በኢንዱስትሪ ፓርኮች የግንባታ መዘግየትና የተጠናቀቁትም ወደ ሥራ ያለመግባት ችግሮች ሊፈቱ ይገባል ይላል የሕወሃት ተወካዮች ምክር ቤት- በሕገ ወጥ አሠሪዎች ሠራተኞች ላይ የሚደርሰው ጉዳትና ጉልበት ምዝበራ ሕወሃት ጉዳዩ እንዳልሆነ ታይቷል!

14 Nov

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 5፣ 2010 (ኢዜአ) በግንባታ ላይ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የግንባታ መዘግየት፣ የተጠናቀቁትም በቶሎ ወደ ስራ ያለመግባት ችግሮች መኖራቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ።

ግንባታቸው የተጠናቀቁት የኮምቦልቻ እና የመቀሌ የኢንዱስትሪ ዞኖች ወደ ምርት ገብተው የስራ እድል እየፈጠሩና ኤክስፖርቱን እየደገፉ አይደለም ተብሏል።

የምክር ቤቱ የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን የሩብ ዓመት ሪፖርት እና የ2010 ዓ.ም ዕቅድ ገምግሟል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኤክስፖርት እጥረቱን ከመቅረፍ እና የስራ ዕድል ከመፍጠር አንፃር ሚናቸው ከፍተኛ ቢሆንም፥ ግንባታቸው እንደሚዘገይ እና ምርታማነት የማሳደግ ክፍተት እንዳለባቸው ገልጿል ቋሚ ኮሚቴው።

ግንባታቸው ከዘገዩት መካከል የባህር ዳር፣ ጅማ፣ ደብረ ብርሃን፣ ድሬዳዋ እና አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገኙበታል።

በሌላ በኩል የኮምቦልቻ እና መቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው የተጠናቀቀ ቢሆንም፥ ለባለሃብት አልተላለፉም፤ ማምረትም አልጀመሩም።

ለወጣቶች ይፈጠራል የተባለው የስራ ዕድል በተፈለገው መልኩ እየተተገበረ አለመሆኑን ጠቅሶ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ተመጣጣኝ ክፍያ የመፈጸም ችግሩ ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲያስረዱ ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል።

ከምክር ቤቱ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠው ኮርፖሬሽኑ፥ የተባሉት ችግሮች መኖራቸውን እና አንዳንዶቹ ግን በሌሎች አካላት ያልተሰሩ ስራዎች በመኖራቸው የተፈጠሩ እንደሆኑ አስረድቷል።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሲሳይ ገመቹ እንዳሉት፥ ለግንባታዎቹ መዘግየት የተቋራጮች በጊዜው አለማስረከብ እና የክረምቱ ወቅት መራዘም ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል።

የኮምቦልቻ እና መቀሌ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በኩል የኃይል አቅርቦት የመጠየቅ እና የማሽን ተከላ ሂደት ጊዜ በመውሰዱ ወደስራ ለመግባት አልተቻለም ነው ያሉት።

በተጨማሪም በሁለቱ ፓርኮች ያልተጠናቀቁ ስራዎች ለምርት ስራው አለመጀመር መንስኤዎች ናቸው ብለዋል።

የፓርኮቹን ስራ ማፋጠን እና ድጋፍ መስጠት የሚችሉ ልምድ ያላቸው ሰራተኞች በክፍያ ማነስ ምክንያት መልቀቃቸውም ሌላው ችግር መሆኑን ጠቁመዋል አቶ ሲሳይ።

የኮርፖሬሽኑ ምክትል ስራ አስፈፃሚ እና የኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ሽፈራው ሰለሞን በበኩላቸው፥ የስራ እድል ከመፍጠር አንፃር በፓርኮቹ የተሻለ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

ሙሉ በሙሉ ማምረት በጀመሩት ሃዋሳ እና ቦሌ ለሚ ፓርኮች ለ25 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ጠቅሰው ሆኖም ከደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ማነስ ጋር ተያይዞ የሰው ሃይል ፍልሰት መኖሩን ተናግረዋል።

ችግሩን የፈጠረው ደግሞ ወጣቶቹ ከመምጣታቸው በፊት የሚነገራቸውና ሲመጡ የሚያገኙት ባለመጣጣሙ ነው ብለዋል።

በፓርኮች አካባቢ የተሻለ ክፍያ ለማግኘት ምርታማነት ስለሚያስፈልግ የክህሎት ክፍተት ላይ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የወጪ ንግዱን ለማሳደግ የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶችን በመሳብ ረገድ ከኢንቨስትመንት ሚኒስቴር ጋር እየሰሩ መሆኑንም ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት የሀዋሳ እና ቦሌ ለሚ አንድ ፓርኮች የአገሪቱን የወጪ ንግድ ያሳድጋሉ ተብሎ እየተሰራባቸው መሆኑንም አክለዋል።

በ2010 ዓ.ም ዕቅድ መሰረት የድሬዳዋ፣ አዳማ፣ ጅማ፣ ደብረ ብርሃን እና ባህርዳር እንዲሁም የቦሌ ለሚ ሁለት ፓርኮች ይጠናቀቃሉ ቢባልም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ስጋት መኖሩን አቶ ሲሳይ አመልክተዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር የካሳ ክፍያ ላይ ተገቢው ስራ እንዲሰራ፣ ከስራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዞም ለወጣቶች በተለይም ለሴቶች ትኩረት እንዲሰጥ አስገንዝቧል።

በተጨማሪም የወጪ ንግዱን ከማሳደግ አንፃር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ ረገድም ኢንቨስትመንቱን ከፍ ለማድረግ ስራቸውን በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም አሳስቧል።
 

%d bloggers like this: