አባቶች የሕወሃት አስተዳደርን መከሩ: “አጥፊዎችን ችላ እያለ ሕዝብን ማፋጀት የለበትም፤መጠየቅ መብት ነው! በአግባቡ መመለስ ግዴታ ነው!”

29 Dec

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

  * በመንግሥትም በቤተ ክህነትም መልካም አስተዳደር ጠፍቷል!

  * መጠየቅ መብት ነው፤ መላሹ በአግባቡ መመለስ ግዴታው ነው!

አቡነ ማትያስ፤ ለኢኦተቤ-ቴቪና ኢቢሲ

†††

  * በጎጥ መለያየት ጥሩ አይደለም፤ ጥንቃቄ ይደረግበት ስንል ጮኸናል

  * ሳይስፋፋ መከላከል ያስፈልጋል፤ ሓላፊነቱ ያለበት መንግሥት ነው

  * ቤተ ክርስቲያንን በሚያፈርሱት መንግሥት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፤ የሰሜን ምዕ/ሸዋ – ሰላሌ ሊቀ ጳጳስ፤ለአዲስ አድማስ

†††

ሰሞኑን በአገራችን የተለያዩ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በተከሠቱ ጎሠኝነት ተኮር ግጭቶች፣ የአራት ተማሪዎች ሕይወት መጥፋቱን መንግሥት አረጋግጧል፡፡ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች መፈናቀልና በመቶዎች ለሚቆጠሩቱ ኅልፈት ምክንያት የኾነው፣ የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የድንበር ግጭት ዳግም አገርሽቶ በርካቶች ለሞት መዳረጋቸውም ታውቋል፡፡ መንግሥት አጥፊዎችን ለሕግ እንደሚያቀርብ ያስታወቀ ሲኾን፣ በግጭቱ ለሞቱት ዜጎች ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማውና ለቤተ ሰዎቻቸው መጽናናትን እንደሚመኝ ገልጿል፡፡

የመንግሥት ሓላፊነት፣ የሐዘን መግለጫ ማስተላለፍ ብቻ ሳይኾን፣ ሞትም ኾነ ጉዳት በዜጎች ላይ እንዳይደርስ መከላከል ነው፡፡ ብዙዎች፣ ኹኔታው ስጋት ላይ እንደጣላቸውና በአፋጣኝ መፍትሔ ማበጀት ካልተጀመረ ወደ ጥፋት መንገድ ማምራታችን አይቀሬ ነው፤ ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡

ስለ ጉዳዩ ኢኦተቤ-ቴቪ እና ኢቢሲ ያነጋገሯቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ጥያቄዎች በወቅቱና በአግባቡ ቢመለሱ ችግሩ እዚህ እንደማይደርስ ገልጸዋል፡፡ “መጠየቅ መብት ነው፤ መላሹ አካል በአግባቡ መመለስ ግዴታው ነው፤” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በውስጥም በውጭም ያሉ ወገኖች ለሰላም ሊያደሉ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

የችግሩ መንሥኤ ፖሊቲካዊ ብቻ ሳይኾን የመልካም አስተዳደር ዕጦትም መኾኑን የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፣ “የምናየው ኹሉ የሚያስደስት አይደለም፤ በመንግሥትም በቤተ ክህነትም መልካም አስተዳደር ጠፍቷል፤” ማለታቸው ተጠቁሟል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከመጸለይ እንዳላቋረጠችና ስለ ሰላምም ድርሻዋን እየተወጣች እንዳለች ያስታወቁት ቅዱስነታቸው፣ ሌሎችም አካላት ለሰላም መስፈን ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ትላንት ዓርብ፣ ታኅሣሥ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ፣ በወቅታዊ ጉዳይ፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቪዥንና (EOTC Tv) ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (EBC) በጽ/ቤታቸው መግለጫ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ በዛሬ ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. እትሙ፣ “በዐዲሱ ትውልድ አእምሮ ውስጥ የተዘራውን የጎሠኝነት መርዝ እንዴት ማርከስ ይቻላል?” በሚል ጥያቄ መነሻ ካነጋገራቸው አንዱ የኾኑት የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፥ መንግሥት ሀገሪቱን በእኩልነት በመምራትና በማስተዳደር፣ አንድነትን የማጽናት ሓላፊነቱንና ተግባሩን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

“በጎጥ መለያየት ጥሩ አይደለም፤ ጥንቃቄ ይደረግበት ስንል ጮኸናል፤ የፈራነው እየደረሰ ነው፤” በማለት ያወሱት ብፁዕነታቸው፣ “አዝማሚያው ከተስፋፋ ኢትዮጵያ የለችም ማለት ነው፤” ብለዋል፡፡

መንግሥት አጥፊዎችን ችላ እያለ ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ፣ ሕዝብን እርስ በርስ የሚያፋጅ ሥራ መሥራት እንደሌለበት ብፁዕነታቸው መክረዋል፡፡ ከመንግሥት የሚጠበቀው የሐዘን መግለጫ ማስተላለፍና አዝኛለሁ ማለት ብቻ ሳይኾን፤ አጥፊዎችን ለሕግ በማቅረብ ሥርዐት ማስያዝ፣ ተጎጅዎችን ደግሞ ቦታ ማስያዝ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ትልቁ መሣሪያ ጸሎት ነው፡፡ በሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰላም ባለቤት እግዚአብሔርን በምሕላ ጸሎት እየለመነች መኾኑን የጠቀሱት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ “መንግሥት ደግሞ ሀገሪቱን በእኩልነት መምራትና ማስተዳደር አለበት፤” ብለዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያንን የሚያፈርሱ ባለሥልጣናት እንዳሉ አያይዘው ያነሡት ብፁዕነታቸው፣ ድርጊቱን በመቃወማቸውና እንዲታረም በመጠየቃቸው በተቃዋሚ ፓርቲ አባልነት መፈረጅ እንደማያዋጣ አስጠንቅቀዋል፤ መንግሥትም ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል-“ይኼ ከፈጣሪ ያጣላናል፤ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው እየኾነ ያለው፤ መንግሥት ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል፡፡”

“ምኞታችን፥ የሀገራችን አንድነት ጸንቶ፣ ልማት ሰፍኖ፣ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ማየት ነው፤” ብለዋል ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፡፡

††††††††††††††††††

“ከመንግሥት የሚጠበቀው አዝኛለሁ ብቻ አይደለም”

የሰላም ባለቤት እግዚአብሔር ነው፡፡ ለዚህም በሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን ፈጣሪን በምሕላ ጸሎት እየለመንን ነው፡፡ የእኛ ትልቁ መሣሪያችን ይኼ ነው፡፡ አደራ ተሰጥቶታል የተባለው መንግሥት ደግሞ ሀገሪቱን በእኩልነት መምራትና ማስተዳደር አለበት፡፡ አጥፊዎችን ለሕግ እያቀረበ ሥርዐት ማስያዝ አለበት፡፡ ተጎጅዎቹን ደግሞ ቦታ ቦታ ማስያዝ ይገባዋል፡፡ ዝም ብሎ ከዳር ኹኖ እንደ ማንኛውም ሰው አዝኛለሁ ቢል አይኾንም፡፡ ሓላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ እንደ ሌላ ሀገራት መንግሥታት እርሱም አብሮ የሐዘን መግለጫ ማስተላለፍ አይጠበቅበትም፡፡

ሐዘኑ እንዳይደርስ የመከላከል ሥራ መሥራት ግዴታው ነው፡፡ አንድነትን ማጽናት ሥራው ነው፡፡ ድሮም የተፈራው ይህ ዐይነቱ ግጭት እንዳይመጣ ነበር፡፡ በጎጥ መለያየት ጥሩ አይደለም፤ ጥንቃቄ ይደረግበት ስንል ጮኸናል፡፡ የፈራነው ነው እየደረሰ ያለው፡፡ አኹንም ሳይስፋፋ መከላከል ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ሓላፊነት ያለበት ደግሞ መንግሥት ነው፡፡

አዝማሚያው ከተስፋፋ ኢትዮጵያ የለችም ማለት ነው፡፡ እኔ በ1999 ዓ.ም ስለዚህ ጉዳይ የጻፍኩት መጽሐፍ አለ፡፡ በወቅቱ አስጊ መኾኑን ተናግረናል፡፡ መንግሥት ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ ሥራ መሥራት የለበትም፡፡ አንዳንዶችም ቤተ ክርስቲያናችንን እያፈረሱ ነው፡፡ ይኼ ከፈጣሪ ጋራ ያጣላናል፡፡ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው እየኾነ ያለው፤ እያለቀስን ነው፡፡ መንግሥት ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል፡፡

ይኼን ስንል የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ናቸው እንባላለን፡፡ ይኼ ደግሞ አያዋጣም፡፡ ሀገሪቱ አንድነቷ ጸንቶ፣ ልማት ሰፍኖ፣ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ማየት ነው፤ ምኞታችን፡፡ ሥልጣን የያዘ አካል ደግሞ በሥነ ሥርዐት መምራት አለበት፡፡ አጥፊዎችን ችላ እያለ፣ ሕዝብን እርስ በርሱ ማፋጀት የለበትም፡፡

(ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፤ የሰሜን ምዕ/ሸዋ – ሰላሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ለአዲስ አድማስ)
/ሐራ ዘተዋሕዶ
 

%d bloggers like this: