ቡኖ በደሌ: ”ከቤታችን ሸሽተን ስንወጣ ጉረቤቶቻችን ያለቅሱ ነበር”

25 Oct

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
by BBCአማርኛ
 
ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ በኦሮሚያ ክልል በቡኖ በደሌ ዞን በተከሰተው ግጭት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሶ የአማራ እና የትግራይ ተወላጆች ቤት ንብረታቸውን ጥለው በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ መዘገባችን ይታወሳል።

”ቤትና ንብረታችን ወድሟል፤ የምንበላውም ሆነ የምንለብሰው የለንም”

በቡኖ በደሌ የተከሰተው ምንድን ነው?

ካለፈው ሃሙስ ጀምሮ የአካባቢው ወጣቶች ተፈናቃዮቹ ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር ሆነው ንብረታቸውን እያወደሙ ውጡልን ስላሏቸው ለህይወታቸው ሰግተው ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንደወጡ ከተፈናቃዮች ሰምተናል።

ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ስለጥቃት ፈፃሚዎቹና ቀደም ሲል ከአካባቢው ተወላጆች ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት ነግረውናል።

አቶ አቢ አዝመራው በ1977 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው ድርቅ ምክንያት ከወሎ ወደ ዴጋ ወረዳ የደርግ መንግሥት እንዳሰፈራቸው ይናገራሉ።

”በዚያ አስቸጋሪ ጊዜ የአካባቢው ነዋሪ እጁን ዘርግቶ ነበር የተቀበለን። አሁን ዘጠኝ የቤተሰብ አባላት አሉኝ፤ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በከተማም ሆነ በገጠር በርካታ ንብረት አፍርቻለው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካለፉት ጥቂት ዓመታት ድረስም ከአካባቢው ተወላጆች ጋር እጅግ መልካም የሚባል ግንኙነት ነበረን” ይላሉ።

”ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ግን አፍላው ወጣት በማናውቀው ምክንያት እኛን ጠላት አድርጎናል” በማለት የሚናገሩት አቶ አቢ ”አሁንም ድረስ ግን የሀገር ሽማግሌዎች እየሸመገሉን ነው” ሲሉ ያሰረዳሉ።

”በእድሜ ገፋ ያሉትን መውቀስ አንፈልግም። ባለፈው ሳምንት ከቤታችን ሸሽተን ስንወጣ ጉረቤቶቻችን ያለቀሱ ነበር። ግን ምን ያደርጋል ልጆቻቸውን ማስቆም አልቻሉም፣ ሲያጠፉም ለህግ አሳልፈው መስጠት አይችሉም። እኔ የማውቃቸው የሀገር ሸማግሌዎች ከኦሮሞ ተጋብታችሁ ኑሩ፣ ቤት ሰርታችሁ ኑሩ እያሉ ነው የሚሸመግሉን ዛሬም እዚህ ተጠልለን ባለንበት ቦታ እየመገቡን ያሉት ኦሮሞዎቹ ናቸው” ሲሉ ይናገራሉ።

ሌላው በስልክ ያነጋገርነው ወጣት ሙሉ ከላይ ይባላል። 28 ዓመቱ ሲሆን ቤተሰቦቹ ከትግራይ ክልል ዓዲ ጉደም ከሚባል ቦታ መጥተው እሱን እዚህ እንደወለዱት ያገልጻል።

በመንግስት መሰሪያ ቤት ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች (ቢ.ቢ.ሲ. ፎቶ)

”እዚሁ ኦሮሚያ ክልል ነው ተወልጄ ትዳር መስርቼ ሁለት ልጆችን የወለድኩት። ቤተሰቦቼ በ1996 ዓ.ም ወደ ትግራይ ሲመለሱ እኔ ግን ሀገሬ እዚህ ነው ብዬ ቀረሁ” ይላል።

የልጅነት ጊዜውን ከኦሮሞ ልጆች ጋር እንዳሳለፈና አሁንም ድረስ ከጓደኞቹ ጋር መልካም ግንኙነት እንዳለው የሚናገረው ሙሉ፤ ”ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የመቃቃርና የመጠራጠር ስሜት እየተፈጠረ መጣ ”ይላል።

”ከኛ ጋር በፍቅር መኖር የሚፈልጉ አሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አካባቢውን ጥለን እንደንወጣ የሚጠይቁ ወጣቶችም አሉ። እኛን ሊረዱ የሚፈልጉት በእነዚህ በወጣቶች ይጠቃሉ” ሲል ይናገራል።

ተፈናቃዮችን በስልክ ባገኘንበት ወቅት የአካባቢው ተወላጅ የሆነው አንድ ወጣት አብሯቸው እንዳለ ገልጸውልን እኛም አነጋግረነዋል።

ልክ እንደእርሱ ሁሉ በአካባቢው በርካታ የኦሮሞ ወጣቶች ከሌሎች ብሄር ተወላጆች ጋር ትዳር መስርተው እንደተዋለዱ ነግሮናል።

”ከእነሱ ጋር ተዋልደን መክበዳችንን ያላስተዋሉ አንዳንድ ወጣቶች አካባቢውን ለቃችሁ ይሂዱ ይላሉ። ምንም እንኳን በእነርሱ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ስከላከል ዛቻ እና ማስፈራሪያ ቢደርሰኝም አሁንም ወደዚህ የመጣሁት የአቅሜን ያክል የሚበላ ነገር ይዤላቸው ነው” ብሎናል።

በአሁኑ ጊዜ የአካባቢው ነዋሪዎችና አስተዳደር የቻሉትን ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን የተፈናቀሉት ሰዎች ነግረውናል።
 

ተዛማጅ፡

 

%d bloggers like this: