የሕወሃትንና የትግራይን የበላይነትና ትሥሥራቸውን ለያይቶ መገንዘብ ያስፈልጋል!

12 Jan

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)
 

ባለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያውያን፡ የሕወሃትን የበላይነት ባይቀበሉትም ጠንቅቀው አውቀውታል! በሕወሃት አባሎችና በመላው የትግራይ መካክለል የእኩልነት፣ የሃብትና የተደላደለ ኑሮ ጠበል ለሁሉም ባይዳረስ፣ የትግራይ
የበላይነት ከአድዋ ተጉዞ፣ በመካከላቸው ያሠረጸው ተስፋ በሃገሪቷ መጎርመት መመጀመሩ እያደር ይበልጥ እየታየ ነው!

ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለሕወሃት ሊቀመንበርነት በተመረጡ በሣምንት ውስጥ ነው በሕወሃት ስም የሚነግዱትን ለፍርድ እንደሚያቀርቡ ማስጠንቀቂያ የሠጡት። ይህ ማለት ደብረጽዮን ንጹህና ተሃድሶ በእርግጥ የመሻት ሳይሆነ፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጣ በድርጅቱ ሙሰኝናትና ዘረኝነት መማረሩን ከመገንዘብ ለጊዜው ለመቆጣጠር መሆኑ አያጠራጥርም።

ስለሕወሃት የበላይነት እየተነጋገርን እያለን ትግራዊ ካልሆኑ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ አስተያየቶች ተሠንረዋል። ሊሆን አይችልም የሚለው ኢትዮጵያዊነትን ያንጸባረቀ ጥርጥር ከሚያሳዩ — ከዚህ በላይ ምን ያድርጉን — እስከሚሉ በጋለ ቁጣ የተሞሉ ዜጎችም አሉ።

እኔ እንደምገነዘበው፣ ካለፈው ዓመት ይልቅ ዘንድሮ እኔም የሕወሃት የበላይነት አለ ወደሚለው ብቻ ሳይሆን፡ የትግራይም የሚያሰኙኝ ብዙ ምልክቶች እየታዩኝ ነው። እያንዳንዱ ሕዋታዊም ከልብ ያምንበታል።

በሌላ አባባል፣ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዛሬ ትልቁ ተግባር የእነዚህን አንድነትና ልዩነት አበክሮ ማየትና መከታተል፣ እንዲሁም የሃገራችንን ነጻ የማውጣቱ ትግል አካል ማድረግ ያስፈልጋል!

ይህ እንደሚሆን ሕወሃትም ስላወቀ፡ በኅዳር 2017 የ35 ቀናት የፖሊት ቢሮውና ማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባው ጭምር — አሁንም መቀሌ ላይ — ይህንን ለማስተባበል ጉንጫቸውን ሲያለፉ እየታየ ነው!

ከላይ ስለተጠቀሱት የሕወሃትና የትግራይ የበላይ መደረግ በየአቅጣጫው ብዙ ምልክቶችን ማየትና በየፈርጁ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ማንነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለሰበረው የጋምቤላ የትግሬዎች መሬት መቀራመትና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ መሥፈርን በተመለከተ የተፈጸመውን በማቅረብ እንደሚከተለው ልጀምር።

የኢትዮጵያ የልማት ባንክ ጋምቤላ ውስጥ በሕወሃት አባሎች ምክንያት ከፍተኛ ኪሣራ እንደደረሰበትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በኩል በአቶ ዓለማየሁ ተገኑ ሰብሳቢነት ጥናት ተካሂዶ፡

    (ሀ) ዕርዳታው በገፍ የተሠጠው ለትግሬዎች መሆኑን

    (ለ) ብድሩ ለእርሻ ልማት ቢሠጣቸውም አንዳንዶቹ እንደቆመሩበትና እዚህ ግባ ሊባል የሚችል የእርሻ ልማት እንዳልሠሩ፡ አንዳንዶቹም አዲስ አበባና ውጭም ቤቶችና መኪናዎች እንደገዙበት ተነግሯል።

ለባንኩ እንኳ ዕዳቸውን እንዳይከፍሉ አቤቱታ ስላሰሙ ነባሩ የኢትዮጵያ የልማት ባንክ እንዲከሥር፡ ሕዋታውያኑ ግን ከዕዳ ነጻ እንዲሆኑ ሸፈንፈን ያለ የሕወሃት አሰተዳዳራዊ ውሳኔ ተላልፎበታል።

ጋምቤላ ለእርሻና ግብርና ሥራ ለኪሣራ አዲስ አይደለችም። የሃገር ውስጥም ሆኑ ባዕዳን አልሚዎች ሲደፉ፣ የሕወሃት አስተዳደር እየከሰሰ እንዳስከፈለ ወይንም ንብረቶቻቸውን እንደያዘባቸው እናስታውሳለን። ‘እንነኬ ባዮቹ’ — የሕወሃት መሣፍንት — ግን ኢትዮጵያን እያደሙ ናቸው።

ለምን ይህ ሆነ ቢባል፣ ብዙም ማሰላሳል አያስፈልገውም! ኢትዮጵያ ኖረች ባፍጥሟ ተደፋች — የፈለገውን ወንጀል ሕወሃቶች ይፈጽሙ (ዕውቁን ‘መስመር’ እስካላለፈ ድረስ) — ከሕወሃትና ትግሬዎች ጥቅሞችና ደህንነት አይበልጥም ነው አስተሳሰባቸው።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ኪሣራውን ተቀብሎ፣ የዛሬ ሁለት ዓመት የኢትዮጵያ ግብር ከፋይ ባንኩን እንደገና ከብር አምስት ቢሊዮን በላይ ከፍሎ እንዲያቋቁመው (recapitalise) ተደርጓል። ነገር ግን ባንኩ አሁንም ለእነዚህ የሕወሃት ሰዎች — ሲቪልና ወታደሮች — ዕርዳታውን እንዲቀጥል በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ‘ተወስኖላቸው’ ሁለተኛ ዕድል ተሠጥቷቸው ነበር።

የፋና ዜና እንደሚያሳየው፡ አዲስ ልገሳ ከተደረገም በኋላ የባንኩ ኪሣራ ቀጥሎ፡ በሚያስገርም ሁኔታ የሕወሃትን ቁጣ የፈራው የኢትዮጵያ የልማት ባንክ ብድርን እንደገና መሥጠትና መከልከልን እኩል ሚዛን ላይ እንዲያስቀመጥ ተገዷል!

በሁለተኛ ዙር ኪሣራ እንደተጣራው የ3.63 ቢሊዮን ብር ውድቀቱን (በባንክ ቋንቋ 64% non performing loans) ተብሎ፣ አሁንም ከ472 እርሻዎች መካከል ተስፋ ይኖራቸው ይሆናል የሚባሉት 158 ሲሆኑ፣ የሌላው ኢትዮጵያዊ ጉሮሮ ተዘግቶ ቀሪው የዚህች ደሃ ሃገር ሃብት እነርሱ ላይ መፍሰሱ ይቀጥላል!

በሌላ አባባል፣ አሁን እንደታየው የተወሰኑቱ (33 ከመቶ) ብድራቸው እንዲቀጥል ምልክት ተሠጥቷል!

የልማት ባንክ አዲስ ባወጣው የወደፊት አቅጣጫው፡ ካበደረው 5.6 ቢሊዮን መካክል የተረፈ የሚመስለውን (እርግጠኛ አይደለም) በእጁ ያለውን ይዞ አሁንም ለሕወሃት መሣፍንት ያውለዋል። የባንኩ ስትራቴጂ ዲሬክተርና ቃል አቀባይ አቶ ክፍሌ ሃይለኢየሱስ እንዳሉት፡

“ብድር ወስድው የፕሮጀክት አፈጻጸማቸው ደካማ የሆኑ ተበዳሪዎችን በተመለከተ ባንኩ ሀብቱን ለማስመለስ ሊሰራ እንደሚችልም በአማራጭ ተቀምጧል።”

ይህ ማለት፣ ማንም በባንኩ ላይ ላደረሱት ውድቀት ተገቢውን ዕዳና ካሣ እንዲከፍሉ ማድረግ የሚችልና የሚያስችል የሕግ አቅም ጭምር በባንኩና በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ባለመኖሩ፡ ሕወሃቶች በኢትዮጵያ ላይ እየተሳለቁ ነው!

በባንክ አሠራር በየታኛውም ሃገር የሃገሪቱን ሕግ በመጠቀም ገንዘቡን ወስዶ በአግባቡና በወቅቱ ያልመለሰው ደንበኛ እስከ መቀጫ ጭምር እንዲከፈል፤ አለያ ንብረቱ እንዲታገድ፣ በሃራጅ እንዲሸጥና ለባንኩ እንዲከፈል ሕግ ያስገድዳል። ከዚህ ዐይነቱ ዓለም አቀፍ አሠራር ነጻ የሆኑት (privileges & immunities ያላቸው) — ሕጋዊ መሠረት ባይኖረውም — የሕወሃት አባላትና ትግሬዎች ብቻ ናቸው!

ከሌላ ብሄር የመጡ ሰዎች፡ በኢኮኖሚ ውስጥ ልቀው መውጣታቸው ሕወሃትን ስለሚያስፈራው፣ በተለያዩ ምክንያቶች እንዲደናቀፉ ይደረጋል። ለጥፋት ምክንያት ይፈልግባቸዋል። ቢሳካላቸውና ቢቋቋሙ ደግሞ፣ ሕወሃት ምክንያት ፈልጎ ያፈርሳቸዋል!

የኅብር ስኳር ፋብሪካ እንዲቋቋም ከ6,000 ባለመዋጮች መሥራቾች ሆነው — እነአቶ አማረ ለገሠ፡ የወንድወሰን በቀለ፡ኃይሌ ዋጋውና ምናላቸው ስማቸው — በአመራርነት ከ2009 (በፈረንጆች) ጣና በለስ ላይ ተመርተው ሊጀምሩት መሥመር ከያዘ በኋላ የሽንሎራ ምርት ለማምረት መሬት ተፈቅዶላቸው በድንገት መከልከላቸውና አመሰራረታቸው እንዲፈርስና ክስም መመሥረቱ ይታወሳል — ሪፖርተርም በወቅቱ እንደዘገበው።

ለምን አማሮች ብቻ ሆኑ ከሆነ፣ በምን ሂሣብ ትግሬዎች ብቻ ሃገራችንን “ረግጠው መግዛት”ተፈቀደላቸው የሚለው ጥያቄ የሃገራችን ዘለቄታ የሚወሰንበት ጉዳይ ነው!

ጥር 11/2018 የእሥረኞችን መፈታት አስመልክቶ ኢሣት ባቀረበው ዜና፡ አስገራሚው ነገር በአሁኑ ወቅት መቀሌ የከተመው የሕወሃት ተሰብሳቢዎች በአንደ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሶስት ሺህ የሚሆኑ የትግራይ ወጣቶች የእሥረኞች ፍቺ ላይ ስምምነታቸውን እንደሚሻ ተጥቅሷል።

ለምን ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አልተጠየቀም? አያገባችሁም ነው! ወይንስ በሃገሪቱ ጉዳይ ትግራዎች ሌላው የሌለው ድምጽ አላቸው የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ታቅዶ ነው?

ይባስ ብሎ፣ ሰሞኑን ስለፖለቲከኛ እሥረኞች መፈታት ሲነገር፡ ሕወሃቶች በገጾቻቸው አንድ ዘመቻ ብቻ ነበራቸው ሰሞኑን በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ሕዝብን እርስ በእርስ ለማጣላት ሲሞክሩ የነበሩን አስመልክቶ፡ — “የፖለቲካ እስረኞች የምትፈቱ ከሆነ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አከባቢዎች “ኦነግ ናችሁ” “ሰላይ ናችሁ” ተብለው የለበጣ ፍርድ የተፈረደባቸው ተጋሩም የዚህ አካል መሆን አለባቸው…”

ከእነዚህ ሁኔታዎች ተነስተን ተነስተን ነገሩን ስናጤነው፡ የሃገራችን የፖለቲካ፡ የደህንነትና የኢኮኖሚ ችግሮች እጅግ የተወሳሰቡና፣ ዛሬ ሊታመን ከሚችለው በላይ የገማ የገለማና አሳሳቢ ነው — በሕወሃቶች ምክንያት!

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ ትግሬዎችና ሌሎች ኢትዮጵያውያን እኩል ነን፣ ወይንም የትግራይ የበላይነት አለ የለም ለሚለው ጥያቄ ግራ የተጋቡት ወገኖቻችን ጠንቀቅ ብለው ሊያስቡበት ይገባል! ሕወሃት ይህቺን ዓመት ከተሻገረና በዚሁ የዘራፊነት ባህሪው ከቀጠለ፣ ይህ ውይይት አይኖርም —ሁኔታዎች በfait accompli! ሕግ እየተገዙ!

ባለፉት ከሁለት ዓመታት በላይ በሃገራችን የሚታየውን የሕዝብ ቁጣና ሃገሪቷ ውስጥ የተጠናከረው ለሕውሃት ያለው ጥላቻ፡ መሠረቱ ይህ የሕወሃት የዘረኝነት ፖለቲካና አጓጉል ብልጣ ብልጥነት ነው!

በሃገራችን እኩልነት፣ ዲሞክራሲና የዜጎች ሲቪል መብቶች መከበር ለሕግ የበላይነት መሠረት ሆኖ መውጣት፡ ይበልጥ ለሕወሃቶች እንደሚበጃቸው ቢገነዘቡ በጋራችንና መከባበራችን ይበልጥ እነርሱ በመጀመሪያ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን በቻሉ ነበር።
 *Updated

ተዛማጅ:

    Gambella’s failed commercial agriculture & Tigrean investors; TPLF nepotism, lawlessness & corruption; Sebhat Nega rooting for Tigrean land grabbers: Unequal Ethiopianity is the challenge in 2017 (Part I)

    Gambella land grab breeds TPLF lawlessness & corruption; DBE & its ponzi scheme at the centre of it!

    The issue in Gambella commercial farms is ethnicity. Why are some Ethiopians more privileged than others, in Gambella the army killing tens of thousands to keep them ‘safe’! There’s crime to unveil!

 

%d bloggers like this: