የህወሓት አባላት ህወሓትና የትግራይ ወጣቶች፡ ሆድና ጀርባ?

11 Oct

ሕወሃት፡ አልሞትኩም ብዬ ዋሻለሁ! ከህወሓት 12ኛ ጉባኤ ላይ የተወሰደ ፎቶ (Girmay Gebru)

 
Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
by BBC አማርኛ
 
ከሰባት ቀናት በኋላ ሰኞ አመሻሹ ላይ መግለጫ የሰጠው ማዕከላዊ ኮሚቴው፤ በጥልቀት መታደሱን፣ የህዝብ ጥያቄ እየመለሰ መሆኑንና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር የነበረውን ግንኙነት ማሻሻሉን በድል አድራጊነት ይገልፃል።

የፓርቲው ልሳን በሆነው ወይን መፅሔት፤ ሐምሌ-ነሐሴ በወጣው እትም ላይ “ከአሁን በኋላ ፓርቲያችንን ከአደጋ ለመታደግ ሰፊ ጊዜና ዕድል የለንም” በማለት ፓርቲው አብዮታዊ መገለጫዎቹን ሊያጣ እንደሚችልና የትግራይ ህዝብ በተለይም ደግሞ ወጣቱ ተስፋ ሊቆርጥበት እንደሚችል ስጋቱን ገልፆ ነበር።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳ በፈቃዳቸው ስልጣን እለቃለሁ ማለታቸውን ጨምሮ፤ በክልሎች መካከል የሚፈጠር ግጭት እየተባባሰ በሄደበት በአሁኑ ወቅት፤ የገዢው ፓርቲ መስራች ድርጅት የሚያካሂደው ስብሰባ የትግራይ ወጣቶችን ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊ ትኩረትን ይስብ ነበር፤ ይላሉ የሃገሪቱ ፖለቲካ ታዛቢዎች።

ለየቅል

ታድያ የፓርቲው ስብሰባ የትግራይ ህዝብን በተለይ ደግሞ የወጣቶችን ትኩረት ያጣበት ምክንያት ምን ይሆን? ፓርቲውን የሚያሰጋው ተስፋ መቁረጥ ላለመፈጠሩስ ምን ዋስትና ይኖራል?

ቢቢሲ በፌስቡክ ገፁ ላይ ወጣቶችን “ከስብሰባው ምን ትጠብቃላችሁ?” በማለት ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ከመቶ በላይ ሰዎች አስተያየታቸውን ያስቀመጡ ሲሆን፤ 95 በመቶዎቹ የሚጠብቁት አዲስ ነገር እንደሌለ ሲገልፁ ጥያቄውን ማቅረባችንን ራሱ የተቹም ነበሩ። በርግጥ ጥቂቶቹም ፓርቲው ስብሰባውን በድል እንደሚያጠቃልል ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም ትምህርት ተቋም መምህር ናሁሰናይ በላይ “የፓርቲው ስብሰባ ሚስጢራዊነት የበዛበትና ዝግ ቢሆንም፤ ቀድም ሲል አንዳንድ መረጃዎች ይወጡና አነጋጋሪ ይሆኑ ነበር” ይላል።

“ዛሬ ግን ያገኘነው መረጃ የለም” ይላል።

ተስፋኪሮስ አረፈ በፌስቡክ ከሚፅፉና ከሚቀሰቅሱ ታዋቂ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። “የማሌሊት አስተሳሰብ እስካልጠፋ ድርጅቱ አይታደስም” በሚል በተደጋጋሚ አቋሙን ያንፀባርቃል። “ይህም አዲስ ነገር የለውም፤ የወጣቱና የፓርቲው አጀንዳዎች ተለያይተዋል” ሲል ሃሳቡን ይገልፃል።

“ከአሁን በኋላ ማን መጣ፤ ማንስ ሄደ የሚለው አያስጨንቀኝም። ጭራሽ መርሳት ነው ያለብን” ይላል ለውጥ እንደማይመጣ ተስፋ በመቁረጥ።

“ነገሩ የወንበራቸው ጉዳይ ይመስለኛል። የውስጣቸው አጀንዳ እንጂ የህዝብ ጉዳይ እያስጨነቃቸው አይመስልም።”

“ምን ሊያጣላቸው እንደሚችል ቀደም ብለው ነግረውናል። ጉዳያቸው የግል ጥቅምና የስልጣን ቆይታቸው ነው” የሚለው ደሞ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር መሓሪ ዮሃንስ ነው።

ፓርቲውን በመተቸት የሚታወቀው መሓሪ “ድርጅቱ ምን አጀንዳ ላይ ይወያይ እንደነበር አላወቅኩም” ይላል። ለማወቅም ብዙ ጉጉት እንደሌለውም ይናገራል።

“ለትግራይ ህዝብ የሚበጅ ነገር እንደማይገኝበት አውቃለሁ። በክልሉም ሆነ በሃገሪቱ ስላለው መሠረታዊ ችግር መረዳት አልቻሉም። መሠረታዊ መፍትሔ ማምጣትም አይችሉም” ይላል መሓሪ።

እሱ እንደሚለው ወጣቶች የሚያቀርቡት ጥያቄ በህወሓት ዘንድ ቀልድ ነው። አልያም የጤና አይደለም። በተለይ ስለ ፍትሕና አስተዳደር፣ ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ሁኔታ፣ የልማት እጦት፣ ስለ ዴሞክራሲ ጥያቄ የሚያነሳ እንደጠላት ነው የሚቆጠረው።

አሉላ ሰለሞን በዋሺንግተን የሚኖር የኮሚዩኒቲ መሪ ነው። በማህበራዊ ገፆች በንቃት የሚሳተፍ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ፓርቲውን ደግፎ በሚያቀርባቸው ፅሑፎቹ ይታወቃል። አሉላ የወጣቱን ተስፋ መቁረጥ ውድቅ አላደረገም። “በአጠቃላይ በስብሰባው ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ የመረጃ እጥረት አለ” ይላል።

“ከዚህ ጋር በተያያዘ መታየት ያለበት ግን በፌደራል ደረጃ ያለውን ሁኔታ ለመለወጥ የኢህአዴግ በተለይም ደግሞ የህወሓት አቅም ውስንነት አለ” ሲልም ሃሳቡን ይሰጣል።

የፓርቲው ልሳን “አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ መገለጫዎቻችን እየተሸረሸሩ፤ የግል ጥቅሞቻችንን ለማሟላት ስንሯሯጥ ነው ፓርቲያችን ስጋት ላይ የሚወድቀውና በጥርጣሬ የተሞላው” ይልና፤ ቀጥሎም በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች “ከጥፋት ሃይሎች” ጋር በመተባበር እየሰሩ እንደሆነ ይገልፃል።

“ውጤቱም የርዕዮተ-ዓለም ጉዳይ አይደለም፤ በተግባር እየተጀመረ ያለ የጥፋት መንገድ ነው” በማለት ያስቀምጣል።

ከህወሓት 12ኛ ጉባኤ ላይ የተወሰደ ፎቶ (BBC Amharic)

“ስራውን ጨርሷል”

አሉላ ስብሰባው የወጣቱን ትኩረት ያልሳበበት ምክንያት የመረጃ እጥረት በመኖሩ ነው ይበል እንጂ፤ ናሑሰናይ ግን ዋናው ምክንያት ሌላ እንደሆነ ይሞግታል።

ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው 12ኛው ጉባኤ ላይ “ከውስጥም ከውጭም የተፈጠረው ተፅዕኖ የት ገባ?” በማለት ናሁሰናይ ይጠይቃል። ሂደቱን አድንቆ በውጤቱ ግን የወጣቱን ተስፋ ለመጨረሻ ጊዜ ያስቆረጠ አጋጣሚ እንደነበር ይናገራል።

“በመጨረሻም እንደወትሮው ነው የሆነው። ትልቅ ያመለጠ ዕድል አድርጌ እቆጥረዋለሁ” ይላል።

አረና (መድረክ) እና ኋላ ላይ ድርጅቱን የተቀላቀለው አብርሃ ደስታ እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ በትኩረት ድርጅቱን ሲተቹ የነበሩ ወጣቶች ለዚህ መነቃቀትና ተስፋ አድርሰውት ነበር።

“በቃ ድርጅቱ አልቻለም፤ ሌላው ቀርቶ የቁርጥ ቀን ደጋፊ የሚባለው እንኳን ፀጥ ብሏል” በማለት ድርጅቱ ማህበራዊ መሠረቱን እያጣ ስለመሆኑ አመላካች ነው ይላል ናሁሰናይ።

የኢህአዴግ ዋና መስራችና በሃሳብ አመንጪነት የሚታወቀው ህወሓት፤ ምናልባት የሊቀመንበሩ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የመለስ ዜናዊ ድንገተኛ ህልፈት ከፈጠረበት መደናገር የወጣ አይመስልም።

ህወሓት አገራዊ ሚናውንም በዚያው ልክ እየተወጣ አይደለም የሚለው ናሁሰናይ፤ የመሪነት ቁመናውን በሌሎች ምናልባትም በኦህዴድ ሊወሰድ እንደሚችል ይገምታል።

መገማገምና መነቃቀፍ የድርጅቱ ባህሪ ነበር። አሁን አሁን ግን የፍትህ እጦት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር እየበዛ በመጣ ቁጥር የድርጅቱ ህዝባዊነት እየተሸረሸረ፤ የታገለለትን ዓላማ እየዘነጋ መምጣቱ ይነገራል።
በእርግጥ ድርጅቱም “በውስጣችን ያለው የዛገ ነገር መቀየር አለበት” በማለት በልሳኑ ላይ አምኗል።

“ትግራይ ውስጥ ያለው የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት ከሌላ አካባቢ የባሰ እንጂ የተሻለ አይደለም” የሚለው መሓሪ፥ ነጻ ሚድያና ተቃዋሚዎች፥ ህዝቡንና ድርጅቱን የአለመለየት ችግር እንዳለባቸው ይናገራል።

አሉላ እንደሚለው፤ ህወሓት እንደ ሌሎች እህት ድርጅቶች የመተካካትና አዲስ አመራር የመፍጠር ሥራ አልሰራም የሚል ስሜት ወጣቱ እንዳለው ይቀበላል።
 

%d bloggers like this: