ሲሚንቶ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ቀውስ ምልክት: በሲሚንቶ ዕጥረት በርካታ ግንባታ ቆሟል፣ ሠራተኞች ተበተኑ የሚል አበቱታ የሥራ ተቋራጮች አሰሙ!

14 Nov

የአዘጋጁ አስተያየት፡

    ማኑፋክቸሪንግ በብሄራዊ ምርት ውስጥ ያለው ድርሻ እስካሁን ከአምስት ከመቶ አልበለጠም። የሲሚንቶ ምርት ለብቻው መዳክም ወይንም መቆም ግን፡ በሕንጻዎች፥ ፋብሬካዎችና በመሠረተ ልማቶች ወዘተ ግንባታ ያለው ተፈላጊነት እጅግ ሠፊ በመሆኑ፣ ይህ በኤኮኖሚ ዕድገ፣ትና በአጠቃላይ የሃገሪቱ ልማት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል።

    ስኳር ለተጠቃሚዎችና ለፋብሪካዎች ያለው አስፈላጊነት የታወቀ በመሆኑ፡ እስካሁን በኅብረተሰቡ በኩል ከፍተኛ ምሬት የተሰማበት ሸቀጥ ነው። የሲሚንቶ ምርት መቆም ደግሞ በሠራተኛ ገቢ በኩልም ብቅ ስለሚል፡ እስካሁን ካየናቸው የሸቀጣሸቀጥ ዕጥረቶች የከፋና የኤኮኖሚው ጤንነት መቃወስ ቀዳሚው ምልክት ሆኖ ወደሚታይበት ሁኔታ ልንሸጋገር እንችላለን!

==========================
 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
አዲስ አበባ፣ ህዳር 5፣ 2010 (ኢዜአ) የሲሚንቶ እጥረትና የክፍያ መዘግየት ምክንያት በርካታ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መቆሙን አሰተያየታቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሰጡ የስራ ተቋራጮችና አማካሪዎች ተናገሩ።

ብዙሃኑ ስራ ተቋራጮች ሰራተኞቻቸውን እስከመበተን ደርሰዋል።

ችግሮች እየተደራረቡበት ያለው የ20/80 የቤት ልማት መርሃ ግብር በተያዘለት ፍጥነት መጓዝ እንዳልቻለ የበርካቶች ትዝብት ነው።

ከሰሞኑ ሰፈራ አራብሳ ወደ ተባለ የአዲስ አበባ አካባቢ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘጋቢ አምርቶ ነበር።

በዚህ አካባቢ ዓመታትን ያስቆጠሩ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታዎች በጅምር ላይ ባሉበት እንደሚገኙ ታዝቧል።

ግንባታዎቹ በየካ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስር ያሉ ሲሆኑ፥ ፅህፈት ቤቱ 61 የስራ ተቋራጮችን ይዞ 140 ህንፃዎችን እየገነባ ቢገኝም የህንፃዎች ግንባታ ግን በችግር ተተብትቦ ተይዟል።

በዚህ ችግር ምክንያትም አንዳንዶቹ ግንባታዎች አራት ዓመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን፥ የተቀሩት ደግሞ ከሁለት ዓመታት ያላነሰ ጊዜ ወስደው ከአንድና ሁለት ፎቅ በላይ መደርደር አቅቷቸው እንደቆሙ ናቸው።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አማካሪና ስራ ተቋራጮች ለዚህ ጉድለት በርካታ ችግሮችን ያቀረቡ ሲሆን፥ የዚህ ግንባታ ፕሮጀክት ዋነኛው ማነቆ ግን የሲሚንቶ አቅርቦት ችግር ነው፤ ሲሚንቶ በዚህ የግንባታ መንደር ውስጥ አሁን ላይ የለም ማለት ይቻላል ይላሉ።

በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት በርካታ ስራ ተቋራጮች መስራት የሚገባቸውን ስራ እየሰሩ አይደሉም፤ ሰራተኞቻቸውንም እንደበተኑ የተናገሩ ስራ ተቋራጮች አሉ።

የሲሚንቶ እጥረቱ ግንባታውን ብቻ ሳይሆን ያስቆመው እንደ ፕሪካስትና ብሎኬት ያሉ የግንባታ ግብዓትች ላይም አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሯል።

ስራ ተቋራጮቹ እና አማካሪዎቹ ይህን ችግር በተመለከተ በተደጋጋሚ ቢናገሩም፥ ችግሩ ተፈቷል ከማለት በዘለለ በተጨባጭ መልስ ማግኘት እንዳልቻሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የየካ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ መለስ ተገኘ እና ሌሎች የስራ ሀላፊዎች አሁንም ምላሻቸው ችግሮቹ እየተፈቱ ነው የሚል ሆኗል።

በእርግጥ ላለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ችግሮችን እንዳለፉ ስራ አስኪያጁ አቶ መለስ ይናገራሉ።

ለአብነት የፕሪካስት ምርት እጥረት አጋጥሞ ነበር፤ እጥረቱ እንዲከሰት ምክንያት የሆነው ደግሞ ከግንባታ አካባቢው ውጪ ባሉ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ማህበራት በአግባቡ ጥራት ያለው ምርት ማቅረብ ባለማቻላቸው ውላቸው እንዲቋረጥ በመደረጉ ነው።

ውላቸው ሲቋረጥ እነሱን የሚተኩ ማህበራት ባለመኖራቸው ለወራት ያህል የፕሪካስት ምርት አቅርቦት ችግር ነበር።

አሁን ግን ወደ 10 የሚጠጉ ማህበራት ገብተው እየሰሩ ስለሚገኙ የፕሪካስት ምርት ችግር የለም ይላሉ አቶ መለስ።

የስላቭ ብሉኬት እና የግድግዳ ብሉኬት የአቅርቦት ችግር የለም የሚሉት አቶ መለስ፥ አሁን ላይ ዋነኛ ችግር የሆነው የሲሚንቶ አቅርቦት ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል።

አሁን ፕሮጀከት ፅህፈት ቤቱ እያደረገ ያለው በመጠን ያነሰውን የሲሚንቶ አቀርቦት እየሰጠ የሚገኘው ፕሪካስት፣ ብሎኬት እና ስላቭ ብሎኬት ለሚያመርቱ ማህበራት ነው።

ስራ ተቋራጮች ግን የሲሚንቶ ግብዓት የማይሰጣቸው ሲሆን፥ የሲሚንቶ እጥረቱ የከፋ መሆኑን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘጋቢ በመኖሪያ መንደር ግንባታ አካባቢዎች ባደረገው ቆይታ ተመልክቷል።

የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ በበዙበት ሃገር በቤት ልማት መርሃ ግብር ላይ እንዴት የሲሚንቶ ግብዓት እጥረት ይነሳል? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ይህ የሲሚንቶ እጥረት ደግሞ የአንድ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ችግር ብቻ ሳይሆን፥ መጠኑ ቢለያይም በ18 የከተማዋ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤቶች ላይ የሚስተዋል ነው።

ከዚህ ቀደም የግንባታ ግብዓቶችን ገዝቶ የሚያቀርበው ራሱ የከተማዋ ቤቶች ልማት ፕሮጀከት ጽህፈት ቤት ነበር።

አሁን ግን የፕሮጀክት ፅህፈት ቤቱን የግዥ ስራዓት ለማስተካከል ሲባል በከተማዋ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በኩል ሁሉም የግንባታ ግብዓቶች ተገዝተው ነው የሚቀርቡለት።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀከት ፅህፈት ቤት ለሲሚንቶ እጥረት የመዳረጉ ምክንያትም፥ ከዚህ እንደሚመነጭ የፕሮጀከት ፅህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ሓረጎት ዓለሙ ይናገራሉ።

ጨረታ አውጥቶ አወዳድሮ አሸናፊው እስኪታወቅ ድረስ ረጅም ጊዜ መውሰዱ ለዚህ ችግር ዳርጎናል ነው ያሉት አቶ ሓረጎት

በእርግጥ ይህን እጥረት ለማቃለል ጊዚያዊ መፍትሄ ለመስጠት ሲባል እስከ 200 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ፥ ከሙገር በቀጥታ ፕሮጀከት ፅህፈት ቤቱ ግዥ በመፈፀም ችግሩን ለማስታገስ ቢሞከርም ፍላጎቱን አላረካም።

የከተማዋ የመንግስት ግዥ አስተዳደር በጨረታ አሸናፊ ናቸው ያላቸውን የሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎችን በመለየቱ፥ ከዚህ በኋላ ሲሚንቶ ችግር የሚሆንበት ሁኔታ አይኖርም ባይ ናቸው።

የስራ ተቋራጮች ግን የሲሚንቶ ችግር ቢፈታም ሌላም ችግር መኖሩን በመጥቀስ፥ ለሰራነው ስራ ሊፈፀምልን የሚገባው ክፍያ በመዘግየቱ በስራችን ላይ ጫና እያሳደረብን ነው ብለዋል።

አቶ ሓረጎት ክፍያን በተመለከተ የፕሮጀከት ፅህፈት ቤቱ ችግር አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተንዛዛ የክፍያ ስርዓት የሚከተል በመሆኑ ከዚህ የመጣ ችግር ነው ሲሉ ችግሩን ከፅህፈት ቤታቸው አርቀውታል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ጣቢያችን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስራ ሃላፊዎችን አግኝቶ ለማናገር ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል።

ፕሮጀከት ፅህፈት ቤቱ ግን ከእነ ችግሮቹም ቢሆን እየገነባቸው ያሉትን የመኖሪያ ቤቶች፥ በተያዘው ዓመት ግንባታቸውን ሰማኒያ በመቶ ለማድረስ እቀዶ እየተጓዘ ነው።
 

%d bloggers like this: