ሕወሃት ኢትዮጵያውያንን ሲተናኮል አዲስ አበባ መጻዒነት ላይ የሕወሃት ‘ትግራይም’ መወሰን አለባት ይላል — ሌላው ቀርቶ ‘ብሔራዊው ምክር ቤት’ እንኳ በሕዝብ የተመረጡ ተወካዮች ሳይኖሩበት!

30 Dec

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
by አዲስ ዘመን
 
ሕገ-መንግሥቱ የሁሉንም ሕዝቦች መብቶችና ጥቅሞች ያስጠብቃል። ዋና መነሻውም አንድ ጠንካራ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ነው።የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ልዩ ጥቅም በህገ-መንግሥቱ እንዲሰፍር ያደረጉትም የኦሮሞ ሕዝብን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸው፡፡ልዩ ጥቅም ሲባል ምን ማለት ነው?

ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ በምታገኘው ልዩ ጥቅም ላይ ማን ይወያይ?</strong>

Credit (Addis Zemen)


የኦሮሚያን ክልል ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ የሁሉንም ህዝብ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን መብቶችና ጥቅሞች በምንም መልኩ የሚሸራርፍ እንዳልሆነ፤ይልቁንም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም በመጠበቁ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል ሕዝቦችን ትስስርና መስተጋብር ይበልጥ ህጋዊ መሥመር ይዞ የሚያጠናክር ነው። ከዚህም በላይ የጋራ ተጠቃሚነትን በማጎልበት፤ ዘላቂ ሰላም በማስፈን ዋስትና ያለው ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ጎልብቶ ፈጣንና ሕዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ልማት እንዲስፋፋ የሚያስችል ነው ይላል፡፡ በዚህ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ምሁራንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሀሳባቸውን አካፍለውናል።

የአፍሪካ ሂዩማኒቴሪያን አክሽን ምክትል ፕሬዚዳንትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ እንዳሉት የአዲስ አበባ ጉዳይ የአንድ ክልል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ተደርጎ መወሰድ አለበት ይላሉ። ይሄ እንዳለ ሆኖ ሁሉንም የሚያስተዳድር አንድ ሉአላዊ የፌዴራል መንግሥት አለ። ይሄ መንግሥት ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ጋር ተነጋግሮ ጉዳዩን መጨረስ ይችላል።

እንደ ምሁሩ ማብራሪያ፤ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያለው ጥቅሞች ይከበሩ ሲባል የጥቅም ጉዳይ በመሆኑ የሚወሰነው ከብሄራዊ በጀቱ ጋር ተያይዞ መሆን አለበት። ኦሮሚያ ለልማት የሚያስፈልገው ገንዘብ ካለ በጀት ተመድቦ መሰራት አለበት።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሀገሪቱ ሉአላዊ ሀገር በመሆኗ አንድ የፌዴራል መንግስት ነው ያላት። ብሄራዊ በጀቱም አንድ ነው። ከዚህ በጀት ኦሮሚያ ጥቅም ማግኘት ካለባት እንደ ክልል በበጀቱ ከፌዴራል መንግስት ተመድቦ ጥቅሙን ተደራሽ ማድረግ ይቻላል። በጀት ደግሞ የሚያፀድቀው ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ምክር ቤቱ ሁሉንም ክልሎች ያቀፈና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የገቡ ህዝቡን የሚወክሉ አባላትን የያዘ ነው። በመሆኑም እዛ ላይ ተነጋግረው ሊያጸድቁት ይገባል። አስፈላጊ ከሆነም የኦሮሚያና የአዲስ አበባ አስተዳደር እንዲሁም ፌዴራል መንግስቱ ተነጋግረው እነዚህን ጥቅሞች ማስከበር ይችላሉ።

በተጨማሪም ጉዳዩን ተመልክቶ ምንያህል በጀት ይመደብ? በጀቱ ከየት ይምጣ ?የሚለውም መታየት እንዳለበት ይናገራሉ።ምክንያቱም ወጪው የሚሸፈነው ከአዲስ አበባ ብቻ በሚገኝ ገቢ ሳይሆን በብድርና በእርዳታ ከሚገኘውም ሊሆን ይችላል። በአሁኑ ወቅት ትልቁ የሀገሪቱ ገቢ የሚገኘውና ትልልቆቹ የልማት ስራዎች የሚከናወኑት ከታክስ ሳይሆን ከዳያስፖራው፣ ከእርዳታና ብድር ነው። ይህንንም ከግንዛቤ ማስገባት ይጠበቃል።

በጀቱ በሚበጀትበት ጊዜም ሁሉም ክልሎች ምን ጥቅም ያስፈልጋቸዋል የሚለውን ማየት ይገባል። አገልግሎት ስለሰጡ አልያም አንድ ቦታ ስለተገኙ ብቻ አይደለም።ኢትዮጵያ እኩል ታድጋለች እኩል የብሄር ብሄረሰቦች ተጠቃሚነት ይሰፍናል ማለት አንዱ ከሌላው ብቻውን ተጠቃሚ ወይም ተጎጂ ሆኖ እንዳይቀር የሚደረግ ጥረት ነው።

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ሲያስረዱም፤ በሀገሪቱ በልማት ወደኋላ የቀሩት ታዳጊ ክልሎች ልዩ ድጎማ የሚሰጣቸው ካለፉት መንግሥታት ምንም አይነት ጥቅም ስላላገኙ ከሌሎቹ ክልሎችና ህዝቦች ጋር እኩል እንዲሆኑ ታሳቢ በማድረግ ነው። የኦሮሚያን ተጠቃሚነት በዚህም ረገድ መመልከት አለብን እንጂ አሁን እየታየ እንዳለው ፓለቲካዊ አቅጣጫ ማስያዝ አይገባም ባይ ናቸው። ጉዳዩ ከጥቅም ማስጠበቅ አልፎ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሲሆን የችግር መነሻ ይሆናል። ሂደቱንም ሰላማዊ እንዳይሆን ያደርገዋል። በተለይም በዚህ ወቅት እንዲህ አይነቱ ነገር ችግሮችን የሚያባብስ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባል ሲሉ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።

ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው አዲስ አበባ የምትገኘው በኦሮሚያ መሬት ላይ ነው።የሌላው ክልል አልነበረችም። የአዲስ አበባ ህዝብ ፣የመንግስት ተቋማትና ሌሎችም ቦታና ጥቅማ ጥቅሞችን የሚያገኙት ከኦሮሚያ ክልል ነው። አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ውሃን ጨምሮ የምትጠቀመው በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶችም አሉ። በመሆኑም ኦሮሚያ ክልል የተለየ ጥቅም ማግኘት እንዳለበት መቀመጡ ተገቢ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

የኦሮሚያ ልዩ ተጠቃሚነት በህገ መንግስቱ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል ተብሎ የተቀመጠ ቢሆንም ላለፉት ሀያ ሁለት ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት በኦህዴድና በኢህአዲግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባዎች ላይ ምክር ቤቱ ህጉን እንዲያወጣ ጥያቄ ቢያቀርብም የተሰራ ነገር ግን አልነበረም። ከዚህ መነሻነት ሲታይ አሁን ለውሳኔ መቅረቡ ተገቢ ነው። በህገ መንግስቱ መሰረት ህግ የሚያወጣው ፓርላማው በመሆኑም አሁንም አስፈላጊውን ሂደት ተከትሎ ውሳኔ መስጠት አለበት። ይሄንን በማድረግ የኦሮሚያን ፖለቲካዊ፣ባህላዊና አስተዳደራዊ ግንኙነቶችና ተጠቃሚነት በፍትሀዊ መንገድ አስተካክሎ በጋራ መስራት የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል ሲሉ የዶክተር ቆስጠንጢኖስን ሀሳብ ይቃወማሉ።

ዶክተር ነጋሶ እንዳብራሩት ፌዴራላዊ ስርዓት መስርተን በጋራ እንኖራለን ተብሎ ጉዞ ሲጀመር አዲስ አበባ የኦሮሚያም የፌዴራሉም ዋና ከተማ መሆን እንዳለባት ተቀምጧል። የፌዴራል መንግስት አስተዳደር ተቋማት መቀመጫም ናት። በሀገሪቱ የሚገኝ ማንኛውም ዜጋ ህገመንግስቱ ያስቀመጠለት ራስን የማስተዳደር እንዲሁም ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች አሉ። እነዚህ መብቶች በአዲስ አበባ ለሚኖር ዜጋም መከበርና መጠበቅ አለባቸው። ይሄ እንዳለ ሆኖ በህገ መንግስቱ ይጠበቃል የተባለው የክልሉ መብት በመሆኑ በውሳኔው ላይ መወያየት ያለበት የኦሮሚያ ህዝብ ነው። ነገር ግን የኦሮሞ ህዝብም ግለኛ መሆን የለበትም የአዲስ አበባም ለኦሮሚያ ማሰብ አለበት ሲባል ሌሎች ክልሎችና ህዝቦችም ለኦሮሚያ ማሰብ አለባቸው ማለት ነው።

ከዚህ ውጪ ግን አሁንም ቢሆን ህጉ ይወጣል ተብሎ የነበረው ባለፈው ዓመት ቢሆንም ዘንድሮም አልፀደቀም። ስለዚህም ለሌሎች ችግሮችም ምክንያት እንዳይሆን በአስቸኳይ ውሳኔ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል ዶክተር ነጋሶ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቤ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት እንዳሉት የተዘጋጀው ህግ መነሻው ህገ መንግስቱ ነው፤ ህገ መንግስቱ ሲረቀቅ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ቦታዎች ከተማው እየሰፋ ሲሄድ የሚያመጣውን ጉዳት አስቀድሞ በመገንዘብ ምላሽ አስቀምጦለታል። ህጉ ከከተማዋ መስፋፋት ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን ከከተማዋ የሚወጣው ፍሳሽና ቆሻሻ የሚያስከትለውን ችግር፤ እንዲሁም ከቋንቋና ባህል ጋር በተያያዘ ለሚፈጠር የሚችለውን ተጽእኖ ከግምት በማስገባት ለኦሮሚያ ልዩ ጥቅም እንደሚገባ አስቀምጧል።

ከአዲስ አበባ ጋር በተያያዘ እየተጎዳ ያለው በዙሪያዋ የሚኖረው የኦሮሚያ ህዝብ ቢሆንም እንደ አካል የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ አካል ነው። አዲስ አበባም የፌዴራል መንግስቱና የኦሮሚያ ክልል ዋና ርእሰ ከተማ ከመሆኗ ባሻገር የአፍሪካ ህብረት መቀመጫና የተለያዩ የዓለም ድርጅቶች ማእከል ናት። በመሆኑም የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በጉዳዩ ላይ መወያየትና ሀሳብ ማቅረብ ይጠበቅበታል ሲሉ ዶክተር ነጋሶ መወያየት ያለበት የኦሮሚያ ህዝብ ብቻ ነው በማለት የሰጡትን ሀሳብ ይቃወማሉ።

በሀገሪቱ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ እየተገነባ በመሆኑ በአንድ አካባቢ ያለ ችግር የሌላውም ነው። በአንድ አካባቢ ያለ ህዝብም ከተጠቀመ የሁሉም ጥቅም ነው የሚሆነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ በየደረጃው በሚካሄደው መድረክ ላይ የራሱን አስተያየት የሚሰጥበት ሁኔታ ይኖራል። ያንን የሚሰጠውን ግብዓት በመጠቀም የሚዘጋጀውን ህግ ማዳበር ይቻላል። ለኦሮሚያ ክልል ህዝብም በበለጠ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ግልፅ እንዲሆን ይደረጋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ መስተዳድርና ኦሮሚያ ክልል ራሳቸው በሚያወጡት ፕሮግራም ሌሎችም ክልሎች በተመሳሳይ በሚካሄዱ ውይይቶች አዋጁ ይዳብርና ለህዝብ ይፋ የውይይት መድረክ የሚዘጋጅ እንደሚሆን ይናገራሉ። አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉትም በቀጣይ ህዝቡ በራሱ የመወሰን ሙሉ ስልጣን ስላለውና ረቂቅ አዋጁ ውጤታማ እንዲሆን በአዋጅ ላይ በምልአት እንዲሳተፍ መደረግ አለበት።
 

%d bloggers like this: