በሕዋታዊ አሠራር የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ወደ ቤተሰቦች መጠቃቀሚያነት መሸጋገር የዲፕሎማሲን ሥራና ከበሬታ አሽቀንጥሮ መጣሉ ቅሬታዎችን አበራከተ! የኢትዮጵያ በዘፈቀደ የማይገሠሡ ሃብቶቿ፡ክብርና ጥቅሞች የቶቹ ይሆኑ? የዓሣ ግማቱ…

23 Nov

የአዘጋጁ አስተያየት፦

  በጣም በተወሰነ ደረጃ፣ ይህ አሠራር ተቀባይነት ሊኖረው ቢገባም፣ የዚህ ዐይነቱ ውሱን አሠራር መለኪያው — ከሁለቱ የአንዱ፣ ማለትም የባል ወይንም የሚስት — ሙያ ተፈላጊነት ብቻ ሊሆን በተገባ ነበር!

  Ambassador Tirfu Kidanemariam Gebrehiwet (Eth Embassy)

  ሃገሪቷ የሕወሃቶች መፈንጫ በመሆኗ፡ በ2015 ሕወሃት ራሱ ወ/ሮ ትርፉ ኪዳነማርያምን — የሕወሃት ሊቀመንበር ዐባይ ወልዱን ባለቤት የሚጥልበት ቦታ ሲያጣ — ግንባሩ በድምጽ ብልጫ ፖሊትቢሮም ሆነ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት በመንፈጉ — ያላንዳች ሙያና ብቃት አውስትራሊያና ኒውዚላንድ አምባሳደር አድርጎ መሾሙ፣ የዲፕሎማሲ ባለሙያዎችን ማስገረሙ ብቻ ሣይሆን፣ አምባሳደሯ በተራ ካድሬነትና የትግራይ ጸረ-ሙስና አመራር ሆነው ከመሥራት ውጭ ምንም ስለሌላቸው፣ በስብሰባ ላይ ከስድብ ውጭ የሚያውቁት ባለመኖሩ፣ ግለሰቧ ከኮሚኒቲው እንዳይገናኙ ውሱን ሆነው መቀመጣቸው — የቴድሮስ አድሃኖም መፍትሄ — ለሥራው ያላቸውን አላስፈላጊነት ገሃድ ካደረገው ከሁለት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል!

  ጥቅምት 31/2016 በተጻፈ — ከሪፖርተርም በተገኘ መረጃ ስለወ/ሮ ትርፉ የሚከተለውን አሥፍሬ ነበር።

   “When the 12th TPLF Congress chased away Tirfu Kidanemariam from both the Central Committee of the TPLF and its politburo, Tedros Adhanom was the one who welcomed her. She chose ambassadorial post in Australia and New Zealand. She got it, not because she had either the education or the skills; she is the wife of Abay Woldu, the chief of Tigray region and the chairman of the ruling TPLF.”


  ሕወሃቶች ለራሳቸው ጠቃሚና ዋና ከተማዎችን ከመያዛቸው ባሻገርም፣ ንግድም የሚካሄድባቸውን ከተሞችና ሃገሮችን በመምረጥ፣ ከነቤተሰቦቻቸው ተጠቃሚ እየሆኑባቸው ናቸው።

  ስለሆነም ይህ የአሁኑ አመዳደብና አሠራር አዲስ ነው ማለት አይቻልም። እጅግ አሳፋሪና አሳዛኝ ነው!

=================
 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
ዋዜማ ራዲዮ– በቅርቡ በተለያዩ ሀገራት ከተመደቡ አምባሳደሮች መካካል የተወሰኑት የትዳር አጋሮቻቸውን በመንግስት ተሿሚነት ማስመደባቸውን የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ምንጮች ለዋዜማ አጋለጡ።

በዲፕሎማቲክ ምደባ ላይ ወትሮም ቢሆን ፖለቲካዊ ውሳኔ ከፍ ያለ ተፅዕኖ ሲፈጥር መቆየቱን የተናገሩት የመስሪያ ቤቱ ባልደረቦች አሁን የተደረሰበት ደረጃ ግን የገዥውን ፓርቲም ሆነ የሀገሪቱን ጥቅሞች የሚፃረር ነው ብለዋል።

በሰኔ ወር መጨረሻ ከሚንስትርነት ለተነሱና ለሌሎች አስራ ሁለት የገዥው ፓርቲ አባላት የዲፕሎማቲክ ሹመት መሰጠቱን ያስታወሱት ምንጮቻችን በዩናይትድ ስቴትስ የተመደቡት አቶ ካሳ ተክለብርሀን ባለቤታቸው የኤምባሲው ባልደረባ ሆነው እንዲመደቡ አድርገዋል።

በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ወሮ አስቴር ማሞ ባለቤትም እንዲሁ የዲፕሎማቲክ ኮር አባል በመሆን ከመንግስት ደሞዝ የሚቆረጥላቸው ተቀጣሪ ተደርገዋል።

ሌላው በተመሳሳይ ባለቤታቸውን ያሾሙ ባለስልጣን በቤልጂየም ብራስልስ አምባሳደር የተደረጉት አቶ እውነቱ ብላታ ሲሆኑ የትዳር አጋራቸውን ለማሾም ከውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጋር ከፍተኛ እሰጥ አገባ እንደነበረባቸው ምንጮቻችን ይናገራሉ።

በሰኔ ወር በተደረገው ሹመት በተለይም ብራስልስ የተመደቡት የአቶ እውነቱ ብላታ የሚስቴ በጀት ተመድቦላት ትቅጠር የሚለው ጥያቄ ከሌሎች በተለየ ውድቅ በተደረገ ሰአት በቀጥታ ኦህዴድ ጣልቃ እንደገባበትም ሰራተኞቹ ይናገራሉ።

ዋዜማ ፎቶዎች

የአምባሳደሮችም ሆነ የዲፕሎማቲክ ስራተኞች ወደ ምድብ ሀገሮቻቸው የትዳር አጋሮቻቸውን ይዘው መሄድ ሙሉ መብት ያላቸው ቢሆንም የትዳር አጋሮቻቸው በመንግስት በጀት ደሞዝ ተከፋይና የመንግስት ተቀጣሪ አድርጎ መውሰድ አዲስ ክስተት መሆኑን ያነጋገርናቸው የመስሪያቤቱ ባልደረቦች ይናገራሉ።

በዘርፉ ልምድ ያላቸውን ወጣት ዲፕሎማቶች ዕድልም የሚዘጋ መሆኑን የሚያስምሩበት አሉ።

በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ከፍ ያለ ቁጥር የሚይዙት የብአዴንና የኦህዴድ አባላት መካከል ብርቱ ሽኩቻ መኖሩን የሚናገሩት የመስሪያ ቤቱ ምንጮች በፓርቲ ሽፋን ጥቅም የማጋበስ እንቅስቃሴ ጎልቶ መታየቱንና ይህም የሀገሪቱን ዲፕሎማሲ በብርቱ የሚጎዳ መሆኑን በአሁኑ ስዓት በዲፕሎማትነት ተመድበው የሚሰሩ አንድ ባልደረባ ነግረውናል።

“የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ ስራ በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ የተንጠለጠለ ነው። ይልቁንም በታሪክ ባለን ስኬታማ ስራ ምክን ያት ተቀባይነታችን የጎላ ነው። አሁን በተያዘው መንገድ ከቀጠልን ለሀገሪቱም ውርደት ነው” ይላሉ አስራ ሁለት አመታትን በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሰሩት እኒህ ግለሰብ።

“በውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከግልና ከፓርቲ ጥቅም የበለጠ የሀገራቸውን ፍላጎት የሚያስቀድሙ በብቃት ደረጃም የተሻሉ የሚባሉ አንጋፋና ወጣቶች ያሉ ቢሆንም አሁን እየተሄደበት ያለው አስራር ብዙ ዋጋ የሚያስከፍለን ይሆናል” ይላል በኣአውሮፓ በዲፕሎማትነት ቆይቶ ከሶስት ዓመት በፊት ከመስሪያ ቤቱ የለቀቀ የቀድሞ ባልደረባ።

ቀደም ሲል በአምባሳደርነት አገልግለው ወደ ሀገር ቤት የተመለሱ ዲፕሎማቶችን በአስራ አንድ የተለያዩ የመግስት ተቋማት በሀላፊነት ለመመደብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ስምተናል።

የአገልግሎት ጊዜን ከጨረሱ በኋላ ወደ ሀገር ቤት አለመመለስ በተለይ በበታችና በመካከለኛ የዲፕሎማቲክ ሰራተኞች ዘንድ እየተበራከተ መምጣቱን የሚናገሩት የመስሪያ ቤቶ ባልደረቦች በአጠቃላይ ችግሮች ላይ ከሚንስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በኩል ምላሽ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።

ከሚንስትሩ መልስ ካለገኙ ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሄደው አቤት ለማለት ዕቅድ እንዳላቸው ሰራተኞቹ ይናገራሉ።
 

%d bloggers like this: