ከኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ ሕዝቡ ምን ይጠብቃል ሲል ይጠይቃል ፋና!

12 Dec

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
አዲስ አበባ፣ ታኅሳስ 3፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በዚህ ለዓመታት የሃገሬ ምድር ብለው ከኖሩበት ቀዬና ሃብት ንብረት ካፈሩበት አካባቢ፥ ዜጎች እንደዋዛ ከእኛ አይደላችሁም ተብለው ሲፈናቀሉ ማየትና መስማት አሁን አሁን በዚች ሃገር እየተዘወተረ ነው።

እነዚህ ግጭቶች ቂም እያዘሉ ሂደው በስፖርታዊ ክዋኔዎችና ለሃገር የሚጠቅም ተመራማሪና አስተዋይ ምሁር ማፍለቂያ ናቸው ተብለው በሚታሰቡ ዩኒቨርሲቲዎች ሳይቀር መስተዋል ጀምረዋል።

ሁኔታው ታዲያ መላ ኢትዮጵያዊያንን ሳያስጨንቅ አልቀረም።

ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ ውስጥ የሆኑት አስተያየት ሰጪዎች፥ አሁን እየታዩ ያሉ ግጭቶች ገጠር አካባቢ የሚገኙ ቤተሰብ ለመጠየቅ እንኳን አስቸጋሪ እየሆነባቸው መምጣቱን ተናግረዋል።

ሰው በሀገሩ በሰላምና በነፃነት የመኖር ዋስትና የማግኘት ሰብዓዊ መብት አለው፤ የኢፌዲሪ ህገ መንግስትም ይህን ይደነግጋል።

ሆኖም ግን አሁን የሚስተዋለው ነገር የሰዎችን ሰብዓዊ መብትም እየገፈፈ ስለመምጣቱ የአስተያየት ሰጪ ግለሰቦች ሃሳብ ነው።

ይሄ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ደግሞ ሄዶ ሄዶ ዜጎች ኢትዮጵያዊነታቸውን እንዲጠራጠሩም እያደረጋቸው መሆኑን ይናገራሉ።

እንደ አስተያየት ሰጪዎቻችን እምነት ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱ ፈተና የተጋረጠበት ይመስላል።

በአስተያየት ሰጪዎቻችን እሳቤ አሁን እየታዩ ያሉ የግጭቶች መቀስቀሻ ዋነኛ መሳሪያ የሆነው ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ነው።

“በህዝብ ዘንድ የሚመላለሱ በርካታ ጥያቄዎቸ አሉ” የሚሉት እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች፥ ሃገሪቱ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ በፍትሃዊነት እየተጠቀምን አይደለም የሚሉ ጥያቄዎች መኖራቸውን እንደ አብነት ያነሳሉ።

እናም ግጭቶችን ለማስቆም ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ላይ መሥራት ቅድሚያ ተሰጥቶ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ይመክራሉ።

በየመንግሥት ተቋማቱ ያሉ አሰራሮች አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ ፖለቲካ የተጫናቸው ናቸው ሲሉም እንደችግር ያነሳሉ።

መንግሥታዊ ተቋማት አቅመ ደካማ በሆኑ፥ ነገር ግን ፖለቲካ የተጫናቸው ሰዎች የሚመሯቸው ሰዎች የሞሏቸው መሆናቸው በታሰበው ልክ ህብረሰቡን ማርካት እየተሳናቸው መጥተዋል ብለው ነው የሚከራከሩት።

አሁንም ለግጭት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ጊዜው አልረፈደም የሚሉት እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች፥ ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ መነጋገር እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።

ምክንያቱም አሁን ላይ መንግስት እና ህዝብ እየተደማመጡ ያሉ አይመስሉም፥ ይህም ሕዝብ ጥያቄ አለኝ ብሎ ሲያነሳ ምላሾቹ ግን አጥጋቢ ያለመሆናቸው ችግሮቹን አባብሰዋል ብለው ያነሳሉ።

አሁን ላይ ለጥያቄዎች ሁሉ መልስ መስጠት የግድ ነው የሚሉት እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች፥ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቀሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከትናንት ጀምሮ ተሰባስቦ እየመከረ ነው።

ዋነኛ አጀንዳዎቹም ወቅታዊ የግጭቶች መንስኤና ሃገራዊ ጉዳዮች ተነስተው አቅጣጫ እንደሚቀመጥላቸው የፓርቲው ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ሙስና የዚህች ሃገር ሰንኮፍ ሁኗል፤ አመራሩም ይህን የሙስና ጥፋቱን ለመሸፋፈን የብሄር ካርድን እንደመጫዎቻ እያደረገው ነው።

የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ታዲያ ፓርቲውን ከሙሰኛ አመራር ለማፅዳት የመፍትሄ አቅጣጫን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

እንደ አቶ ሽፈራው ገለፃ በመሰረታዊ ድርጅቶች መሪዎች መካከል መጠራጠር አለ፤ ይሄ ያለመተማመን ግን ሊፈታ የሚችል መሆኑን ያነሳሉ።

አሁን የተፈጠረው ያለመተማመን የቆየና ከዓመት ዓመት እየተደራረበ የመጣ ነው ያሉት አቶ ሽፈራው፥ ቢዘገይም አሁን የፓርቲው አመራር ሀገሪቱን ከውደቀት ለመታደግ ሃላፊነት የተሞላበት ውሳኔ ያሳልፋል የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ።

በዚህ ሂደትም ተቀራርቦ በመነጋገር ወደ ጀምርነው ድህነትን ወደመታገያ የልማት አጀንዳዎቻቸችን እንመለሳለን ባይ ናቸው።
 

%d bloggers like this: