በሪፖርተር ስለታሠሩት ግለስቦች የሚገልጸውን ዜናዊ ሪፖርት በማንበብ የሕወሃትን ምክንያታዊነት ኢትዮጵያውያን ግንዛቤ ውሰዱ!

16 Aug

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በሪፖርተር
 

“መርማሪ ቡድኑ አቶ ሳምሶንን በምን እንደጠረጠራቸው ተጠይቆ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪው ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ሲሆኑ፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተውና ከባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር ያልተጠናቀቁና ችግር ያለባቸውን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደተጠናቀቁና ያላንዳች ችግር ግንባታቸው እንዳለቀ አስመስለው በመገናኛ ብዙኃን አስተላልፈዋል፡፡ አንድ ተቋራጭ የሌለውን የግንባታ ማሽነሪ እንዳለው በማስመሰልና ለመሥሪያ ቤታቸው በመግለጽ ደረጃው ከፍ እንዲልና እንዲያሸንፍ በማድረግ፣ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን አስረድቷል፡፡”

ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ 500,000 ብር ጉቦ በማቀባበል የተጠረጠሩት አቶ ኢዮብ በልሁ፣ በቁጥጥር ሥር ውለው ነሐሴ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ነሐሴ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ገልጾ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተጠርጣሪው፣ የትራንስ ናሽናል ኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ኩባንያ ሠራተኛ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ እንዳስረዳው ተጠርጣሪው ለሚኒስትር ዴኤታው 500,000 ብር ጉቦ ሰጥተዋል፡፡

ተጠርጣሪው ለፍርድ ቤቱ እንደተናገሩት የተያዙበትን ጉዳይ በዕለቱ ከመስማታቸው ውጪ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ ‹‹እኔ ፕሮፌሽናል ነኝ፡፡ ወደ መሥሪያ ቤቱ የገባሁት ጨረታ ወጥቶና አሸንፎ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ነሐሴ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በድንገት ተይዘው ስለታሰሩ ቤተሰቦቻቸው የት እንዳሉ እንደማያውቁና ማንም እንዳልጠየቃቸው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸውም ጠይቀዋል፡፡

ሌላው ለመጀመርያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት ከቤተሰቦቻቸው ጋር በአሜሪካ አገር ዕረፍት አድርገው እንደተመለሱ በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ናቸው፡፡

መርማሪ ቡድኑ አቶ ሳምሶንን በምን እንደጠረጠራቸው ተጠይቆ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪው ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ሲሆኑ፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተውና ከባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር ያልተጠናቀቁና ችግር ያለባቸውን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደተጠናቀቁና ያላንዳች ችግር ግንባታቸው እንዳለቀ አስመስለው በመገናኛ ብዙኃን አስተላልፈዋል፡፡ አንድ ተቋራጭ የሌለውን የግንባታ ማሽነሪ እንዳለው በማስመሰልና ለመሥሪያ ቤታቸው በመግለጽ ደረጃው ከፍ እንዲልና እንዲያሸንፍ በማድረግ፣ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን አስረድቷል፡፡

‹‹ከፍተኛ ጉዳት ማለት ምን ማለት ነው? በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ሆነው ሲሠሩ ማለት ምን ማለት ነው?›› በማለት ፍርድ ቤቱ ላነሳው ጥያቄ መርማሪ ቡድኑ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ አቶ ሳምሶን በተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር መሆናቸውን፣ አድርሰዋል የተባለው ከፍተኛ ጉዳትም የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት እነ አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል በተጠረጠሩበት አምስት የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ተፈጽሟል በተባለው የ1.3 ቢሊዮን ብር ጉዳት ጋር የተገናኘ መሆኑን አስረድቷል፡፡ በአቶ ሳምሶን ላይ አምስት ምስክሮች እንዳሉትና ቃላቸውን እንዳልተቀበላቸው፣ ሀብታቸውን ማጥናት፣ ቢሮአቸው ሲበረበር የተገኙ ሰነዶችን መተንተን፣ በባንክ ያደረጉትን የገንዘብ ልውውጥ የሚያሳዩ የባንክ የሒሳብ መግለጫ ጠይቆ ማየት እንደሚቀረው በማስረዳት፣ ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

አቶ ሳምሶን በጠበቃቸው አማካይነት ባደረጉት ክርክር ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ በቢሮአቸው ብርበራ ተደርጎ ሰነዶች ተወስደዋል፡፡ የተያዙት ሌሎች የተቋሙ ተጠርጣሪዎች በተያዙበት የ1.3 ቢሊዮን ብር ጋር በተገናኘ ነው መባሉንም ተቃውመዋል፡፡ የእሳቸው ተሳትፎ ተገልጾና መጀመርያ መረጃዎችን አጠናክሮ መያዝ ሲገባ፣ አስሮ ማስረጃ መፈለግ ሕገወጥ ድርጊትና ተገቢ ያልሆነ ዕርምጃ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ የባንክ የሒሳብ መግለጫ የሚገኘው ከመንግሥት ወይም ከግል ተቋማት በመሆኑ ከእሳቸው ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለና እሳቸው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆናቸው፣ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር የሚያገናኛቸው የሙያም ሆነ የኃላፊነት አንድነት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ከኃላፊዎቻቸው የሚደርሳቸውን መረጃ በመገናኛ ብዙኃን ማስተላለፍ ከሆነም፣ ሊታሰሩ ስለማይገባ ዋስትና ተፈቅዶላቸው በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠበቃቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን ለሁለተኛ ጊዜ አቅርቦ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት የጠየቀባቸው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ኃላፊ የነበሩት እነ ወ/ሮ ፀዳለ ማሞ ናቸው፡፡

የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ወ/ሮ ፀዳለ ማሞ፣ ምክትላቸው አቶ የማነ ፀጋዬ፣ የጽሕፈት ቤቱ ማስተባበሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሽመልስ ዓለማየሁ፣ የጽሕፈት ቤቱ የመሬት ዝግጅትና መሠረተ ልማት ዲዛይን ረዳት ኃላፊ ወ/ሮ ሳባ መኮንንና የየማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ ባለቤት አቶ የማነ ግርማይ ፍርድ ቤት ቀርበው ተከራክረዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን የሚያስረዱ ሦስት ምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ የአንድ ኦዲተር የሙያ አስተያየት መቀበሉን፣ ከመኖርያ ቤትና ከተለያዩ ቦታዎች የተሰበሰቡ ሰነዶችን ለይቶ መተንተን ላይ መሆኑን፣ የባንክ ማስረጃዎችን እየሰበሰበ መሆኑን፣ አስተዳደሩ ማስረጃ እንዲሰጠው ደብዳቤ መጻፉን፣ የወንጀል ፍሬ ናቸው ያላቸውን ንብረቶች በኤግዚቢትነት መያዙንና 14 ጥራዝ ክፍያ የተፈጸመባቸው ፋይሎች መሰብሰቡን አስረድቷል፡፡ የ12 ምስክሮች ቃል መቀበልና የሁለት ኦዲተሮችን አስተያየት መቀበል እንደሚቀረው፣ ከኤሌክትሮኒክሶች ላይ ያገኘውን መረጃ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ተቋም መጠየቅ፣ ንብረት ማሳገድና ለፎረንሲክ የተላኩ ሰነዶችን ውጤት መጠባበቅ እንደሚቀረው ገልጾ የጠየቀው ጊዜ እንዲፈቀድለት መርማሪ ቡድኑ ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የመርማሪ ቡድኑን ክርክር በመቃወም እንደተናገሩት፣ ድርጊቱ ተፈጸመ የተባለው በ1999 ዓ.ም. ነው፡፡ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ታኅሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ምርመራ ሲደረግበት የከረመ መዝገብ ነው፡፡ መርማሪ ቡድኑ ተጠርጣሪዎችን አስሮ ሌላ ማስረጃ ሊፈልግ አይገባም፡፡ ያለፉት 14 ቀናት ከበቂ በላይ በመሆናቸው የተጠርጣሪዎቹን ቃል ተቀብሎ ማጠናቀቅ ነበረበት፡፡

ወ/ሮ ፀዳለ ተቋሙን ከለቀቁ ስምንት ዓመታት እንዳለፋቸውና በዋስ ቢወጡ እንኳን ምስክሮችን ኃላፊዎችንም ሊያውቁ እንደማይችሉ በጠበቃቸው አማካይነት አስረድተዋል፡፡ ሰነዶች ሁሉ በተቋሙ ስለሆኑ ታስረው የሚቆዩበት ምክንያት እንደሌለና መርማሪ ቡድኑ በ14 ቀናት ውስጥ ሦስት ምስክሮችን ብቻ ተቀብያለሁ ማለቱ በአግባቡ እየሠራ አለመሆኑን እንደሚያሳይም ተናግረዋል፡፡ ከቤተሰብና ከጠበቃ ጋር አለመገናኘት ችግሮች እንደቀጠሉም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች ተመሳሳይ ተቃውሞ በማቅረብ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው አመልክተዋል፡፡

በዋስ ቢወጡ ምስክሮችን እንደሚያባብሉበት፣ ሰነዶችን ሊያስጠፉ እንደሚችሉና ያላከናወናቸው ሥራዎች ብዙ መሆናቸውን መርማሪ ቡድኑ በማስረዳት የተጠየቀውን ዋስትና እንደሚቃወም በመግለጽ፣ የጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በእነ ወ/ሮ ፀዳለ ማሞ ላይ የቀረበውን ምርመራ ሥራ ሲመለከተው ቀሪ ሥራዎች እንዳሉት መገንዘቡን ጠቁሞ፣ ነገር ግን መርማሪ ቡድኑ በአግባቡ ሥራውን እያከናወነ እንዳልሆነ በመረዳቱ መዝገቡን በልዩ ክትትል እንደሚያየው በመግለጽ አሥር ቀናት ተጨማሪ ጊዜ መፍቀዱን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ መብቶች እንዲከበሩ በተደጋጋሚ መግለጹን በማስታወስ፣ መርማሪ ቡድኑ በቀጣይ ቀጠሮ የጠያቂዎችን ዝርዝር ቃል በማካተት ሪፖርት እንዲያቀርብም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ለነሐሴ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ አቶ ሳምሶን ወንድሙ የጠየቁት የዋስትና መብት ታልፎ፣ በእነ አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል መዝገብ ተካተው ነሐሴ 15 ቀን 2009 እንዲቀርቡ፣ አቶ ኢዮብ በልሁም በእነ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ መዝገብ ተካተው ነሐሴ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
 

ተዛማጅ:

ሃገራችንን ሙልጭ አድረገው የጋጧት እየተዝናኑ፡ ሕወሃት የ210 ባለሃብቶችን ንብረት አገድኩ ይለናል መፍትሄ ይመስል!
 

%d bloggers like this: