ለተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መዳከም ተጠያቂው ማን ነው? ሕወሃት ምን እየሠራ ነው? በሃገሪቱ የሚዲያ ነጻነት አለ ለማለት ታስቦ እንዳይሆን ይህ ሁሉ መንበዛበዝ?

13 Dec

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 25 ዓመታት 15 የፖለቲካ ፓርቲዎች የፈረሱ ሲሆን፥ አራት ጥምረቶች እና ቅንጅቶች ተበትነዋል።

በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመዳከማቸው ኢህአዴግን የሚከሱ ሲሆን፥ ኢህአዴግ ግን ችግሩ ከራሳቸው ነው ራሳቸውን ይመልከቱ ይላል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ተወካይ አቶ አዳነ ጥላሁን፥ ትልቁ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግር የመንግስት አፈና ነው ይላሉ።

የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አበበ አካሉም ይህንን ሀሳብ የሚጋሩ ሲሆን፥ ባልሰራነው ወንጀል መወንጀል እና ማስፈራራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቁ ፈተና ነው ይላሉ።

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አክለውም ከአዲስ አበባ እስከ ገጠር ቀበሌ ድረስ ጽህፈት ቤት ለመክፈት መቸገራቸውን እና ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ አለመቻላቸውንም በምክንያትነት አንስተዋል።

የኢዴፓ መስራች አቶ ልደቱ አያሌው፥ ይህ ሀገሪቱን የሚመራው መንግስት ጠንካራ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይኖር ተግቶ እየሰራ መሆኑን ማረጋገጫ ነው ይላሉ።

ይህ ብቻ አይደለም የሚሉት አቶ ልደቱ መንግስት በእለት ተእለት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰሩትን ተግባራት የማጣጣል ተግባር ስራ እየሰራ ነው ሲሉም ይናገራሉ።

የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለዚህ በሰጡት ምላሽ፥ ይህ የማይሆን እና የማይታመን ክስ ነው ብለዋል።

አቶ ሽፈራው፥ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለው ችግር ከራሳቸው ነው ራሳቸውን ይመልከቱ ሲሉም ተናግረዋል።

“ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እኮ የሰራተኛ ፓርቲዎች ናቸው ስለዚህ እነሱን ለማጥፋት ኢህአዴግ ጊዜ ማጥፋትም ይሁን ስምሪት መስጠት አይጠበቅበትም ይላሉ አቶ ሽፈራው።

ለዚህ ምክንያት ደግሞ “ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መጀመሪያውንም የሉም” ሲሉ አቶ ሽፈራው ይናገራሉ።

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለመዳከማቸው ኢህአዴግን ብቻ ሳይሆን፥ ራሳቸውንም ተጠያቂ ያደርጋሉ።

ለዚህ ደግሞ የሚያደርጉት ስብሰባ ዴሞክራሲያዊ አለመሆን እና የፓርቲያቸውን ሊቀመንበርነት ስፍራ ለመልቀቅ አለመፈለግን በማሳያነት ያነሳሉ።
 

%d bloggers like this: