በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ወረርሽኝ ሊባል በሚችል ደረጃ እየተስፋፋ መምጣቱ ተገለፀ

18 Oct

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ወረርሽኝ ሊባል በሚችል ደረጃ እየተስፋፋ መምጣቱ ተገለፀ።

በዓመት ከ27 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ይይዛሉ የተባለ ሲሆን፥ ከ19 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ አማካኝነት ይሞታሉ ነው የተባለው።

በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ውይይት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና በፌዴራል የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት አዘጋጅነት በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የቫይረሱ የስርጭት ምጣኔው ከ2 ነጥብ 5 እስከ 25 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።

እንዲሁም አጠቃላይ ሀገር አቀፍ የስርጭት መጠኑ ደግሞ 1 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱ ተብራርቷል።

አሃዙ የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ወረርሽኝ ሊባል የሚችል ደረጃ መሆኑን ነው በኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብረሃም ገብረመድህን የተናገሩት።

በትልልቅ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክቶች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የአበባ ልማትና መሰል ሰፋፊ የልማት አካባቢዎች የኤች አይ ቪ አጋላጭ ባህሪያት መስፋት ለቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ ስጋት ሆኗልም ብለዋል።

ይህ ደግሞ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ጉዳት እንደሚያደርስም አብራርተዋል።

እንደማሳያነትም ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት ላይ የተሰራን የጥናት ውጤት ያቀረቡ ሲሆን፥ ጥናቱም ኤች አይ ቪ/ኤድስ ከሳሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራትን የኢኮኖሚ እድገት ከ2 — 4 በመቶ እንዲቀንስ እያደረገ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

ይህ ሊሆን የቻለውም በአሁኑ ጊዜ ቫይረሱ በብዛት እያጠቃ ያለው አምራች ሀይል የሚባለውን ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል ነው፤ ይህንን ለመግታትም በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ በበኩላቸው፥ ከአምሰት ዓመት ወዲህ ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከል የተሰራው ስራ መቀዛቀዝ እንደታየበት አንስተዋል።

ከዚያ በፊት በተሰሩ ስራዎች በቫይረሱ አማካኝነት የሚከሰት ሞትን 70 በመቶ እንዲሁም አዳዲስ የሚያዙ ሰዎችን በ90 በመቶ መቀነስ ተችሎ እንደነበረ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውሰዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት የተመዘገበው ለውጥ መዘናጋት መፍጠሩንም ነው ዶክተር ከበደ ያነሱት።

ከ5 ዓመት በፊት የነበረውን ኤች አይ ቪን የመግታት ስራ ለመድገም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
 

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመንገድና ስኳር ፕሮጀክቶች ኤች አይ ቪ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ነው ተባለ!
 

%d bloggers like this: