል — ሕወሃቶችም በልባቸው ቀድሞ ነገር ማን ዕድሉን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሠጥቶ በማለት ለጊዜው ራሳቸውን ከእያንዳንዱ ስህተቶቻቸው በኋላ ለጊዜው ያጽናኑ ይሆናል! ይሁን እስቲ!

ልብ ሊባል የሚገባው፥ ይህ ውሣኔ —ሪፖርተር እንደዘገበው — የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ለመሆኑ እንደሚከተለው ተገልጿል፦

“ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ዘጠኝ ነጥቦችን የያዘ ዕቅዳቸውን እንዳቀረቡ የዓለም ባንክ ሰነድ የገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አሥር በመቶ የሚሆኑት ስደተኞች ቀስ በቀስ ከካምፕ ወጥተው እንዲኖሩ ማድረግ፣ እስከ 100 ሺሕ ስደተኞችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲቀጠሩ ማድረግ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሥር ሺሕ ሔክታር የእርሻ መሬት በማቅረብ በእርሻ እንዲተዳደሩ ማድረግ፣ እስከ 213 ሺሕ ለሚደርሱ ስደተኛ ተማሪዎች የትምህርት ዕድል መስጠት፣ ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ እንዲያገኙ ማድረግ፣ ከ20 ዓመታት በላይ የኖሩት ሕጋዊ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲፈጥሩ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል፡”

ሃገራችን ዲሞክራሲያዊ አሠራር ስለማትከተል፣ እርሳቸውም ሆኑ ፓርላማው ቢወስነው አንዱ የሌላው ‘ተቀጣሪ’ ስለሆነ፣ በሕገ መንግሥታዊ አመለካከትና አሠራር የፓርላማው አባላት የሕዝብ ውክልና አለብን ብለው ለሃገር ሲሉ የሚያደርጉት ነገር ባለመኖሩ፡ ማን ወሰነው ማንም ለውጥ አያመጣም። ነገር ግን ይህ ብዙ አሳሳቢና ያልታሰቡ ችግሮችን ስለሚያስከትል፣ ነገሩ በድብቅ ከዓለም ባንክ ባለሥልጣኖች በእንግሊዝ መንግሥት የጀርባ ግፌት በሰብዓዊ ርኅራሄነት ስም የተደረገው ስምምነት ውንብድና ነው፡ ሕጋዊ አሠራር ባለበት ሃገር፡ ይህ ጉዳይ ኅብረተሰብ ሙሉ ሊመክርበት የሚገባ የፖለቲካ ጉዳይ እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ — በአንድ ግለሰብ ብቻ — መወሰኑ ስህተት ነው።

እስከ መቼ ነው ይህቺ ሃገር እንዲህ መቀለጃ የምትሆነው?

ነገ ለሚከተለው ችግር ሌላ የ’ጥልቅ ተሃድሶ’ ዳንኪራ ለመረገጥ ነው? ወይስ ሕዝቡን እንደገና በሕዝቡ ብሔራዊ ስሜት እያሾፉ በፖለቲካ ድለላ ለጦርነት ለመልመል?
 

የሕዝባዊ አመጹ መሥዋዕታት ሙት ዓመት ዋዜማ

በቅርቡ በሃገራችን የተፈጸመሙትን ኢሰባዊ ድርጊቶችና መንግሥታዊ ጭካኔዎች፡ ማለትም ከሕግ ውጭ የሆኑ የዜጎችን እሥራትን በየቀኑ በማካሄድ የሚታወቅ፣ በእሥር ቤቶች ደራሽ የሌላቸውን ወንድ ሴት ኢትዮጵያውያኖች ሰብዓዊ ክብራቸውን ለማዋረድ መብቶቻቸውን በመርገጥ ሠቆቃዎችንና ግድያዎችን በየቀኑ የሚፈጽም መንግሥት የተሰደዱ ሶማሌዎችን፡ ደቡብ ሱዳኖችንና ኤርትራውያንን ሰው የሚያደርጋቸውን መተዳደሪያ ሰጥቶ ሰብዓዊነታቸውን ለማስከበር የተደረገ ነው የሚለው ውሃ አይቋጥርም!

ይህ በኢትዮጵያ ጉሮሮ ውስጥ በገንዘብ ዕርዳታና ለሕወሃት በሚስጥ ድጎማ የተገፋ ጥቂት ቆይቶ ኅብረተሰባችን ውስጥ የሚርመጠመጥ መርዝ እንዳይሆን እሰጋለሁ! ምክንያቶቼን ልግለጽ:-

አንደኛ፡ ሕወሃት ለዚህ ዐይነት ፍጹም ሰብዓዊ ተግባር ብቃትም ሆነ እምነት የሌለው በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ተካሄደ ሸፍጥና ፕሮፓጋንዳ ነው!

ሁለተኛ፡ ምንደነው ዓላማው? ሕወሃት ተክባሪ ሆኖ ነፍሰ ገዳይነቱና ጥቃቱ እንዳይጋለጥ ዘራፊነቱን የሚያጋልጡትን ለማስጠላት ታቅዶ ከሆኑ አይሳካም፤ የለም ይቻላል የሚሉ ካሉ፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተመቻቸና ሌላው አንጌላ መርከል ነው ብለው የሚያስቡ ካሉ ተሳስተዋል! በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በሕወሃት የተጫነበትን የራሱን ቁስል እያዳመጠ ነው!

ሶስተኛ፡ ከውጭ የተጫነው ‘ግዴታ’ (ጥቂት መቶ ሺዎች ዶላሮች/ምናልባትም ሚሊዮኖች ማማለያ ሆኖ) የተደረገ እንጂ የሕወሃት አስተዳደር ለስደተኞቹ ተቆርቁረው የበጎ ፈቃድ ማረጋገጫ አድርጎ ለመውሰድ አዳጋች ነው!
በኢትዮጵያ ሕዝብና በመንግሥት ተብየው መካከል መቆራረጥ በመፈጠሩ፡ ይህንን የመሰለ በሕዝብና መንግሥት መካከል መተሳሰር መቀራረብ አስፈላጊነትን እርምጃ ሕወሃት ሊወስድ የሚያስችል የፖለቲካ አቅሙና የሞራል ብቃቱ የለውም!

አራተኛ፡ እስከዛሬ የታዘብናቸው ሁኔታን መሠረት በማድረግ አንዱ ሕወሃት ይህንን ሰብዓዊ እርምጃ ለማስመሰል ቢሞክርም፡ መሠረታዊ ዓላማው የሚያተኩረው ኤርትራውያን ላይ ነው። አሁንም ሃገሪቱ ውስጥ በስለላ ተግባር እንደሚጠቀምባቸው ከውስጥ አዋቂዎች በየጊዜው የሚሾልኩ መረጃዎች ሲያመለክቱ ስለነበር፡ ሱማሌዎቹና ደቡብ ሱዳኖቹ ለማስመያ የተጠቀሱ እንጂ ምንም ዐይነት ሥራ እንደማይሰጣቸው ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

አምስተኛ፡ ኢትዮጵያ ብትፈልግ ትፈነጋገል ብሎ በልቡ የወሰነው የአውሮፓ ማኅበረሰብ፡ የኢትዮጵያንና የጎረቤት ሃገሮች ፈላሽ ስደተኞችን ከአውሮፓ ለመቀነስ የወጣ ስትራቴጂ እንደመሆኑ፡ በቀላሉ ሊማለል የሚችለው ሕወሃት ነው ብለው እንግሊዞቹ ስላሰቡ ነው በቅድሚያ ይህንን ሙከራ በማካሄድ ላይ ያሉት።

ለትምህርታዊነቱና ትዕዝብቱ፣ እንደ ሕውሃቶች በዚህ መሰል ሁኔታ በየጊዜው በችግሮቻቸው ብቻ ተገፍተው እንዲህ ያለ እርምጃዎች ወስደው፡ ሕዝቦቻቸው ለአራዊት የጣሏቸው መንግሥታትን ከታሪክ ማስታወሱ ይጠቅማል!
 

World Bank document
 

%d bloggers like this: