በወልዲያ አራት ተማሪዎች ተገደሉ፤ በጎንደር፡ ደብረታቦርና አምቦ የተማሪዎች አመጽ ተቀጣጥሏል!

12 Dec

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
by AbbayMedia
 

የአጋዚ ጦር ተመሪዎችን በመደብደብ ተጠምደው መዋላቸው ታውቋል፡፡ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች መያዝን ተቃመው የአዲግራት ከተማ ነዋሪዎች ሰልፍ መውጣታቸው ታውቋል! ተቃውሞዎች ተባብሰው ሕይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም በማድረግ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት የመንግስት ታጣቂዎች መሆናቸውን አመጽ ከተቀሰቀሱባቸው ተቋማት በተመሳሳይ የሚወጡ ሪፖርቶች ያስረዳሉ፡፡

በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ድብደባና ግድያ ተከትሎ በጎንደር፣ ደብረታቦር፣ ወልድያና አምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ቀሰቀሰ። እስክአሁን ባገኘነው መረጃ መሰረት በወልዲያ ከአራት በላይ ተመሪዎች ሲገደሉ በርካቶች ቆስለዋ። በደብረታቦርና ወልድያ ሕንጻዎች ላይ እሳት መነሳቱን ጨምሮ የአጋዚ ጦር ተመሪዎችን በመደብደብ ተጠምደው መዋላቸው ታውቋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሶስት ካምፓሶች የተነሳው የተማሪዎች ተቃውሞ ብሄርን ከብሄር የሚያጋጭ ስርአት አንፈልግም በሚል የስርአት ለውጥ የሚጠይቅ ነበር። በደብረ ታቦር እንዲሁ የተነሳውን የተማሪዎች ተቃውሞ ተከትሎ አንድ ሕንጻ ላይ የእሳት ቃጠሎ መድረሱ ሲታውቅ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም በአዲግራት የተፈጸመውን ድብደባና ግድያን በማውገዝ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

በአማራና ኦሮሚያ በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች አመጽ እንዲያገረሽ ምክንያት በሆነው የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ አሁንም ከሌላ ክልል የመጡ ተማሪዎች ከጊቢው እንዳይወጡ ታግደዋል። ይበልጡኑ በመከላከያ ሰራዊት ተክበው በሜዳ ላይ ጸሀይ ላይ እንዲውሉ ሲደረግ በሌላ በኩል ደግሞ ከተማሪዎች ግድያ ጋር በተያያዘ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች መያዝን ተቃመው የአዲግራት ከተማ ነዋሪዎች ሰልፍ መውጣታቸው ታውቋል፡፡

ከፍተኛ የተማሪዎች ተቃውሞ በታየባት ወልዲያ በአጋዚ ጦር ክአራት በላይ ተማሪዎች የተገደሉ ሲሆን የወልዲያ ሆስፒታል ለመቀበል ከአቅሙ በላይ እስኪሆን የደረሰ በርካታ ተማሪዎች ላይ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰ ታውቋል። የአጋዚ ጦር ተማሪዎችን ጫማ እያስወለቀ ሲደበድባቸው መዋሉን ጨምሮ የወሎ ሀገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት አቡነ ኤርሚያስ በስፍራው በመገኘት ሁኔታውን ለማብረድ የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ መዋላቸውም የተሰምቷል። አመሻሽ ላይ በዩኒቨርሲቲው ጊቢ ውስጥ በሚገኝ የቤተ-መጽሕፍት ሕንጻ ላይ እሳት መነሳቱ ታውቋል፡፡

ትናንት ሰኞ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተቀጣጠለው የተማሪዎች አመጽ ማምሻውን ጋብ ያለ ቢመስልም፣ በመንግስት ኃይሎች እንደተለመደው ሌሊቱን ድብደባና አፈና ሊፊጸም ይችላል ከሚል ስጋት ተማሪዎች ጊቢውን ለመልቀቅ ተገደዋል። አቅሙ ያላቸው ሆቴል በመያዝ ቀሪዎቹ ደግሞ በየቤተክርስቲያኑ ለመጠለል እየሞከሩ መሆኑም ክየከተማዎቹ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ተቃውሞዎች ተባብሰው ሕይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም በማድረግ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት የመንግስት ታጣቂዎች መሆናቸውን አመጽ ከተቀሰቀሱባቸው ተቋማት በተመሳሳይ የሚወጡ ሪፖርቶች ያስረዳሉ፡፡

ሪፖርቶቹ የጎንደር ተማሪዎች የጀመሩትን ሰላማዊ ተቃውሞ በመጥቀስ የመከላከያ፣ የፌደራልና የአጋዚ ሰራዊት ተቃውሞዎችን በሰላማዊ መንገድ ከማብረድ ይልቅ ተመጣጣኝ ባልሆነ ሀይል በመጠቀም፣ ድብደባና ግድያ በመፈጸም የሚሄዱበት መንገድተቃውሞዎች መልካቸው እንዲቀየር ከማድረጋቸውም በላይ በህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ያስረዳሉ፡፡
 

%d bloggers like this: