ለኬንያ የተሸጠ ስኳር ጭነው ወደ ናይሮቢ የተላኩ 110 ተሽከርካሪዎች እስከ ዛሬ ሞያሌ ቆመዋል! ከከሸፈው የኬንያ ምርጫ ጋር የተገናኘ ነገር ይኖረው ይሆን?

1 Sep

የአዘጋጁ አስተያየት:


    የስኳር ዕጥረት ሃገራችን ውስጥ እያለ ለምን ይሆን ሕወሃት 110 የጭነት መኪናዎች 4400 ቶን ስኳር ወደኬንያ ያጎረፈው፣ ለዚያውም ሁኔታውን አጣርቶ መላክ ሲገባው አጉል ሆኖ እንደተጫነ ቀርቶባቸዋል። ሕወሃት የከሸፈው የኬንያ ምርጫ ውስጥ እጅ አለው ማለት ነው፡ ዜጎቻችን አስርቦ፡ ለኡሁሩ ኬንያታ ምርጫ ስኳራችንን ያጎረፈው?

 
==============
Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 24፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ ለኬንያ የተሸጠ ስኳር ጭነው ወደ ናይሮቢ ጉዞ የጀመሩ 110 የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች ከ10 ቀን በላይ ሞያሌ ላይ ቆመዋል።

መንግስት ለኬንያ ስኳር ለመሸጥ በተስማማው መሰረት ነው ከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎቹ ስኳሩን ጭነው ወደ ናይሮቢ ጉዞ በማድረግ ላይ የነበሩት።

አሽከርካሪዎች ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባቀረቡት ቅሬታ፥ “ከነሃሴ 3 ጀምሮ ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ ስኳር በመጫን ወደ ኖይሮቢ ጉዞ ብንጀምርም ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ሞያሌ ላይ ለመቆመ ተገዳናል” ብለዋል።

አሽከርካሪዎቹ፥ ያለ ምኝንም ምክንያት 10 ቀን በወንጂ ስኳር ፋበሪካ፤ 10 ቀን ደግሞ በኬኒያ ድንበር አቅራቢያ እንድንቆም ተደርገናል ይላሉ።

የብራይት ድንበር ተሻጋሪ ደረጃ አንድ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማህበር ተጠባባቂ ስራ እስኪያጅ አቶ ደረሰልኝ አበጀ፥ ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ ጀምሮ የአሽከርካሪዎች ፓስፖርት እና መሰል ጉዳዮችን ለማሟላት የተወሰኑ ጊዜ ወስዶብናል ይላሉ።

የማጓጓዝ ስምምነቱን ስኳሩን ከገዛው የኬንያ ድርጅት ጋር ካደረግን በኋላ ስኳሩ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጊዜ ወስዷል ብለዋል።

ለተጨማሪ ቀናት ተሽከርካሪዎቹ በሞያሌ እንዲቆዩ የተደረጉበት ምክንያት ግን በኬኒያ በኩል ያልተፈታ ጉዳይ በመኖሩ ነው ሲሉም ተጠባባቂ ስራ እስኪያጅ ተናግረዋል።

ተጠባባቂ ስራ አስኪያጁ፥ “በማህበሩ ስህተት የተፈጠረውን ችግር በኛ በኩል ይሸፈናል፤ በኬኒያ በኩል ያለውን ደግሞ የኬንያ ድርጅት እንዲሸፍን መግባባት ላይ ደርሰናል” ብለዋል።

የስኳር ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አይችሉም፥ የኬንያ መንግስት ጥያቄን መሰረት በማድረግ ኢትዮጵያ ለኬንያ 100 ሽህ ኩንታል ስኳር ለመላክ ግንቦት ላይ ስመምነት ላይ መድረሷን ይናገራሉ።

ስኳሩን ለማጓጓዝም ከብራይት ድንበር ተሻጋሪ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማህበር ጋር ስመምነት ላይ የደረሱት ስኳሩን የገዛዉ የኬንያው ድርጅት ነው ያሉት አቶ ጋሻው፤ በኬንያ አንድ ተሽከርካሪ መጫን የነበረበት 280 ኩንታል እያለ ተሽከርካሪዎቹ ግን የጫኑት 400 ኩንታል ነዉ፤ ይህን ችግር መፍታትም ጊዜ መውሰዱን አስታውቀዋል።

ችግሩን ለመፍታት ከኬንያ መንግስት ጋር የትራንስፖርት ባለስልጣንን ጨምሮ የስኳር ኮርፖሬሽን ምክክር ሲያደርግ መቆየቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ከነገ ጀምሮ 4 ሽህ 400 ቶን ስኳርን የጫኑ 110 ተሽከርካሪዎች ወደ ናይሮቢ እንዲያቀኑ መግባባት ላይ መደረሱንም ሃላፊው አስታውቀዋል።

አቶ ጋሻው አያይዘውም፥ ግንቦት ላይ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ ለኬንያ መንግስት ማቅረበ የነበረባት 100 ሺህ ኩንታል ስኳር ነበር ይላሉ።

የተላክው ግን 44 ሽህ ኩንታሉ ብቻ ነው፤ የብራይት የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማህበር በገባው ውል መሰረት በአፋጣኘ ትራንስፖርት ባለማቅረቡ ማግኘት የነበረብንን የውጭ ምንዛሬ በጊዜ እንዳናገኝ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ፋብሪካዎች ለእደሳት ስራ ማቆማቸዉን የተናገሩት አቶ ጋሻዉ፣ በእድሳት ወቅት ለመለዋወጫ እና ለጥገና የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህ እጥረት ለመሙላትም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ታሳቢ በማድረግ ስኳር ኮርፖሬሽን ጥሩ ዋጋ በሚገኝበት ወቅት ወደ ውጭ በመላክ እጥረት በሚፈለግበት ወቅት ደግሞ ከአማራጭ ገበያዎች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት እቅድ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
 

%d bloggers like this: