ሃገራችንን ሙልጭ አድረገው የጋጧት እየተዝናኑ፡ ሕወሃት የ210 ባለሃብቶችን ንብረት አገድኩ ይለናል መፍትሄ ይመስል!

10 Aug

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

አዲስ አበባ ነሃሴ 4፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከሰሞኑ በሙስና ተጠርጥረው ጉዳያቸው በሕግ እየታዩ ካሉ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች፣ ባለሀብቶችና ደላሎች ጋር ግንኙነት ያላቸው የ210 ግለሰቦችና ተቋማት ንብረት ታገደ።

እንዲሁም 15 የተጠርጣሪዎችና ከተጠርጣሪዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ኩባንያዎች ንብረትም ታግዷል። ከታገዱት መካከልም፦

  –   አሰር ኮንስትራክሽን
  –   ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን
  –   ቲና ኮንስትራክሽን
  –   ዲ ኤም ሲ ኮንስትራክሽን
  –   የማነ ግርማይ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ
  –   ትራንስ ናሽናል ኮምፒውተር ትሬዲንግ
  –   ሀይሰም ኢንጂነሪንግ አክሲዮን ማህበር
  –   ከማኒክ ትሬዲንግ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር
  –   ጆንግ ሊንግ ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግና ሌሎችም ይገኙበታል።

ልብ ብሎ ለተከታተለ፣ ሃገራችን በአሁኑ ወቅት ባለፈው ዓመት ተከታይ የሆነ ቈጣ እያሰተናገደች ትገኛለች። ምናልባትም በሚዲያ በተደጋጋሚ የሚነገርው በየወረዳው በየተለይም አማራና ኦሮሚያ ውስጥ ያለው የሥራ ማቆም አድማ ቢሆንም፡ ችግሩ ውስጥ ለውስጥ የሚነድ የሕዝብ ከአስተዳደሩ ብልግና ጋር የተፋጠጠ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።

ይህም ባልታሰበ ፍጥነት መልኩን ሊቀይር የሚችል ዐይነት ነው!

የፖለቲካ እሥረኛው መረራ ጉዲና ከሕግ ውጭ በሰንሰለት ታሥረው (ተስፋ ኒውስ ፎቶ)

ለምሣሌም ያህል ኦሮሚያ ውስጥ ከሥራ ማቆሙ አድማ ጎን ለጎን አንገብጋቢ ሆኖ እየመጣ ያለው፣ ሕውሃት ኦሮሞችን ለማዋረድ ፕሮፈሰር መረራ ጉዲናን በሚያዋርድ መልክና ከሕግ ውጭ ፍርድ ቤት ከሰሞኑ ያቀረበበት መንገድ ቁጣውን በበቂ መልክ እያቀጣጠልው ነው።

የፖለቲካ እሥረኛው በካቴና ታሥረው (ኢሣት ፎቶ)

ያ ችግር መፍትሄ ሳይገኝ፡ አቶ በቀለ ገርባን ከቀረበባቸው የሽብር ክስ ፍርድ ቤት ነጻ ካደረጋቸው ወዲህ፡ የዋስ መብት መንፈጉ ከላይ ከተነሳው ጋር ያለውን ዝምድና ማየቱ አይከብድም! እርሳቸውም እንዲሁ ከሕግ ውጭ እጃቸውን በሰንሰለት ታሥረው ነው ወደ ፍርድ ቤት የተወሰዱት!

ለማንኛውም በግብር ዙሪያ ለተነሳው ችግር የግብር ይውጣ መልስ እንደመሰጠቱና በተቃውሞ ተባባሪ ሆናችኋል እየተባለ የአማራ ባለሃብቶችን እየሰበሰበ ሕወሃት ማሠሩ፡ የችግሩ ቁልፍ እንደጠፋበት ከማሳየት ባሻገር፣ የችግሩን መባባስ የሚፈልገውና መፍትሄው ከዚያ ይገኛል የሚል ተስፋ ያደረገ አስመስሎታል።

ሕወሃትም መንግሥት ከሆነ፡ ሕዝብን በመናቁ ደብድቤና እንደፈለግሁ ረግጭ ሃገሪቷን ገዛለሁ ብሎ በዶ/ር ደብረጽዮን ፍልስፍና፡ አማራ ከሆነ የሚያስቸግረን እንኳን 30 ሚሊዮን አማራዎችን ሕወሃት አፍሪካንም መደምሰስ ይቻላል ማለታቸው ዛሬም የገዥው ፓርቲ ፍልስፍና ያ ሆኖ ስለሚታይ ሃገራችን አደጋ ላይ መሆኗን ልንገነዘብ ይገባል!


 
ከላይ በፋና ዜና እነደተገለጸው ከሆነ፣ አብዛኞቹ ግለሰቦችና ንበረቶቻቸው የታገዱባቸው ኩባንያዎች በኮንስትራክሽን መስክ ያሉ በመሆናቸው፣ በአብዛኛው በሃገሪቱ ሙስና ውስጥ ሥር ሰደው ያሉት፡ እነማን እንደሆኑ መገመት አያዳግትም።

ከሩቅ የኢትዮጵያን ልብ ትርታ ለማዳመጥ ለሞከረ ሁሉ፡ እንኳን 210 ኩባንያዎች ቀርቶ ሕወሃት የሃገሪቱን መንገዶችንም በሙሉ ጭምር ቢዘጋቸው መፍትሄ አይሆንም!

ከግለሰቦች ውጭ፡ ሃገርን በመመዝበር ረገድና ዕድገቷንም በማዳከም ወንጀል ከፈጸሙት ከዋና ዋናዎቹ በጥቂቱ፡ መቴክ፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክና በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ውስጥ የተፈጸመው ዘረፋ ጋር ከአናት እስከ ቅርንጫፍ ምርመራው መጠየቅ የሚገባቸውን እስካላካተተ ድረስ፡ ሃገረቱ ትርምሷ ይባባሳል፤ ብዙ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ በመሄድ ያልተፈለገ አደጋ ሊከተል ይችላል።

ይህንን ሃገር ያወቀውን ፀሐይ የሞቀውን የወንጀል ተራራ ችላ ብሎ ትናንሾቹን ደላሎች እያሳደዱ የዘርና የብሄረ ስብ ችግሮችን በመቆፈር ፋታ ለማግኘት ሕወሃት ማሰቡ ራሱን በማዕበሉ ለማስወስድ ከሚደረግ ጅላጅልነቱ ተለይቶ አይታይም!/*Updated.
 

ተዛማጅ:

  የልማት ባንክ የተበላሸ ብድር መጠን ከ25 በመቶ በላይ መድረሱ ታወቀ

  የጋምቤላ ሙስና ደረጃ በዛሬው ዜና ሲታይ፣ ለሕግ የሚገዛ አስተዳደር የሌላት ኢትዮጵያ ሃገሪቷን በየደረጃው ‘መረን የለሿ ምዕራብ’ – (Wild West) አድርጓታል!

  ፓርላማው በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አመራሮች ላይ የብቃት ጥያቄ አነሳ

 

%d bloggers like this: