በረከት ስምኦን የንግድ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢነትን እንዲያስረክብ ታዘዘ!

15 Oct

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በሪፖርተር
 

አቶ በረከት ስምኦንንም ሆነ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ላይ ለማነጋገር ጥረት ቢደረግም አልተሳካም። የተቆጣጣሪ ኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል ለቀረበላቸው የስልክ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

ላለፉት ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን፣ ለብሔራዊ የፕላን ኮሚሽነሩ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ሊያስረክቡ ነው።

በመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል (ዶ/ር) ሐሙስ ጥቅምት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ፣ የአቶ በረከት የቦርድ ሰብሳቢነት እንዲያበቃ ተደርጓል፡፡ ኃላፊነታቸውን የሚያስረክቡበት ምክንያት ግን አልተገለጸም።

አቶ በረከት የቦርድ ሰብሳቢነታቸውን ጠቅልለው የሚያስረክቡት ጥቅምት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ስምንት አባላት ሲኖሩት ከዚህ ቀደም አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ወልዳይ አመሐ (ዶ/ር) እና አቶ ጌታቸው ነገራ በተለያዩ ጊዜያት ተሰናብተዋል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የግዢ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ነገራ፣ በቅርቡ በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።

አቶ በረከት ከሰባት ዓመታት በፊት የንግድ ባንክን ቦርድ ሰብሳቢነት የተረከቡት ከአቶ ዓባይ ፀሐዬ እንደነበር ይታወሳል።

ነባሩ የኢሕአዴግ አመራር አቶ በረከት ስምኦን በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም የማስታወቂያ ሚኒስትር፣ የመጀመሪያው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ሆነው መሥራታቸው አይዘነጋም።

የብሔራዊ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ከጥቅምት 21 ቀን 2010 ጀምሮ ሙሉ በሙሉ የቦርድ ሰብሳቢነቱን እንደሚረከቡ ይጠበቃል። ከዚህ ቀደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩ ሲሆን፣ ሒልተን ሆቴልን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ሆቴሎች አስተዳደር አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቦርድ አባልም ናቸው።

አቶ በረከት ስምኦንንም ሆነ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ላይ ለማነጋገር ጥረት ቢደረግም አልተሳካም። የተቆጣጣሪ ኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል ለቀረበላቸው የስልክ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
 

ተዛማጅ:

    Already approved CBE loan to Al Amoudi disapproved; why are culprits not taken to task?

    CBE Board under Bereket’s chairmanship approves ETB one billion to Al Amoudi

    World Bank denies blame for violent Ethiopian evictions

    New evidences & old denials clash over human rights violations in Gambella, as fortified evidences emerge; but does the Meles regime have either the innocence or credibility to fight this off?

 

%d bloggers like this: