የበረከት ስምዖን መበለት:                    ቀኑን ጠብቆ የመጣ ‘የኪራይ ሰብሳቢ’ ዋጋ!

5 Nov

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በከፍያለው ገብረመድኅን
 
ኢሣት አርብ ማታ (ኅዳር 3/2017) ባቀረበው ዜና በ300 ሚሊየን ብር ወጪ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ያለውና በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው ደብል ትሪ ባለ አራት ኮከብ ዘመናዊ ሆቴል ምሥጢራዊ የአቶ በረከት ስምዖን ንብረት ነው በሚል ሕወሃት ምርመራ እንዳስጀመረባቸው ተዘክሯል።

እኔ አቶ በረከትን መመርመር ይገባቸዋል ብዬ ያሰብኩት፣ ገና ድሮ ነበር።

ለምን በሉኝ?

ከአላሙዲ ጋር ባላቸው ግንኙነት ነው። ለነገሩ ሼክ አላሙዲም ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ እሥር ቤት መውረዱን ሬውተር አላረብያን ጠቅሶ በዛሬው ዕለት ዘግቧል።

ወደ ጀመርነው ስንመለስ፥ ገሃድ ወጥቶ የነበረው የአቶ በረከት ማን አለብኝነትና ከአላሙዲ የሚያገኙትን በአደባባይ ቆጥረው የሚረከቡበት ኪራይ ሰብሳቢነታቸው መብት በወቅቱ ምን ያህል አንጀት እንደሚያሳርር ማንም የተገነዘበው፣ በጽሞና ያለፈው/ያላለፈው ወይንም የሚያልፈው አይመስለኝም።

አቶ በረከት በሕወሃቶች ክፍፍልና በፖለቲካ ምክንያት ዛሬ ለዚህ ምርመራ ተጋላጭ ቢሆኑም፡ የሕወሃት አስተዳደር ውስጥ — ለጊዜው ነው እንጂ — ብቸውኛው ወንጀለኛ አያደርጋቸውም።

በዚህም ምክንያት፥ ይህንን ጽሁፍ የሚመለከቱ አንባብያን — አንዳንዶች እንደሚሉት — ሥንጥቁና አሁን ከሣሽ የሆነው ሕወሃት ንጹህ ነውና ሌሎቹን መመርመር ይችላል — የሚል መልዕክት በሽልምልም ሊያስተላልፉ እየሞክሩ ናቸው። ስለሆነም፣ ከሁሉ አስቀድሞ ሌሎቹን ቀርቶ ሕወሃት በቀኙም ይሁን በግራ መልኩ የራሱን የተግማማ ገበና መመልከት እንደማይችል አንባቢዎች ግንዛቤ ውስጥ እንዲያስገቡ ላስታውስ እወዳለሁ!

ቂመኛና መርዘኛው ሕወሃት በአቶ በረከት ስምዖን ላይ ስላገኘባቸው ሙስናና መረጃዎች የማውቀው ስለሌለ፡ ምንም አስተያየት መስጠት አልችልም።

ከአቶ በረከት ጋር በግልም ስለማንተዋወቅ፣ ግላዊ ቅሬታ የለኝም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ጥቁሩን ነጭ፣ ነጩን ሲያጠቅሩ በዘመነ የመንግሥት ቃል አቀባይነታቸው ባደረጉት አስከፊ አስተዋኦ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ አስታውሳቸዋለሁ። በተለይም የመሬት ዘረፋውንና በጋምቤላ የተካሄደውን የመንደር ግንባታ የሕወሃት ወንጀሎች ዙሪያ — እንደሌላው ሃገርና ወገን ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የራሴ የሆነ ከፍተኛ ቅሬታና ቅዋሜ ቢኖረኝም፣ ያ ግን የዚህን ጽሁፍና አመለካከቴን እንዳይቆጣጠር ራሴን በሚገባ አስጠንቅቄያለሁ።

በመጨረሻም፣ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ‘የወደቀ ዛፍ ምሣር ይበዛበታል’ የሚለውን መስሎ እንዳይታይ በአንባብያንን የበሰለ አመለካከት ተስፋ አደርጋለሁ! ለዚህም አንባብያን በኔና በሕወሃት አገዛዝ መካከል ገና ከመጀመሪያው ሃገር አፍራሽ ሥራውን ከተያያዘበት ጊዜ ጀምሮ ያለኝን የማውገዝና እዚያው በሩቁ አመለካከት አንባብያን ከተለያቱዩ ጽሁፎቼ እንደተገነዘቡ ተስፋ አደርጋለሁ!

ይህንን ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ ባለሥልጣኖች የእርስ በእርስ መነካከስ ሁኔታ አንድ ቀን እንዲህ ድራማ እስኪመስል ድረስ በዐይናችን እንደምናየው በግልጽ ይሰማኝ ነበር — ይህ አባባል ሃገሪቱ ውስጥ ተጣያቂነት አለ የማለት ትርጉም እንደማይሠጠውም ተስፋ አለኝ። የኔ አተረጓጎም የተመሠረተው፣ እንደዚህ ያለ የተግማማ ሥርዓት መጨረሻው መገርሰስ መሆኑን ከመገንዘብ፣ የባለሥልጣኖቹን እርስ በእርስ መነካከስ በመጠበቅ ነው።

እንዲህ ያለው ሥርዓት ብዙ ጊዜ ሲወድቅም — እንዳውሎ ንፋስ ወይንም ጎርፍ — በአካባቢው ያሉትን ጠራርጎ፣ ሁሉም ነገር እርስ በእርስ ተጠላልፎ መውደቁ አጠያያቂ አለመሆኑን ከሌሎች ሁኔታዎች በመማርም ነው።

ከዚያ በፊት ግን ባለሥልጣኖቹ እርስ በእርስ ዒላማ መደራረጋቸው የሚጠበቅ ነው። በመተማማት እንደሚጠላለፉ ሁሉ ገና ከንጋቱ እንስማ ነበርን። ከቅርብ ጊዜ ወዲህማ ኢትዮጵያ ውስጥ የኪራይ ስብሳቢነትና ጉበኝነት ጸያፍነት በመደብዘዙ፣ በመካከላቸውም አንዱ ሌላው ላይ ነጥብ ለማስቆጠር “ኪራይ ሰብሳቢ” አስገራሚ አለመሆኑን — ለኔ ድሮ የትምህርት ቤት ጓደኛ የነበረ ቀደም ሲል የእነርሱው ባለሥልጣን ሆኖ የሠራ ግለሰብ — ቀደም ሲል ውጭ ሃገር እንዳጫወተኝ!

እዚህ ላይ እኔን እንቅልፍ የነሳኝን የአንድ ምሽት ሁኔታ ልተርክላችሁ።

ለኔ አቶ በረከት ስምዖን፣ እንደሌሎቹ በሕወሃት ሥር እንደተራወጡትና እንደሚራወጡት፣ የሃገራችን ካድሬዎችና ባልሥልጣኖች — አንዳቸውም ሳይዘለሉ — “በኪራይ ሰብሳቢነት” በሂስና ግለሂስ መድረክ ሲስማ የተኖረው፣ ከመወንጀልና ከመጠየቅ ማምለጥ እንደማይገባቸው የመጀመሪያውን ግንዛቤ ያገኘሁባቸው ግለሰብ ናቸው።

ለዚህ መነሻዬም መድረሻዪም፣ ጆሮዬን የጣልኩበት የግል ባህሪያቸውና ከአላሙዲ ጋር ያላቸው ጥብቅ ትስስር ነው። ማን አለ ሕወሃት ውስጥ — ከመለስ ጭምር — የነበረውን ሥልጣን ተጠቅሞ ዘረፋ ያላካሄደው? የትኛው ሹም ነው አላሙዲን ከሃገር ገንዘብ ለማሸሽ ያልተጠቀመበት ቱባ ባለሥልጣን አትበሉኝ እንጂ!

ስለዚሁ አላሙዲ በአደባባይ የበረከት መጽሐፍ የተመረቀበት ምሽት ግብዣ ላይ ሲናገር

“ከዋናው ሰውዬ ጀምሮ ወዳጆች ነን፤ ተግባብተን እና ተቻችለን ነው የምንኖረው፤ እኔ ግን አንድ ቀን እንዲህ ሆንኩ ብዬ ቅሬታ አቅርቤላቸው አላውቅም እንደውም እነሱ እንደኔ ሁሉንም የሚጭኑበት ሰው የለም” ማለቱን አስታውሳለሁ!

መቼም ጉቦ ሠጥቻቸዋለሁ እንዲል መጠበቅ፡ ከየዋህነት ባሻገር የእርሱንም ራሱን ያለመውንጀል መብት መጋፋት ይሆናል።

በነገራችን ላይ በአሁኗ ሰዓት፥ አላሙዲ በሳኡዲ አረቢያ በሙስና ወንጀል መታሠሩን የሃገሪቱ ጋዜጦች ጥቆማ እየሰጡ ነው!

አቶ በረከት ስምዖን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦርድ ሊቀ መንበርነታቻው ሃገራችንን ለምዘበራ አጋልጠው፣ በእርሳቸው ግንባር ቀደም ኪራይ ሰብሳቢነት ምክንያት ኢትዮጵያ ምን ያህል እንደተመዘበረች መገመት ይቻላል። ከሠፋፊ የገጠር መሬቶች ገበሬዎቻችን እየተፈናቀሉ፡ ልማቱም በዘረፋ ምክንያት ላይሳካ፥ የተለያዩ የልማትና የንግድ መንግሥታዊ ድርጅቶችን ዕዳ ለማይከፍል — ለማስገደድም ባለሥልጣኖቹ የመለስና የበረከትን ጫና እየፈሩ በሚኖሩባት ሃገር — በረከት ብድር በተከለከለበት ወቅት እንኳ ቱጃሩ እስከ ቢሊዮን ብር ያሠጡ ባለሥልጣን መሆናቸውን አግባብ ይመስለኛል!

እዚህ ሃገር እንመራለን ብለው ከመለስ ዜናዊ እስከ ታችኞቹ ባልሥልጣኖች ድረስ በሼኩ እጅ እንደሆኑ ሸራተን የበረከትን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ናይሮቢ በራሱ ወጭ እንዲሁም የበረከትን ሚስት ወንድም የመዘመርን መጽሐፍ ሼኩ በነጻ እንዳሳተሙላቸው ለተጋብዡ በራሳቸው አንደበት ሲናገሩ መስማቱ የሕውሃት አመራር በአጠቃላይ ሆድ አደር፣ ወራዳ ኪራይ ሰብሳቢዎች ስብስብ እንደሆነ ማወቁ እጅግ ያስገርማል!

በወቅቱ ከጀመርኩት ያን ጊዜ ሁለት ዓመት የሞላት ብሎጌ (Transforming Ethiopia (TE)), አሁን The Ethiopia Observatory (TEO)) ላይ የመጽሃፉ ምረቃ ዕለት ሌሊት የተወሰኑ ነጥቦችን በማንሳት ቅሬታዬን ዘግቤ አደርኩ፟። ከዚያም ብዙ የከነከኝ ነገር ሆኖ እንደገና ያንኑ ጽሁፍ በመጠኑ በማሸት ጥር 18/2013 እዛ ውስጥ ውስጥ የሚከተለው ነገሮች ጋር ተደማምሮ ወጥቷል፦

    “…Ato Bereket openly announced that his book and that of his brother-in-law’s were published in Nairobi, with full publication costs covered from the sheik’s deep pocket on the basis of — his words — “the instruction” he gave the sheik.

    Not only that. The sheik is also caretaker of the minister’s health, for whose maintenance not long ago he paid a hefty sum in Rands in South Africa, including arranging for the patient to fly by private jet.

    Surely, in the eyes of the leadership this would be considered a crime only when someone outside their circle does it or when a member outlives his usefulness. Certainly, they would inflict on him or her the full force of the law as punishment, which Ethiopian law provides up to ten years of imprisonment for influence peddling and kickbacks received by officials.”

በረከትም በስካር ይሁን በአለቆቻቸው በመተማመን ይህንኑ በአደባባይ በመናገራቸው፣ እኔም ግብዣው ዲጂታሊ በመተላለፉና ፊንላንድ ሆኜ በመስማቴ፣ በወቅቱም ሆነ ዛሬ ምናልባትም አቶ በረከት ስምዖን በገሃድና በነጻነት ኪራይ ሰብሳቢ እንዲሆኑ የመጀመሪያው ‘ሊቼንሣ’ የተሠጣቸው ሕወሃታዊ ባለሥልጣን ሣይሆኑ አይቀሩም ቢባል ማጋነን አይደለም እላለሁ።

ነገሩ እጅግ የከነከነኝ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያን የንግድ ማኅበረሰብ እንደመዳፉ የሚያውቅ አንድ ወዳጄ ከኢትዮጵያ መጥቶ ፈረንሣይ ተገናኝተን ጥሩ ወይን ጠጅ ጉሮሯችንን እያለሳለሰ ብቻ ሳይሆን፣ ሰሜታችንን እያዝናን ሳለን፣ “ከመንግሥት ባልሥልጣኖች ሁሉ በረከት ለገንዘብና ለሙስና ያልተራወጠ ፖለቲካውን ሃይማኖቱ ያደረገ ይመስለኛል” አልኩ! ብርጭቆው ሥር የተደበቀ ሰው/ወንም ሌላ ነገር ያለ ይመስል ወደ ላይ ብድግ አድርጎ በብርሃን ከተመለከተ በኋላ፣ ብርጭቆው ወደ ጠረጴዛው ሳይመለስ “አንተ አልክ!” ያለው ጆሮዪ ውስጥ ሳይደላደል፣ “ግሩም ወይን!” ብሎ በተዘዋዋሪ የጫወታችንን መቀየር ምልክት መስጥቱ ነው ብዬ፣ የሚቀጥለውን ጨዋታ እርሱ እስኪጀምር ወደ ዝምታ አጋደልኩ!
 

ለመሆኑ ኪራይ ሰብሳቢነት ምንደነው?

ደመቀ መኮንን ም/ጠ/ሚኒስትር ሆነው በተሾሙ ማግሥት፥ ሼክ አላሙዲ ደመቀን በመዳፋቸው ሲያስገባ። በወቅቱ ይህ የካፒታል ፎቶ Sheiking Demeke ተብሎ TEO ላይ ጥቅምት 11/2012 ወጣ! https://ethiopiaobservatory.com/2012/10/11/al-amoudi-sheiking-demeke-come-on-tell-me-desires-of-your-heart-ill-get-it/

ታዲያ ከላይ የተጠቀስው ያ አርብ ማታ አቶ በረከትን የሕወሃት አንዱ ወገን (እንደሚባለው ከሆነ) እንደ ብልት በልቶ የመጣል ዘመቻ መጀመርን በዜና ስሰማ በጣም ነው የተደነቅሁት።

እንዲያውም አንድ ምሽት ታህሳስ 22/2011 — ከብዙ ሻምፔኝና… ራት በኋላ ሁለቱም ወንድማማቾች መሆናችውን በሚዲያ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሲያስተጋቡ ከሰማሁ በኋላ — ኢትዮጵያ ውስጥ ከሕወሃቶች አንደበት ከሚወጣው ብልግና ሁሉ ጆሮዬን ቋቅ የሚለው ቃል — በእነርሱ አንደበት ስድብ የተደረገው ይኸ “ኪራይ ሰብሳቢ” የሚባለው ቃል ነው።

ለነገሩ “ኪራይ ሰብሳቢ/ነት” የፖሊቲካል ኤኮኖሚ ጽንሰ ሃሣብ የሚገልጽ ቃል/ተርሚኖሎጂ ነው — ከልማት የሚገሸሸውን ገንዘብ/መዋዕለ ንዋይ አመላካች ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ‘ልማታዊ መንግሥት’ የሚባለው እንደነሕወሃትና የሩዋንዳው የመሰሰሉት፡ በዘረፋ ወይንም ሙስና የሚባክነውን ማሸሺያ አሳጥተነው ወደ ልማት እንዲገባ ማድረግ ማስቻልን የጨምራል ይላል መለስ ዜናዊ ከመሞቱ በፊት በ2012 ‘States and Markets: Neoliberal Limitations and the Case for a Developmental State’ በወጣው ጽሁፉ፦

    “‘Rent-seeking’ refers to the generation of rents to serve particular economic and political interests, as opposed to the various forms of rent creation and use that are inherent in development processes.”

የልማታዊ መንግሥት ችግሩ የመሪዎቹ ፍላጎት እንጂ የሕዝቡን ስለማያንጸባርቅ በሕወሃት እንዳየነው፣ ራሱን የቻለ የዘረፋ ቀዳዳ ነው!

ባለሥልጣኖቹም በአደባባይ በዳረጎት ወይንም ሰወር ያለ ጉቦ በአደባባይ እንደነ በረከት ስምዖን ሲቀበሉ እንዳየነው፡ የዚህ ዐይነቱ ሃብት ለልማት መዋሉ አጠራጣሪ ነው።
 

%d bloggers like this: