ሕወሃት መደናገጡ ሲያይልበት ዜጎችን ማደናገሪያና ማደንዘዣ እንዲሆኑ ተግባራዊ የማይሆኑ የልማት ሥራዎችን ይደረደራል

13 Jan

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)
 
የሕወሃትን አሰተዳደር ከሁሉም መንግሥታት ለየት የሚያደርገው፡ ውሸትና ማምታታት ያላንዳች ማወላወል ከዓመት ዓመት ዋነኛ የፖለቲካና ፕሮፓጋንዳ መሣሪያው አድርጎ መቆየቱ ነው።

ለምሣሌ ዛሬ ቅዳሜ ሪፖርተር ስለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ባቀረበው ዜና በአሁኑ ወቅት የሁለተኛው ዙር የአምስት ዓመት የልማት ፕላን ስለቱሪዝም ከተቀመጠው ግብ 90 በመቶ ተግባራዊ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ለፓርላማ ምሥክርነታችውን መሥጠታቸውን ሪፖርተር ይጠቅሳል።

በ2020 ዓ.ም.ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ሃገሪቱን እንዲጎበኙ ለማደረግ የወጣውን ዕቅድ በተያዘው የበጀት ዓመት የመጀመሪያዎች ስድስት ወር 485,806 ቱሪስቶች ሃገሪቱን በመጎብኘት $1.8 ቢሊዮን ገቢ መገኘቱን፣ ሪፖርተር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯን በመጥቀስ ዘግቧል።

በ2020 የቱሪዝም ዘርፉ — ሪፖርተር እንደዘገበው — 1.2 ሚሊዮን ቱሪስቶችና እንደሚያስተናግድና ሃገሪቱም $4.2 ቢሊዮን እንደምታገኝ የቱሪዝም ምክትል ሚኒስትሯ መዓዛ ገብረመድኅን ተንብየዋል።

በመስኩ ያሉ የሃገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎች ደግሞ ገቢውን ቁጥሩንም ፈጠራ በማለት ያጣጥሉታል። ዋናው መከራከሪያቸው፣ አንደኛ ኢትዮጵያ ይህን ያህል ቱሪስቶች ሊያስተናግድ የሚችል መሠረተ ልማት ስለሌላት፡ የተባለው ቁጥር እስክሪፕቶ እንደፈጠረው፤ ሁለተኛ፡ የቱርስቶቹ ቁጥር የተወሰደው ከኢሚግሬሽን መዝገብ እንደሆነና የተባሉት በሙሉ ቪዛ ለማግኝት ምክንያታቸውን ሃገር ጉብኝት ይበሉ እንጂ ቱሪስቶች አለመሆናቸውን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

ቱሪዝም ትልቅ የገቢ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ቢታመንበትም፣ የሕወሃት አስተዳደር የዜጎችን ቅሬታ አዳምጦ መልስ ከመስጠት ይልቅ በተለይም የዶ/ር ደብረጽዮን ዐይነቶችና መሰሎቻቸው የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶችን በመርገጥ፣ ዜጎችን አላግባብ በማሠርና በመግደል፣ ከ2015 ጀምሮ ኢትዮጵያ ነውጥ ውስጥ እንድትገባ በማድረግ ቱሪዝም መዳከሙ ግልፅ ነው።

ይህም እንኳ ሳይሆን፣ ሃገሪቱ በዓለም አቀፍ ቱሪዝም ደረጃ በዓለም 120ኛን በአፍሪካ 17ኛ መሆኑን ሪፖርተር መረጃውን አካፍሏል።

ስለሆነም፣ አሁን ባለው ይዞታ፣ የቱሪስት ኢንዱስትሪው ተገቢውን ድጋፍ ለልማት ማበርከት አልቻለም።

በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሃገሪቱ የውጭ ንግድ (ቡና፣ ወርቅ፣ የቅባት እህሎች፣ ጫት፣ ወዘተ) ገቢ፣ በተለይም ከ2015/2016 ጀምሮ በ28 ከመቶ መቀነሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዘግቧል። እስከዛሬ መሻሻል አልታየም።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሃገሪቱ ከውጭ የምታስገባቸው ሸቀጦች በከፍተኛ ደረጃ መቀነሳቸው፡ ተያያዥ የልማት ሥራዎችን መጉዳቱ ብቻ ሣይሆን፣ ለዜጎች ሕልውና አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒቶችን እንኳ ማስገባት አስቸጋሪ ሆኗል።

የሃገሪቱ የወጭ መጠንና ፍላጎቶች በብዙ ዕጥፍ ጨምሯል። ከዚህ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት የመከላከያና ደኅነነት ወጭ ከፍተኛ ደረጃ በመድረሱ የልማት ግቦችና ጥረቶች በአብዛኛው እየተተው ነው።

ሕወሃት ታዲያ ልማት በፍላጎት ብቻ የሚከናውን ይመስል፡ ራሱን “ልማታዊ መንግሥት” ብሎ ሠይሞ፣ እንዳሁኑ በሕዝባዊ አመጽና አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲከማቹበት ልማትንም የአፍና የወሬ ጉዳይ አድርጎት ዕርፍ ብሏል።

ከመቀሌው የሕወሃት ስብሰባ፣ የኢሕዴግ ጉባኤያቸው ሰሞን ፋና ሲደረድራቸው የነበሩ፡ (ሀ) አዳዲስ የሚወጡ ሕግጋት፡ (ለ) የሚሠሩ አዳዲስ ተቋማዊ ሥራዎች፣ (ሐ) የመሠረተ ልማት ሥራዎች ዝርዝር ቀላል አይደሉም።

እስቲ የሰሞኑን — ከሁለተኛው የመቀሌ ጉባኤ ወዲህ በመደዳ መጉረፍ የጀመሩትን እንመልከታቸው፦

    *   የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር ማሰልጠኛ አካዳሚ ግንባታ ሊጀምር ነው

    *   በኦሮሚያ ክልል በ9 ሆስፒታሎችና 61 ጤና ጣቢያዎች የማስፋፊያ ግንባታ ሊካሄድ ነው

    *   የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በመዲናዋ ከ16 ሺህ በላይ ቤቶች እንደሚገነባ አስታወቀ

    *   በአዲስ አበባ ከ16 በላይ አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሊጀመር ነው

    *   በመዲናዋ የኩላሊት ህክምናን በአንድ ቦታ የሚሰጥ ማዕከል ሊቋቋም ነው

 

ባለፈው ዓመት እንደሚታወሰው፣ የ$14 ቢሊዮን በጀት ለ2017/2018 ሲዘጋጅ ትልቁ ችግር ግብር በተገቢው መጠን ለመሰብሰብ ባለመቻኩ፡ ገንዘብ ሚኒስቴር በጀቱ እንደጸደቀ 19 የግዥ ዘቀጦች ላይ ወጭ እንዳይደረግ ማገዱ ራሱ በቂ ማስረጃ ነው።

የሕወሃት አስተዳደር የገንዘብ (የበጀት) ዕጥረት አለበት! የሃገሪቱ ምርት አለመሻሻልና የውጭ ንግዱም ፈር አለመያዙ፡ ብዙ የኤኮኖሚ ችግሮች ይታያሉ። የዋጋ ግሽበት በ13% ላይ እንዲቆም ተደርጓል ቢባልም፣ የእህል ዋጋ ውድነት፣ የሸቀጣሸቀጦች አለመገኘትና ቢገኙም የዋጋቸው ጣራ መንካት ከገበያተኛው አቅም በላይ አድርጎታል።

በአስተዳደሩ በኩልም፣ የገንዘብ ዕጥረት አለ — የውጭ ምንዛሪ ብቻ ሣይሆን የሃገር ውስጥ ገንዘብም!

ሕወሃቶችም ያውቃሉ፤ እኛም እናውቃለን! የአመራር ፓርቲው የሕዝብ ተቃውሞ በተጠናከረበት ሁኔታ ውስጥ ስብሰባ ሲቀመጥ፣ በበጀት ገንዘብ ያልተያዘላቸው ሥራዎች ሁሉ ይሠራሉ የሚለውን ለዚህ በተዘጋጁ ፕሮፓጋንዲስቶች የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳውን ማስተጋባቱን ያካሄዳል!

ዋናው ጥያቄ — ከእነርሱ ዘረፋ የተረፈው — ገነዘብ እንኳ የታልና ነው እነዚህን እነዚያነ የልማት ሥራዎች ተግባራዊ እናደርጋለን የሚሉት በየሣምንቱ?
 

%d bloggers like this: