በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለተፈጠረው ሁኔታ የተጠረቃቀሙ ጉዳዮች፡ በተለይም ‘በብሄረ ሰቦች ቀን’ የሌሎች ብሄረሰቦች ሙዚቃዎች ቦታ ማጣታቸው ጭምር ሁኔታውን ወደ ግጭት ወስዶታል!

12 Dec

ከአዘጋጁ፡

    አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እየታየ ያለው ሁኔታ የኢትዮጵያን ሕዝብ በየአካባቢው እያጋጠመው ያለው የፖለቲካ፡ ኢኮኖሚያዊ፡ ማኅበራዊ ኑሮና የደኅንነት ችግሮች ማይክሮኮዝም ነው!

    ሕወሃት በወታደራዊ ኃይል ጨበጣው ኢትዮጵያውያንን ሰብዓዊ መብቶቻቸውን፡ ቋንቋዎቻቸውንና ባህላቸውን በመርገጥ የራሱን የበላይነት ለማረጋገጥ ገና ከዚህ የከፋ ሥራም ሊሠራ እንደሚችል፡ በራሱ የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት እርሱን ማነጋገር እንኳ እንደማይቻል ከመግለጹ የከፋ ወራዳ የጥጋብ ጥጋብ የትኛው ዓለም ውስጥ ያለ ምሁርና ፖለቲክኛ የሚያሳየው?

    ለነገሩ ወጣቱ አማራ የተገደለው በዚሁ የአዲግራት ዩኔቨርሲቲ ውስጥ ሆኖ ሳለ፡ ከ20 የሚበልጡ ወጣቶች ተገሸላልጠው የጎዱበት ተቋምና፡ ባለፈው ጥቅምት ወርም አንድ ኦሮሞ ወጣት በትግሬዎች ዶርሚታሪ ውስጥ ታፍኖና ተደብድቦ የተገደለበትን ስናስታውስ፣ አሁን የአማራ ተወካይ የሆነውን ቡድን ለማነጋገር ፈቃደኛ አለመሆን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዛይድ ነጋሽ እንደ ክብር ጃኖ ለብሶት ይሆናል!!

============
 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት

“ሆኖም በ25 [የብሄረሰቦች ቀን] ዩኒቨርሲቲው በሚያውቀው መልኩ ተከብሯል”!

በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ በተነሳ ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱንና የመማር ማስተማር ሂደቱ መስተጓጎሉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ባህርዳር ፡ታህሳስ 2/2010 ዓ/ም (አብመድ) ስለግጭቱ መንስኤ እና አሁን ላይ እየተሰራ ያለውን ስራ በተመከለተ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የብአዴን አስተባባሪ አቶ ወንድወሰን ከበደ ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር በስልክ ቆይታ አድርገዋል፡፡

አቶ ወንድወሰን ከበደ እንዳሉት የግጭቱ መነሻ‹‹የብሄር ብሄረሰቦች በዓል በማክበር ላይ በነበረ ዝግጅት ሙዚቃዎች በሚቀርቡበት ወቅት የሁሉንም ብሄር መሰረት ያደረጉ አይደሉም፡ የሚል ሀሳብ ነው፡፡ሆኖም በ25 ዩኒቨርሲቲው በሚያውቀው መልኩ ተከብሯል፡፡ከዛ በኋላም በ10 ዲፓርትመንቶች በግል ያከበሩበት ፕሮግራም ላይ ማኔጀብል (የተደራጀ) ስላልነበረ በተወሰነ መልኩ የእኛ ሙዚቃ አልቀረበም በሚል ተነስቶ ነው ችግሩ የተፈጠረው፡፡በተወሰነ መልኩም እየሰፋ የመጣው፣ ዋና ምክንያቱም ያ ነው፡፡››

አልፎ አልፎ ደግሞ በግል ደረጃ የሚያነሷቸው ኢንተርስቶች /ፍላጎቶች/ ወልዲያ አካባቢ የተፈጠረውን ችግር ያነሱ ልጆች ነበሩ፡፡አሁን ላይ ችግሩ በቁጥጥር ስር እየዋለ ነው ፡፡የአንድ ሰው ሕይወት አልፏል፡፡ዛሬ ወደ አካባቢው የሚደርስበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

አቶ ወንድወሰን ከበደ ‹‹ቀላል ጉዳት 21 በሚደርሱ ተማሪዎች በመውደቅም በዲንጋይም ደርሷል፡፡ የተጎዱ አሉ፡፡እነሱም ህክምና ወስደው ወደ ዶርም የገቡ አሉ፡፡አሁን ላይ ከፌዴራልም ፣ከክልሉም ፣ከትግራይ ክልል እና ከጸጥታ ሀይሉ ጋር በቁርኝት እየሰራን ነው፡፡አሁን ስጋት የለም›› ብለዋል ፡፡

ችግሩን ይፈጥራሉ የተባሉ ‹‹ከ250 በላይ ልጆች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ዛሬም የማጣራቱ ስራ ይቀጥላል፡፡ወላጆች አሁን ላይ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሚያሰጋ ነገር አለመኖሩን ማወቅ አለባቸው ››ብለዋል፡፡

ዛሬ በተወሰኑ መልኩ የመማር ማስተማሩ ተጀምሯል፡፡የተወሰኑ ተማሪዎችም ገብተዋል፡፡

ክላስ ያልገቡ እና ውይይት እንፈልጋለን ያሉ ተማሪዎችም አሉ፡፡ከአማራ ተወላጆችም ጋር ውይይት መፍጠር፣ከትግራይ ፣ከደቡብ እና ኦሮምያም ጋር ያለውን ውይይት በእቅድ እየተመራ ይቀጥላል፡፤ ዛሬ የሀገር ሽማግሌዎች የማስተካከል ስራ ሰርተዋል ብለዋል፡፡

የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዛይድን ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

አማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተከታታይ ዘገባን ለመስራት ስምሪት ሰጥቷል፡፡
 

%d bloggers like this: