ክልል 5 ሕወሃትን ማጋለጡ/ማንጓጠጡ? የሶማሌ ክልል አስተዳደር ከፊዴራል መንግሥት ቁጥጥር ውጭ በመሆን ግጭቶች ማጫሩና ማካሄዱን መቀጠሉን ፌደራል መንግሥቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ አመነ!

27 Nov

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
ግጭት ላይ የተሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ማዋል ላይ በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች በተመሳሳይ ደረጃ እየተሰራ እይደለም

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ላይ በተከሰተው ግጭት ላይ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር በማዋል በሁለቱ ክልሎች በተመሳሳይ ደረጃ እየተሰራ አንዳልሆነ መገምገሙን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ተናገሩ።

የፌደራል እና አርብቶ አደር ልማት ጎዳዮች ሚኒስቴር ጨምሮ ዘጠኝ የፌደራል መስሪያ ቤቶች የተካተቱበት ግብረ ሃይል ትናንት በምከትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ሰብሳቢነት የእስካሁኑን ስራ ገምግሟል።

ዶክተር ነገሪ ሌንጮ (ፋና ፎቶ)

የመንግስት ከሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ግምገማውን በማስመልከት በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።

ዶክተር ነገሪ፥ በመድረኩ በሁለቱ ክልሎች ያለውን የፀጥታ ሁኔታ መገምገሙን የገለፁ ሲሆን፥ በዚህም በአሁኑ ጊዜ ችግሩ መቶ በመቶ ቆሟል በሚል መደምደም ባይቻልም በምስራቁ አካባቢ የተሻለ የሰላም ሁኔታ መኖሩን የፌደራል ፖሊስ ሪፖርት ያሳያል ብለዋል።

ሆኖም ግን ባለፈው ሳምንት በቦረና ሞያሌ፣ በጉጂ እንዲሁም በባሌ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች በአዲስ መልክ ግጭት እንደነበረ ፌደራል ፖሊስ መግለፁን አስታውቀዋል።

በዚህ ግጭትም ከሁለቱም ክልሎች ከ20 በላይ ዜጎች ህይወት ማለፉን በሪፖርቱ ተመልክቷል ሲሉም ዶከት ነገሪ አብራርተዋል።

የፌደራል መንግስት እና የሁለቱ ክልል መንግስተታት ችግሩን ለመፍታት እየሰሩ ባለበት ወቅት ተጨማሪ ግጭት መከሰቱና የሰው ህይወት ማለፉ በጣም አሳሳዛኝ እና መሆን የሌለበት ክስተት እንደሆነ ግብረ ሀይሉ መገምገሙን አንስተዋል።

የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የሁለቱም ክልሎች የፀጥታ አካላት ለዜጎች ህይወት ጥበቃ እንዲያደርጉ እና በዚህ ተግባር የሚሳተፉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ ግብረ ሀይሉ አቅጣጫ ማስቀመጡን ገልፀዋል።

ተፋናቃዮችን በተመለከተ በአሁኑ ጊዜ የፌዴራል መንግስት በአደጋ ስጋት ስራና ዝግጁነት ኮሚሽን በኩል ክትትል ተደርጎ ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች በየጎዜው ሲሰጥ እንደነበረ እና አሁንም የሚደረገው ግዳፍ መቀጠሉን በሪፖርቱ ተብራርቷል ብለዋል።

ተፈናቃይ ዜጎች በአፋጣኝ ከመጠለያ ጣቢያዎች ወጥተው የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው እየተሰራ መሆኑን ግምገማው ያሳያል ብለዋል።

የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ላይም ግብረ ሀይሉ ትኩረት ሰጥቶ ገምግሟል ያሉት ዶክተር ነገሪ፥ በግምገማውም የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አኳያ ክፍተቶች መስተዋላቸው በሪፖርቱ ተገምግሟል ብለዋል።

በዚህም በኦሮሚያ ክልል በተለይም በአወዳይ አካባቢ በተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ የኦሮሚያ ክልል መንግስት እና የክልሉ የፀጥታ አካላት እስካሁን 54 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር አውለዋል ብለዋል።

እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የፌደራል ፖሊስ ገጭቱ በተከሰተበት አካባቢ በመንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው የተጠርጣሪዎች ቁጥር 44 መሆኑን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ሶማሌ ደግሞ የፌደራል ፖሊስ በራሱ ክትትል ባገኘው መረጃ እስካሁን 38 ተጠርጣሪዎችን መለየቱንና ከእነዚህም ውስጥ 29 ተጠርጣሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ ወጥቶ እስካሁን 5 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አብራርተዋል።

የሰላም ኮንፈረስ በተመለከተም ህዳር 10 ሊካሄድ የነበረው ኮንፍረንስ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄድ መቅረቱም ተነስቷል።

የሰላም ኮንፈረሱ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት በቅርብ ጊዜ እንደሚካሄድ አቅጣጫ መቀመጡንም ገልፀዋል።
 

%d bloggers like this: