ለዘንድሮ የታቀደው የ196 ቢሊዮን ብር ገቢ መሳካቱ ‘በመንግሥታዊ’ በጀት አፈጻጸም ዙርያ ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሯል!

26 Oct

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በሪፖርተር
 
የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ለሁለት ቀናት የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤት ኃላፊዎችን ጠርቶ ባነጋገረበት ወቅት፣ በዚህ ዓመት ለየትኛውም መሥሪያ ቤት ምንም ዓይነት ተጨማሪ በጀት እንደማይመደብለት ይፋ አደረገ፡፡

ጥቅምት 13 እና 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ሚኒስትሮችን፣ ዋና ዳይሬክተሮችን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶችንና ሌሎች ኃላፊዎችን መሥሪያ ቤታቸው ጠርተው ያነጋገሩት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ ለ2010 በጀት ዓመት የተመደበው የፌደራል መንግሥት በጀት 321 ቢሊዮን ብር መሆኑን በማስታወስ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶቹ በቁጠባ እንዲጠቀሙና እንዲያሸጋሽጉ በመጠየቅ ተጨማሪ በጀት እንደማይመደብላቸው አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስትሩ መንግሥት በዚህ ዓመት ለመደበው የ321 ቢሊዮን ብር ወጪ ከሚሸፈንባቸው ዋና ዋና የገቢ ምንጮች አንዱ የታክስ ገቢ እንደሆነና ለዓመቱ የታቀደው የገቢ መጠንም 196 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ጠቁመው፣ ይህንን ገቢ መሰብሰብ ከባድ ፈተና እንደሚሆን ሲያብራሩም የጠቀሱት በአገሪቱ ያለው ተጨባጭ ሁኔታን ነው፡፡ ባለፈው ዓመት የታቀደው የታክስ ገቢ 170 ቢሊዮን ብር ቢሆንም፣ መሰብሰብ የተቻለው ግን 130 ቢሊዮን ብር በመሆኑ የ40 ቢሊዮን ብር የገቢ ጉድለት ማጋጠሙን አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና በወጪና በገቢ መካከል የታየውን ክፍተት በትብብር ወጪዎችን በማሸጋሸግ ሲያስፈልግም ወደዚህኛው ዓመት በማዛወር ዓመቱ ማለፉን ዶ/ር አብርሃም አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም ባለፈው ዓመት ተመድቦ ከነበረው የ81 ቢሊዮን ብር መደበኛ ወጪ (ለሠራተኛ ደመወዝና ለተለያዩ ሥራ ማስኬጃዎች የሚመደብ)፣ ለዘንድሮ የተመደበው የመደበኛ ወጪዎች በጀት በአንድ ቢሊዮን ብር ብቻ ጨምሮ 82 ቢሊዮን ብር ብቻ እንዲሆን የተደረገው፣ የመበደኛ ወጪዎችን በቁጠባ በመጠቀም ባሉበት እንዲቀጥሉ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ ከፌዴራል መ/ቤቶች ኃላፊዎች ጋር ስለበጀቱ መሳካት ለመምከር ተሰብስበው (ፎቶ ሪፖርተር)

በዚህም ሳቢያ በሐምሌ 2009 ዓ.ም. ለሁሉም ሚኒስቴሮችና የፌዴራል ባለበጀት ተቋማት የተላለፈው የወጪ ቅነሳ መመርያ በመበደኛ ወጪዎች ቅነሳ ላይ ያጠነጠኑ 19 ወጪ ሊወጣባቸው አይገባም ወይም ወጪያቸው መቀነስ አለበት ያላቸውን ነጥቦች በዝርዝር ሚኒስቴሩ አስቀምጧል፡፡ የመደበኛ ወጪ ቅነሳ ተደርጎባቸዋል የተባሉት ነገር ግን በርካታ ተቋማት ቅሬታና ተቃውሟቸውን ያቀረቡባቸው ከመመርያው የወጪ ቅነሳ ገደቦች ውስጥ በተለይ የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ የተሽከርካሪ ጥገና ወጪ፣ የተሽከርካሪ ኪራይ፣ የስልክ ወጪና የመስተንግዶ ወጪዎች ካነጋገሩና ቅሬታ ከቀረበባቸው መካከል ሚዛን የሚደፉ ናቸው፡፡

‹‹በየመሥሪያ ቤቱ ለሚደረጉ ስብሰባዎች፣ ዓውደ ጥናቶችና ሴሚናሮች እንደ ሻይ፣ ቡናና ውኃ ከመሳሰሉት ወጪዎች በስተቀር ሌላ ግብዣ ማድረግ አይቻልም፤›› በማለት የግብዣ ወጪዎችን የሚከለክለው የመመርያው ክፍል፣ ‹‹ቦርሳ፣ ቲሸርት፣ ካኔቴራ፣ ኮፍያ፣ ሻርፕና የተለያዩ የአገር ባህል አልባሳትን መግዛት አይቻልም፡፡ በተቻለ መጠን ስብሰባዎች በየተቋማቱ መሰብሰቢያ አዳራሾች በማካሄድ ለሆቴሎች የሚወጣውን ወጪ ማስቀረት ይቻላል፤›› በማለት ምክር አዘል ክልከላ አስቀምጧል፡፡

እንዲህ ያሉ የወጪ ክልከላዎችን በበጎ እንደሚቀበሉ የገለጹ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ሰሞኑን 25ኛ የምሥረታ በዓሉን ያከበረው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅንቄ (ደኢሕዴን) በስብሰባ ወቅት ያሳየውን በመኮነን አስተያየታቸውን ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡ የመንግሥት ወጪን ለመቆጠብ ሲባል ካኔቴራና ኮፍያ መግዛት ይቅር እየተባለ ባለበት ወቅት፣ የፓርቲው አባላት በኮፍያና በቲሸርት ያደመቁት ስብሰባ ከአባላቱ መዋጮ የተገዛም ቢሆን የአገር ሀብት አይደለም ወይ? አንዱ ኃላፊነቱን እየተወጣ ሌላው እንዳሻው የሚሆነው ለምንድን ነው? በማለት ጠይቀዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲዎች የቀረበው የወጪ ቅነሳ መመርያ በተለይ በተማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ እያስነሳና ለብጥብጥም ጭምር መንስዔ እየሆነ መጥቷል በማለት ከጠቀሱት ውስጥ፣ በቀን ለምግብ የሚከፈለው የ15 ብር መጠን ያለው የምግብ አቅርቦት በማለት የወጪ ቅነሳ መመርያው የአበልና የትርፍ ሰዓት ክፍያዎችን እንዲያሻሽል የጠየቁ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ነበሩ፡፡

በዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች ሚኒስቴሮች መነጋገሪያ ሆነው የተገኙት ከመመርያው ክፍሎች ውስጥ የተሽከርካሪ ጥገናና የኪራይ፣ እንዲሁም የስልክ ወጪን የተመለከቱት ሰፊ ጊዜ ወስደዋል፡፡ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መሠረት የተሽከርካሪዎች ጥገና መካሄድ ያለበት እንደ ማንኛውም የግዥ አገልግሎት በጨረታ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ከትልልቅ የተሽከርካሪ አስመጪ ኩባንያዎች ጋር በቀጥታ ስምምነት በማድረግ የሚወጣውን ወጪ መቀነስ ይቻላል፡፡ ሚኒስትር አብርሃም እንደጠቀሱት ከሆነ በአሁኑ ወቅት እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ ለአንድ መኪና የጥገና ወጪ እየተጠየቀ ነው፡፡ የተሽከርካሪ ኪራይን በተመለከተም በበጀት መሥሪያ ቤቶች በማዕከል ግዥ ተከናውኖ ተሽከርካሪ የሚመደብ በመሆኑ፣ ለተሽከርካሪ ኪራይ በጀት ካልተፈቀደ በቀር ወጪ መደረግ የለበትም ተብሏል፡፡ ሆኖም ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች በመስክ ሥራ ላይ የሚያተኩሩ መሥሪያ ቤቶች የጥገናም ሆነ የኪራይ ወጪ መከልከሉን ተቃውመዋል፡፡ እንደ ጋምቤላ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች የባለሙያዎች ዕጥረት ከፍተኛ በሆነበት አካባቢ በጋራዦች ተሽከርካሪዎችን ማስጠገን ከጥቅሙ ጉዳቱ ይብሳል በማለት ተቃውመውታል፡፡ ለትራፊክ ደኅንነት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል በማለት ጥገና በአስመጪ ኩባንያዎች መካሄድ አለበት ሲሉ የተደመጡም አሉ፡፡

ሁሉም የመሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ለመካከለኛና ከዚያም በታች ላሉ ኃላፊዎች የሞባይል ካርድ ግዥ ወጪ ማድረግ አይቻልም መባሉ ሥራ እንዳስተጓጎለባቸው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች 24 ሰዓት የሚሠሩ ተቋማት በመሆናቸው አብዛኛውን ጊዜ ከሥራ ሰዓትና ከቢሮ ውጪ ባሉት ጊዜያት የሥራ ክትትል ለማድረግ የሚረዳቸው የሞባይል ስልክና የኢንተርኔት ግንኙነት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሌሎችም መሥሪያ ቤቶች የተደረገው ክልከላ ተገቢ አይደለም በማለት ተከራክረዋል፡፡ ሚኒስትሩና የሥራ ተጠሪዎቻቸው ግን በሞባይል ካርድ ግዥ ብቻም ሳይሆን በመደበኛ ስልክ አጠቃቀም ላይ በየመሥሪያ ቤቱ ተመን ሊወጣ እንደሚገባና ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች በበኩላቸው ከሚታዩባቸው ከፍተኛ የፋይናንስ አስተዳደር ችግሮች መካከል በኦዲተሮች፣ በሒሳብና በፋይናንስ ባለሙያዎች እጥረትና ፍልሰት እየተቸገሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ የወጪ ቅነሳው ላይ ከቀረቡ በርካታ ቅሬታዎች መካከል የአክሲዮን ግዥ የፈጸሙ ዩኒቨርሲቲዎችም ጥያቄ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል፡፡ ‹‹ምን እናድርግ?›› በማለት ላቀረቡት ጥያቄም፣ ‹‹ባለበጀት መሥሪያ ቤት ትርፍ በሚያስገኝና በአክሲዮን ግዥ ሒደት መሳተፉ ከየትኛውም ጉዳይ ወጣ ያለ ነው፡፡ በቶሎ አስተካክሉ፡፡ ሳይረፍድ በቶሎ አስተካክሉ፤›› በማለት ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል፡፡

ቅጥ ያጡ ወጪዎች ይታይባቸዋል ከተባሉት ውስጥ የቢሮ ኪራይ ይገኝበታል፡፡ በአዲሱ መመርያ መሠረት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች አዲስ ቢሮ መከራየት አይችሉም፡፡ ተከራይተው ከፍተኛ ወጪ እየከፈሉ ያሉትም ወጪያቸውን የሚቀንሱበትን መንገድ እንዲፈትሹ ተጠይቀዋል፡፡ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የበጀት ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ መኮንን እንዳብራሩት፣ ለአንድ ተቋም የሚወጣው የቢሮ ኪራይ ወጪ 650 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የቢሮ ግንባታ የሚያከናወኑ መሥሪያ ቤቶችም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተጠየቁ መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በሚኒስትር አብርሃም፣ በሚኒስትር ዴኤታው አቶ አድማሱ ነበበ የተመራው የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችን የፋይናንስ አስተዳደር የተመለከተው የውይይት መድረክ ከወጪ ቅነሳ ባሻገር፣ ውዝፍ ተሰብሳቢና ተካፋይ ሒሳቦች በቶሎ እንዲጠናቀቁ ተጠይቋል፡፡ እንደ አቶ ተፈሪ ገለጻ፣ ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን ብር ውዝፍ ሒሳብ የሚታይባቸው ትልልቅ መሥሪያ ቤቶች አሉ፡፡

እንደ ስፖንሰርሺፕ፣ ሽልማት፣ ድጋፍና መሰል ወጪዎችም በአዲሱ መመርያ ተከልክለዋል፡፡ እንደ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ያሉትም በዚህ ክልከላ ከሚቀርብልን ቅጥ ያጣ ጥያቄ ተገላግለናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ሚኒስትር አብርሃም፣ ‹‹የግብር ከፋዩን ገንዘብ እያነሳችሁ ማንንም መሸለም አትችሉም፡፡ ገንዘብ ሚኒስቴር ስለከለከለ አይደለም፡፡ የሕዝብ ገንዘብ ስለሆነ ነው፡፡ ይህ መቆም አለበት፤›› ነው ያሉት፡፡

እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ያንሸራሸረው ስብሰባ ላይ በ2010 በጀት ዓመት ምንም ዓይነት የተጨማሪ በጀት የማይጠየቅበት፣ ይልቁንም እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ቢቻለው የአምስት በመቶና ከዚያም በላይ ወጪ ከተመደበለት በጀት በመቆጠብ አስተዋጽኦ እንዲያርግ ተጠይቋል፡፡ በዚህ መጠን እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት መቆጠብ ቢችል ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን እንደሚቻል ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ እስካሁንም ከ80 በላይ መሥሪያ ቤቶች፣ ከ560 ሚሊዮን ብር በላይ ከተመደበላቸው በጀት ውስጥ በመቆጠብ በጀት እንደቀነሱ ተገልጿል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በዚህ ዓመት ከተመደበው የ321 ቢሊዮን ብር የፌዴራል በጀት ተጨማሪ የክልሎች በጀት ሲታከልበት የአገሪቱ የ2010 በጀት ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ይገመታል፡፡ መንግሥት ለመደበኛ ወጪዎች ከመደበው ከ82 ቢሊዮን ብር ባሻገር የ115 ቢሊዮን ብር የካፒታል በጀት ሲመደብ፣ ለክልሎች በድጋፍ የሚሰጠው 117 ቢሊዮን ብር እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሰባት ቢሊዮን ብር ለዘላቂ ግቦች ማስፈጸሚያ ለክልሎች የሚከፋፈል ሲሆን፣ ከጠቅላላው የ321 ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ ለመንገድ ሥራ 46 ቢሊዮን ብር ወይም 23 በመቶ፣ ለትምህርት 43 ቢሊዮን ብር ወይም 22 በመቶ የካፒታልና የመበደኛ ወጪዎች ተመድበዋል፡፡
 

ተዛማጅ፡

    ድንገተኛ የገንዘብ ሚኒስትሩ ትውስታ? የግብር ገቢ አሰባሰብና የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛነት የ2010 በጀትን ለማሳካት እንደሚያዳግት የገንዘብ ሚ/ሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ አመኑ!

    የመንግስት መስሪያ ቤቶች የወጪ ቅነሳ መመሪያን ተከትሎ ከ560 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን ተችሏል

    ትልቁ የኢትዮጵያ ‘ፌደራል’ በጀት ድክመቱ፣ገጽታዎቹና ውስብስብ ችግሮቹ

    “የፍትህ ያለህ!” ያስባሉ የፓርላማ ኦዲት ሪፖርቶች በባለሙያዎች እይታ

 

%d bloggers like this: