ንብረትነቱ የኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ ኩባንያ የሆነ ማሳ በተቃዋሚዎች መቃጠሉ ተገለፀ

19 Nov

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

ከአዲስ አበባ 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምዕራብ አርሲ ዞን በሻሸመኔ አቅራቢያ ቢሻን ጉራቻ ተብሎ በሚጠራዉ ቦታ በ70 ሄክታር መሬት ላይ የተመረተ በቆሎ በተቃዋሚዎች መጋየቱን ፎርቹን ሳምንታዊው ጋዜጣ የዘገበዉን መነሻ በማድረግና የእራሱም ምንጭ በመጨመር ትንሳኤ ሬዲዮ ኅዳር 18/2017 አስታወቀ።

ይህ ንብረትነቱ በአካባቢው ከሚገኙት ከአራቱ የሚድሮክ እርሻዎች አንዱ የሆነው የኤልፎራ አግሮ እንዱስትሪ ኩባንያ የተቃጠለው ረቡዕ ከሌሊቱ 7 ሰዓት ላይ እንደሆነና ከሸሬ ቦራኖ እና ቸጌ ከተባሉ አጎራባች ቀበሌዎች ተደራጅተው በመጡ ወጣቶች እንደሆነ ተገልጿል።

በኤልፎራ እርሻ ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን እስከአሁን በትክክል ባይታወቅም በመሬቱ ላይ ከነበረው የደረሰ የበቆሎ ሰብል ሦስት አራተኛዉ እንደወደመ የምንጮቹን ግምት ጠቅሶ ጋዜጣው ዘግቧል።

ስለጉዳዩ የኤልፎራን ማኔጀር አቶ አንበሴ አስራትን አነጋግሮ ለማጣራት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ ግን ማኔጀሩ መግለጫ ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆኑም በእርሳቸው የተመራ ልዑክ በሚቀጥለው ቀን ወደቦታው በመሄድ የደረሰዉን ዉድመት መጎብኘታቸዉና በስፍራው ያሉትን ሠራተኞች ማነጋገራቸው ታውቋል።

የኤልፎራ እርሻ ልማት 630 ጊዜያዊና ቋሚ ሠራተኞች እንዳሉት እና የዚህ ዓይነት እርምጃ ሲወሰድበትም ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ተገልጿል። ከዚህ ጥቃትም ጋር ተያይዞ በፖሊስ 51 ሰዎች መታሰራቸውንና ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን አስታውቋል።
 

%d bloggers like this: